ዓውደ ጥበባት ሚዲያ - Awede Tibebat Media

ዓውደ ጥበባት ሚዲያ - Awede Tibebat Media Contact information, map and directions, contact form, opening hours, services, ratings, photos, videos and announcements from ዓውደ ጥበባት ሚዲያ - Awede Tibebat Media, Religious organisation, አዲስ አበባ, Dire Dawa.

ዓውደ ጥበባት ሚዲያ ትኩረቱን በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ ትምህርቶችና ጉዳዮች ላይ ትኩረት አድርጎ በጥበብ ቃለ ወንጌልን ለማዳረስ ለጥያቄዎችዎ ምላሽ በቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት ለማሰጠት ያልታዩና ያልተዳሰሱ የቤ/ክ ጉዳዮችን በመዳሰስ ምዕመናንን ለማንቃትና ለማስተማር የሚሰራ ሚዲያ ነው!

"የባዕዳን ስም የማጥፋት ዘመቻ፣ የቤተ ክርስቲያኗን እምነት ከመንቀፍና ከማብጠልጠል በላይ አልፎ የቅዱሳንን ቅዱስ ሥዕል በአደባባይ እስከ መቅደድ ተደርሶአል" ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ በስ...
22/10/2025

"የባዕዳን ስም የማጥፋት ዘመቻ፣ የቤተ ክርስቲያኗን እምነት ከመንቀፍና ከማብጠልጠል በላይ አልፎ የቅዱሳንን ቅዱስ ሥዕል በአደባባይ እስከ መቅደድ ተደርሶአል" ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!

• ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ
የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ፤

• ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ
የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ፣

• ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት፣

በአጠቃላይ በዚህ ዓመታዊ ቅዱስ ጉባኤ የተገኛችሁ በሙሉ፤
የጎደለብንን እየሞላ አገልግሎታችንን እያቃና ከዚህ ላደረሰን፣ ይህንን ዓመታዊና ሐዋርያዊ ጉባኤያችንን ለማካሄድም ለሰበሰበን ለአምላካችን ለእግዚአብሔር ምስጋና እናቀርባለን፡፡

“ወእፌጽም ታሕጻጸ ሕማሙ ለክርስቶስ በሥጋየ በእንተ ሥጋሁ እንተ ይእቲ ቤተ ክርስቲያኑ፡- ስለ አካሉ ማለትም ስለ ቤተክርስቲያኑ ስል በሥጋዬ በክርስቶስ መከራ የጎደለውን እፈጽማለሁ” (ቈላ.፩÷፳፬) \

ያለንበት ዓለም በሁሉም ነገር በጉድለቱ የሚታወቅ ነው፤ ጉድለት ባይኖርና ሁሉም የሞላለት ቢሆን ኖሮ ፍጥረት እርስ በርስ የሚተረማመስበት ሁኔታ አይኖርም ነበር ወይም አሁን ባለበት ደረጃ የከፋ አይሆንም ነበር፡፡

እግዚአብሔር ሁሉንም አሟልቶ መፍጠር ወይም መስጠት የሚችል ከሃሊ አምላክ ቢሆንም፣ እሱ ባወቀ ፍጥረትን ሁሉ ጉድለት ያለበት አድርጎ ፈጥሮታል፤ በዚህም ምክንያት እያንዳንዱ ጉድለቱን ለመሙላት በሚያደርገው ፍትጊያ እየተጋጨ እርስ በርስ ሲተረማመስ ማየቱ የተለመደ ነው፡፡ ምድራዊቷ ቤተ ክርስቲያንም በጐዶሎው ዓለም እስካለች ድረስ ከሚመጣው ፈተና አታመልጥም፤ ይህም በመሆኑ ቅዱስ ጳውሎስ ለቈላስይስ ሰዎች “የጎደለውን እፈጽማለሁ” በማለት ሲጽፍ እናስተውላለን፡፡

• ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት!

በጐዶሎው ዓለም የምትኖር ቤተ ክርስቲያን ጉድለቷን ለመሙላት ብዙ መሥዋዕትነት ከፍላለች፤ ቤተ ክርስቲያን ለቀጣዩ ትውልድ መሸጋገርና የጐደለባትን ለመሙላት ስትል ከቅዱሳን ሐዋርያት አንሥቶ እስካለንበት ዘመን ድረስ ብዙና የብዙ ብዙ አበው ካህናትን፣ ሊቃውንትንና ምእመናንን ከደም ጠብታ፣ እስከ ቁስ ስጦታ ገብራለች፡፡

አሁን በምድር ላይ ያለችው ቤተ ክርስቲያን የዚህ ሁሉ ውጤት ናት፤ ቤተ ክርስቲያን እንደ ሌላው ጊዜ ሁሉ ዛሬም የጐደለባት ብዙ ነገር አለ፤ በተቻለ መጠን እርሱን ለሟሟላት መጣርና በተሻለ ሁኔታ ወደፊት ማሻገር ደግሞ የዚህ ጉባኤ ተቀዳሚ ተግባር ነው፡፡ በዚህ ረገድ ይህ ጉባኤ ብቻው አይደለም፤ በብዙ ሚሊዮኖች የሚቈጠሩ የእግዚአብሔር ልጆች ድምፁን ለመስማት ከዙሪያው ሆነው በጉጉት ይጠብቃሉ፡፡ እነኝህ የእግዚአብሔር ልጆች ለመስማት ብቻ ሳይሆን ድምፁን ሰምተው ለመታዘዝም የተዘጋጁ ናቸው፣ ከሁሉ በላይ ደግሞ “ሁለትም ሦስትም ሆናችሁ በስሜ በተሰበሰባችሁበት እኔ በመካከላችሁ እገኛለሁ” በማለት ጉባኤውን የመሠረተው አምላክ ከዚህ ጉባኤ መካከል አለ፡፡

በመሆኑም ይህ ጉባኤ የተወሰን አባቶች ብቻ ሳንሆን ብዙ ሰማውያንና ምድራውያን ባለድርሻ ያሉበት፣ መንፈስ ቅዱስም በመንፈስ የሚመራው እንደሆነ የማይታበል ነው፡፡ ከዚህ አንጻር ጉባኤው በምድር ያለችውን የእግዚአብሔር መንግሥት በበላይነት የሚመራ ነውና፣ ያለበት ኃላፊነት ከባድና እጅግ የላቀ ነው፡፡ ጉባኤው ኃላፊነቱን በአግባቡ ሲወጣ የሚሰጠው ሽልማት ታላቅ እንደሆነ ሁሉ፣ ኃላፊነቱን በትክክል ካልተወጣ ደግሞ ተጠያቂነቱ በዚያው ልክ ከባድ ነው፤ ብዙ ከተሰጠው ብዙ ይፈለጋል ተብሎአልና፡፡

• ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት!

እኛ በአገልግሎትና በመሪነት በምንገኝበት በዚህ ዘመን ቤተ ክርስቲያን የጐደሉባት ነገሮች ብዙ ናቸው፤ ከሁሉ በላይ በውስጣችን የአንድነት ጐድለት በስፋት ይታያል፤ ለተሰየምንለት መለኮታዊ ተልእኮ አንድ ሐሳብ፣ አንድ ቃል፣ አንድ ልብ ሆነን መሰለፍ ያለመቻል ክፍተት እየተንጸባረቀ ነው፡፡ የዘመኑን ጥበብና ስልት ያልተከተለ ሐዋርያዊ ተልእኮአችንና አስተዳደራችንም ምእመናንን አላረካም፤ ክፍተቱ የሚድያ ቀለብ ከመሆንም አልፎ በጎቻችን በሌሎች እንዲዘረፉ ትልቅ በር እየከፈተ ነው፡፡ በእነዚህ ዓበይት ጉዳዮች እና በመሳሰሉት ጉድለቶቻች ላይ ፈጣን፣ ቈራጥና አዋጭ የሆነ ሥራ ካልሰራን ለወደፊት የቤተ ክርስቲያንን ህልውና ጥያቄ ውስጥ መክተቱ አይቀሬ ነው፡፡

• ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት!

ቤተ ክርስቲያናችን በተጠቀሱት ችግሮች ተከባ ባለችበት ሁኔታ የሀገራችን ሰላም መቀዛቀዝ ደግሞ ሌላው ተጨማሪ ጉድለትን እያስከተለብን ነው፡፡ አማንያን የመንፈስና የሥነ ልቡና ሰላም ከማጣታቸውም በላይ አካላቸው ለሞትና ለጉዳት፤ ሃብታቸው ለዝርፊያና ለውድመት እየተዳረገ ነው፡፡ ይኽም ሁሉ ሆኖ ፍትሕን እያገኙ አይደለም፤ አብያተ ክርስቲያናትም በምእመናን ፍልሰት እየተዘጉም እየተቃጠሉም ነው፡፡

ከዚህም ሌላ የሌለን ነገር እንዳለ አስመስሎ ከየአቅጣጫው የሚወረወረው የባዕዳን ስም የማጥፋት ዘመቻ፣ የቤተ ክርስቲያኗን እምነት ከመንቀፍና ከማብጠልጠል በላይ አልፎ የቅዱሳንን ቅዱስ ሥዕል በአደባባይ እስከ መቅደድ ተደርሶአል፤ በቤተ ክርስቲያናችን ህልውና ላይ በዓላማ የተነሡ አካላት የላኳቸው እንዳሉ በሚመስል መልኩ በስመ ተሐድሶ የሚደረገው እንቅስቃሴ የኛው መለያ የሆነውን ንዋየ ቅድሳትና ልብሰ ተክህኖ፣ መዝሙርና ሥርዓተ አምልኮ በመጠቀም ቤተ ክርስቲያናችንን በአደባባይ እየተዳፈረ ይገኛል፡፡

ይህ አላስፈላጊ ተግባር የሀገሪቱን ዜጎች በእኩልነት የሚያስተዳድረውን ሕገ መንግሥት በቀጥታ የሚፃረር ድርጊት ነው፤ ሆኖም በሕግ የሚጠይቅና የሚያስቆም አካል አልተገኘም፤ እኛም ዝምታን የመረጥን መስለናል፡፡ ነገር ግን መፍትሔው ዝምታ ሳይሆን በሕግ አግባብ ነገሩን ለመፍታት መንቀሳቀስ እንደሆነ ሁሉም ሊገነዘበው ይገባል፡፡

• ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት!

በዘመናችን እየተከሠተ ያለው ችግር ስንዘረዝር ውለን ብናድር መናገሩ በራሱ መፍትሔ ሊያመጣልን አይችልም፤ ጉባኤው ከዚህ በላይ መናገር እንደሚችልም እንገነዘባለን፤ ነገር ግን ለዚህ ሁሉ ችግር ዘላቂ መፍትሔ ሊያመጣ የሚችል መደላድል ይህ ጉባኤ በዚህ ስብሰባ ሊተልም ይገባል ብለን ከአደራ ጋር ማሳሰብ እንወዳለን፡፡ በሌላ በኩል በሀገራችን ያለው ያለመረጋጋት በሕዝባችን አጠቃላይ ሥነ ልቡና በሀገሪቱ አንድነትና ዕድገት የሚያስከትለውን ጫና በቀላሉ የሚታይ አይሆንም፤ የሕዝቡ ሥነ ልቡና ከተጐዳ የነገው ዕድል ጤናማ ይሆናል ተብሎ አይታሰብም፡፡

ችግሩ እየታየ ያለው በዋናነት በሀገራችን ፖለቲከኞች በመሆኑ ነገሩ የተወሳሰበና የተራዘመ እንዲሆን አድርጎታል፤ በመሆኑም ይህ የርስ በርስ ግጭት ቆሞ ችግሮች በውይይትና በድርድር በመፍታት የወንድማማች እልቂት የሚያስቆም የሰላምና የዕርቅ ዕድል ቅድሚያ እንዲሰጠው ጉባኤው የበኩሉን ጥረት ማድረግ ይገባዋል፡፡ የነገው ትውልድ ልማታዊ ተስፋ እውን ሊሆን የሚችለው ሰላምና አንድነት ሲኖር ነውና መንግሥት፣ ተፎካካሪ ፖለቲከኞችና ነፍጥ ያነሡ ወገኖች ሁሉ ለሰላም መስፈንና ለልማት ዕድገት መረጋገጥ ሲባል ወደ መግባባት እንዲመጡ በእግዚአብሔር ስም አባታዊ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን፡፡

በመጨረሻም ዓመታዊውና ቀኖናዊው የቅዱስ ሲኖዶስ ዓቢይ ጉባኤ በዛሬው ዕለት በጸሎት የተከፈተ መሆኑን ለሕዝበ ክርስቲያኑ በእግዚአብሔር ስም እናበስራለን፡፡

እግዚአብሔር የተባረከና የተቀደሰ ጉባኤ ያድርግልን፤

እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቦችዋን ይባርክ
ወስብሐት ለእግዚአብሔር፤ አሜን፡፡

አባ ማትያስ ቀዳማዊ
ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ
ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት

ጥቅምት ፲፪ ቀን ፳፻፲፰ ዓመተ ምሕረት
አዲስ አበባ - ኢትዮጵያ

በተቀዳሚ ሙፍቲ ሐጅ ዑመር ኢድሪስ ሕልፈተ ሕይወትን በማስመልከት ከቅዱስ ሲኖሲኖዶስ ጽ/ቤት የተሰጠ የኀዘን  መግለጫ
20/10/2025

በተቀዳሚ ሙፍቲ ሐጅ ዑመር ኢድሪስ ሕልፈተ ሕይወትን በማስመልከት ከቅዱስ ሲኖሲኖዶስ ጽ/ቤት የተሰጠ የኀዘን መግለጫ

በተራዘመዉ ጦርነት የፍልስጤም ክርስትያኖች 800 ብቻ ቀርተዋል !ግብፅ በፍልስጤም የወደሙ መሳጂዶችን ዳግም ለመገንባት አዲስ አረብ ሀገራት የሚሳተፉበት የገቢ ማሰባሰብያ ለማዘጋጀት ቃል መግባ...
14/10/2025

በተራዘመዉ ጦርነት የፍልስጤም ክርስትያኖች 800 ብቻ ቀርተዋል !

ግብፅ በፍልስጤም የወደሙ መሳጂዶችን ዳግም ለመገንባት አዲስ አረብ ሀገራት የሚሳተፉበት የገቢ ማሰባሰብያ ለማዘጋጀት ቃል መግባቷ ተሰምቷል አብያተክርስቲያናቱን ግን እስካሁን ዳግም ለመስራት አልተገኘም ።

በአንድ ወቅት አለምአቀፋዊው ጳጳሳዊ ፋውንዴሽን በዓለማች 38 አገሮች ውስጥ ክርስቲያኖች ስቃይና በደል እንዲሁም መገለል እንደሚደርስባቸው ከሰባቱ መካከል አንዱ ስቃይ መከራና ስደት እንደሚዳረግ
በጥናት አረጋግጧል ። ጥናቱ እንደገለፀው ከሆነ ደግሞ ክርስቲያኖች የሚገፉት የእምነቱ መፍለቂያ ከተባለው መካከለኛው ምስራቅ ነዉ ከቀዳሚዎቹ ደግሞ ፍልስጤም ትጠቀሳለች ።

እስኪ ለዛሬው እንደሌሉ ተቆጥረው ልሳን ቸግሯቸዉ በሁለት ጉልበተኞች መሃል ተገኝተው ህልዉናቸዉ አደጋ ላይ ስለሚገኘው የፍልስጤም ክርስትያኖችና አብያተክርስቲያናት ጥቂት ልበል ።

ፍልስጤም በጥንታዊ እና በዘመናዊው የመካከለኛው ምስራቅ ታሪክ ውስጥ ታላቅ ሚና ያለው አንድ አነስተኛ ክልል ነው። ለበርካታ የዓለማችን ዋና ዋና እምነቶች ካለው ጠቀሜታ እና በአፍሪካ እና እስያ መካከል ጠቃሚ የሆነ አገናኝ ድልድይ የሆነ መልከዓ ምድራዊ አቀማመጥ ያለው በመሆኑ የፍልስጤም ታሪክ ተደጋጋሚ በሆነ ፖለቲካዊ ግጭት እና በአደገኛ የመሬት ወረራ የተሞላ ነው።

ይህ ሰርጥ ከግጭቱ በፊት በነበረ ቁጥራዊ መረጃ ከሆነ ሰፊውን ቁጥር የሚይዙት አረቦች ከዚህም ውስጥ በአብዛኛው የሱኒ ሙስሊም ሀይማኖት ተከታይ ቢሆንም ቅሉ ቀላል የማይባል አናሳ ክርስቲያኖች ይገኙበት ነበር።

የጋዛ ክርስቲያኖች ቁጥራቸው እምብዛም ባይሆንም እኒህ የጋዛ ክርስቲያኖች በቤተ-ክርስቲያኑ ዙሪያ ካለው መሬት ጋር ትልቅ ቁርኝት ስላላቸው ከጥንት እስከዛሬ እምነታቸው አስጠብቀው መዝለቅ ችለዉ ነበር ። ነገር ግን ከሁለት አመት በፊት አይ.ሁ..ዳዊ መሰረት ባላት እስራኤልና ከስሙ መነሻ ጀምሮ ለእስልምና እንደሚታገል የሚገልጸው ሃማስ ጦርነቱ ተቀሰቀሰ ።

በሀማስና እስራኤል በተራዘመ ጦርነት ምክንያት በ365 ስኩዌር ኪሎሜትር በ40 ኪሎሜትር የባህር እርዝማኔ ክልል ዉስጥ የምትገኘውን 2 ሚሊዮን በላይ ዜጎች ይኖሩባታል የተባለችዉን ጋዛ ሰርጥ የምድር ገሀነም ሆነች ሁለቱም ፅንፍ በመያዝ አፀፋ በሚመላለሱበት ወቅት በሁለቱም ዘንድ በሰላይነት የተፈረጁ እነዚህን ክርስትያኖች እና የእምነት ተቋማት ከቁብ የሚቆጥር ጠፋ ።

እስራኤል " የሐማስን መሪዎች ላይ ያነጣጠረ " እያለች በምትፈፅማቸዉ ንፁሃንን ከታጣቂዎች ያለየ ጥቃትና በሰማይ የቦንብ ዶፍም ሆነ ሃማስ ሰላይ ናችሁ በማለት በሚያደርስባቸዉ ማህበራዊ መገለል መፈጠራቸውን እስኪጠሉ መከራ ገጠማቸው ።
በዓለም ላይ ካሉት ጥንታዊ አብያተ ክርስቲያናት አንዱ በዓለም ላይ ካሉት ጥንታዊ አብያተ ክርስቲያናት አንዱ እንደሆነ የሚታመነዉ በ400 ዓ.ም አካባቢ በቅዱስ ፖርፊየስ እራሱ ባሰራው ቤተክርስትያን መሰረት ላይ እንደታነፀ የሚነገርለት በአለም ላይ ካሉ ጥንታዊ አብያተ ክርስትያናት አንዱ የሆነዉ በአለም ሶስተኛው ጥንታዊ ቤተክርስትያን ወደመ ።
የክርስቶስ የልደት ስፍራ በሆነችው የፍልስጥኤም ግዛት የዌስት ባንክ ከተማ ቤቴልሄም እና በጋዛ ሰርጥ የሚገኙ ክርስቲያኖች የልደቱን በዓል እንዲያከብሩ ተከለከሉ ሌሎችም አብያተክርስቲያናት እንዳልነበሩ ሆኑ ።

ምንድነው ማስረጃዎችህ ከተባልኩ አለምአቀፋዊ ሚዲያዎችን መጥቀስና ዘገባዎችን ማስታወስ ይቻላል ።

ለአለም አቀፍ የወንጀል ችሎት (ICC) የወንጀል ምርመራ ሪፖርት እንደገለፁት ከአምስት በላይ አብያተ ክርስቲያናት የ150 ዓመታት ታሪክን መዛግብትን ጨምሮ ተጎድተዋል ወይም ወድመዋል። ሲል ገልፆታል ።

በጋዛ የባህል ዘርፍ መጥፋት፣ ቤተመጻሕፍት እና የባህል ቅርሶች በመውደማቸው እንዳስደነገጣቸው ባለሙያዎቹ ተናግረዋል። "የፍልስጤም ማህበረሰብ መሰረቱ ወደ ፍርስራሽነት እየተቀየረ ነው፣ እናም ታሪካቸው እየጠፋ ነው።" ብለዉታል ።

በአለፉት ሁለት ዓመታት የጋዛ አነስተኛ ክርስቲያኖች መካከል 550 የሚጠጉ ሰዎች ከቤታቸዉ ከቤተክርስቲያን ተፈናቅለው
የመቃብር ሥፍራዎች ለመኖር ተገደዋል. ሲል ፎክስ ኒዉስ ዘግቧል ።

በጋዛ የሚኖሩ ክርስቲያኖች እስራኤል የምትፈፅመው ሞትና ውድመት እንዲያበቃ በመጸለይ የገናን በዓል አክብረዋል። በዌስት ባንክ ከተማ ቤተልሔም የኢየሱስ የትውልድ ቦታ በርካቶች ጸሎታቸውን ያቀረቡ ሲሆን በእስራኤል “የዘር ማጥፋት” ሰለባዎችን በማስታወስ ፀሎት አድርገዋል። የሚለው ዘገባ የ ዋሽንግተን ፖስት ነዉ ።

በ2024 እስራኤል በጋዛ ሰርጥ ከሚገኙት ሶስት አብያተ ክርስቲያናትን ሙሉ በሙሉ አፍርሳለች ሲል የግዛቱ ኢንዶውመንት ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ለአናዶሉ ተናግሯል።

ኢክራሚ አል ሙዳላል እንዳሉት የእስራኤል ጦር ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ጋር ግንኙነት ያላቸውን 255 የሀይማኖት አባቶች እና መግደሉን እና ሌሎች 26 ሰዎችን ማሰሩን ተናግረዋል። ብሏል የአናዶሉ ዘገባ

" የአምልኮ ቦታዎች ላይ በፀጥታ ሃይሎች ላይ የሚፈፀመው ጥቃት ሁሉንም ቅድስናዎች፣አለም አቀፍ ህጎች እና የሰብአዊ መብት ህጎችን መጣስ ነው"ብለዋል።

በአውሮፓውያኑ 2024 ጥቅምት 19 አመሻሽ ገደማ ከእስራኤል የተወነጨፈ ሚሳዔል አንዱን የቤተ-ክርስቲያኑን ሕንፃ መታው። በጥቃቱ 18 ሰዎች ተገደሉ፤ በርካቶች ቆሰሉ።

ማሪያን እንደምትለው የ34 ዓመቱ የባሏ ወንድም ሶሊማን ልጆቹን ከሕንፃው ፍርስራሽ ሲከላከል ሕይወቱ አልፏል።

“በጣም አስፈሪ ነው። የሞተ ሰው አይቼ አላውቅም። ምን ማለት እንዳለበኝ አላውቅም። በጣም ፈጣን ሞት ነበር።”

ራሚ ታራዚ ደግሞ ሕንፃው በሚሳዔል ሲመታ በሥፍራው የነበረውን ሁኔታ ሲያስታውስ “ከባድ ሚሳዔል ነው። በጣም ትልቅ ከመሆኑ የተነሳ በሌላኛው ሕንፃ ውስጥ የነበሩ ሰዎች አቧሯ ለብሰው ነው የወጡት” ይላል።

የእስራኤል መከላከያ ሠራዊት ቤተ-ክርስቲያኑ በአቅራቢያው በነበረ የሐማስ ይዞታ ላይ በተሰነዘረ ጥቃት እንደተጎዳ አምኗል። የቢቢሲ ዘገባ ነበር ።

በቀድሞው ትዊተር በአሁኑ ኤክስ ላይ የተለጠፈ ቪድዮ፣ አንድ የእስራኤል ወታደር የወደቀ ሃይማኖታዊ ሕንፃን በእብራይስጥ ቋንቋ ሲያቆሽሽ አስመልክቷል።

ቢቢሲ ለእስራኤል መከላከያ ይህን ቪድዮ ልኮ አስተያየት ቢጠይቅም ምላሽ አላገኘም።

የለንደን ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ የአርኪዮሎጂ ተቋም ፕሮፌሰር የሆኑት ጆርጂያ አንድሪው፣ በጋዛ ሰርጥ ጉዳት የደረሰባቸውን ሕንፃዎች ሲያጠኑ ቆይተዋል።

ፕሮፌሰሯ እኒህ ሃይማኖታዊ ሥፍራዎች በጣም ትልቅ ታሪካዊ ጠቀሜታ አላቸው ይላሉ።

“[ጥቃቱ] ሰዎች ከእነዚህ ሕንፃዎች ጋር ያላቸውን ቁርኝት ለማጥፋት እንደተደረገ ሙከራ ነው መታየት ያለበት” የሚሉት ምሑሯ መሰል ውድመት አይተው እንደማያውቁ ይናገራሉ።

በአለም ሶስተኛው ጥንታዊ ቤተክርስትያን ነው ተብሎ የሚታሰበው በዉስጡ የያዛቸውን ታሪኮቹ ቅርስና መዛግብቶችን እንደያዘ ወደ አመድነት መቀየሩን ተከትሎም ።

የቤተ ክርስቲያኒቱ መሪዎችም ጉዳዩን በተመለከተ መግለጫ ያወጡ ሲሆን “የጋዛ ሕዝብ፣ በአያቶቻቸው ምድር ለትውልድ የኖሩ ቤተሰቦች፣ በግዞት መገደድ የለባቸውም፣ የተረፈውን ቤታቸውን፣ ቅርሶቻቸውን፣ እና የማንነታቸው መገለጫ በሆነው ምድር ላይ የመቆየት መብታቸውን ሊነጠቁ አይገባም” ሲሉ መናገራቸውን አልጀዚራ ዘገባ ያሳያል ።

የኢየሩሳሌም አብያተ ክርስቲያናት እንደ ክርስቲያን በጋዛ ሕዝብ ለሚደርስባቸው መከራ ግድየለሾች ሊሆኑ እንደማይችሉ "ወንጌል የሰውን ልጅ ሁሉ ክብር እንድንጠብቅ ያዘናልና።"
የአለም አቀፉ ማህበረሰብ በጋዛ ያለውን ሰብአዊ አደጋ ለመግታት አፋጣኝ እና ቆራጥ እርምጃ እንዲወስዱ ያሳስባሉ።

የሰው ልጅ ሕይወት ቅድስና እና መከላከያ የሌላቸውን የመጠበቅ የሞራል ግዴታ ከጥፋት እና ተስፋ መቁረጥ ይበልጡ። ተስፋ የቆረጡ ሰዎች አፋጣኝ ያልተገደበ ሰብዓዊ እርዳታ እንዲደረግ እንጠይቃለን።"ያሉት ኩስቶስ ብፁዕ አቡነ ፍራንቸስኮ ፓተን
"ልመናቸውን በእምነት እና በተስፋ መልእክት ሲያጠቃልሉ፣ የኢየሩሳሌም ቤተ ክርስቲያን መሪዎች ለሐዘን መጽናናት፣ ለቆሰሉት ፈውስ እና መከራ ቢደርስባቸውም በአገራቸው ለሚቀሩት ጽናትን ለማግኘት እንደሚፀልዩ ተናግረዋል ። በማለት የዘገበው ጀሩሳሌም ፖስት ነበር ።

እነዚህና ምናልባት በዝርዝር ብፅፋቸዉ አንባቢያን እንዳይሰለቹ የተዉኳቸዉ በሁለቱም ወገኖች በሀማስና እስራኤል በተራዘመ ጦርነት ምክንያት በ365 ስኩዌር ኪሎሜትር በ40 ኪሎሜትር የባህር እርዝማኔ ክልል ዉስጥ የምትገኘውን ጋዛ ሰርጥ ይኖሩ በነበሩ ክርስትያኖች ላይ የደረሱ ግፎች ናቸው ። ከዚህ ምስቅልቅል በኋላ ለወትሮው ጥቂት የነበረው የፍልስጤማውያን ክርስትያኖች ቁጥር አሽቆልቁሎ 800 ብቻ ቀርቷል ። እነዚህም የማምለኪያ ስፍራዎች ስለወደሙባቸዉ መቀጠላቸው ያጠራጥራል ሲል ያስነበበው ደግሞ አለምአቀፋዊ የክርስቲያን ህብረት ነዉ ።

( ታዴ የማመይ ልጅ በየኔታ ትዩብ )

ዜና ሀዘን በታላቋ ገዳም የዳግማዊ ምኒልክ መታሰቢያ ታዕካ ነገሥት በአታ ለማርያም ገዳም የመምህራን እና ቀሳውስት ማሰልጠኛ መንፈሳዊ (አብነት) ት/ቤት በሐዲስ ኪዳን መምህርነት ከግማሽ ምዕተ...
01/10/2025

ዜና ሀዘን

በታላቋ ገዳም የዳግማዊ ምኒልክ መታሰቢያ ታዕካ ነገሥት በአታ ለማርያም ገዳም የመምህራን እና ቀሳውስት ማሰልጠኛ መንፈሳዊ (አብነት) ት/ቤት በሐዲስ ኪዳን መምህርነት ከግማሽ ምዕተ ዓመት በላይ ያገለገሉት ታላቁ ሊቅ መጋቤ ሐዲስ የኔታ ደምፀ አንበርብር ከዚኽ ዓለም ድካም በዕረፍተ ሥጋ ተለይተዋል።

ታላላቅ ሊቃነ ጳጳሳትን እንዲኹም በቅድስት ቤተ ክርስቲያን የአስተዳደር መዋቅር ታላላቅ የኃላፊነት ድርሻዎችን የተወጡ ሊቃውንትን ያፈሩት የኔታ ደምፀ በቅርቡ በሕማመ ሥጋ መክረማቸው የሚታወስ ሲኾን ትላንት መስከረም 20 ቀን 2018 ዓ.ም. ማምሻውን ማረፋቸው ተሰምቷል።

ሊቁ የኔታ ደምፀ ለምዕመናን ታላላቆቹን የውዳሴ ማርያም እና ቅዳሴ ማርያም ፤ አቡነ ዘበሰማያት አንድምታ ትርጓሜ በመጽሐፍ መልክ በማዘጋጀት ለምዕመናን ተደራሽ ማድረግ የቻሉ አባት ናቸው፡፡

የአባታችን በረከታቸው ይደርብን!

መስቀሉ ለክርስቲያኖች የተሰጠበት ምክንያት!ሀ. መስቀሉ ለክርስቲያኖች ምልክት ነው   ምልክት መለያ መታወቂያ ነው፡፡ መስቀልም ክርስቲያኖች ከኢ-አማንያን /ከአህዛብ/ የሚለዩበት ከእግዚአብሔር...
26/09/2025

መስቀሉ ለክርስቲያኖች የተሰጠበት ምክንያት!
ሀ. መስቀሉ ለክርስቲያኖች ምልክት ነው
ምልክት መለያ መታወቂያ ነው፡፡ መስቀልም ክርስቲያኖች ከኢ-አማንያን /ከአህዛብ/ የሚለዩበት ከእግዚአብሔር ዘንድ የተሰጠ ምልክት ነው፤ ‹ለሚፈሩህ ምልክትን ሰጠሃቸው› (መዝ59፡4) እንዲል። እስራኤል ዘሥጋ በግብፅ ሳሉ ከቀሳፊ መልአክ እንዲድኑ የበጉን ደም ምልክት በቤታቸው በመቃኑና በመድረኩ እንዲረጩ በእግዚአብሔር ታዘው ነበር፡፡ በዚህም የደም ምልክት ከቀሳፊ መላእክ ተጠብቀዋል፡፡ (ዘፀ 12፡13) ክርስቲያኖችም በክርስቶስ ደም መዳናቸውን የሚያበስር የመስቀሉ ምልክትነት ነው፡፡
ለ. መስቀሉ ለክርስቲያኖች ሃይል ነው
ሃይል መንፈሳዊ ሃይል ሰማያዊ የምናገኝበት ከእግዚአብሔር የተሰጠን ይህ ቅዱስ መስቀሉ ነው። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ይህንን ሲገልፅ ‹የመስቀሉ ቃል ለሚጠፉት ሞኝነት ለእኛ ለምንድን ግን የእግዚአብሔር ኃይል ነው› (1ቆሮ 1፡18) ብሏል፡፡ ‹ለሚጠፉት› ብሎ በመስቀሉ ለሚቀጠቀጡ ለአጋንነት አንድም አጋንንት አድሮባቸው በክህደት ለፀኑ ኢ-አማንያን /መናፍቃን/ የመስቀሉ ነገር ሞኝነት ይመስላል፤ ሐይማኖት አፅንተው ምግባር አቅንተው መስቀሉን መጠጊያ ላደረጉ ምዕመናን ግን ኃይል ነው ማለቱ ነው፡፡ ከዚህ ኃይለ ቃል ጋር ቅዱስ ዳዊትም ይተባበራል። (መዝ 43፡5) ‹በአንተ ጠላቶቻችንን እንወጋቸዋለን በስምህም በላያችን የቆሙትን እናዋርዳቸዋልን› ብሏል። እኛም ክርስቶስ በሰጠን በመስቀሉ ኃይል ስመ ሥላሴን በመጥራት ማለትም በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ በማለት በትምህርተ መስቀል በማማተብ በላያችን የቆሙ ማለትም ኃጢአት በማሳሰብና በማሰራት የሚታወቁ አጋንንትን ድል የምንነሳበት በቅዱስ መስቀሉ ኃይል እንደሆነ እንረዳለን፡፡
ሐ. መስቀሉ ለክርስቲያኖች መመኪያ ነው
መስቀል በጥንተ ታሪኩ የእርግማንና የኃጢአት አርማ ሆኖ መቆየቱ ቢታወቅም ዛሬ ግን የክርስቲያኖች መመኪያና አለኝታ መከታና የድል አርማ ነው፡፡
ከክርስቶስ መስቀል በቀር ሌላ ትምክህት ከእኔ ይራቅ (ገላ 6፡14) አይሁድ በመገረዝና ሕግን በመፈፀም ይመካሉ ጳውሎስ ግን በክርስቶስ የመሥዋዕትነት ሥራ ይመካል በእግዚአብሔር ክብር ተስፋ እንመካለን (ሮሜ 5፡2) መከራ ትዕግሥትን እንደሚያደርግ ትዕግሥትም ፈተናን ፈተናም ተስፋን እንደሚያደርግ እያወቅን በመከራቸውን እንመካለን (ሮሜ 5፡3) በማለት ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ እንደተናገረው ዲያብሎስ ድል የተነሣበት እኛም የቀደመ ክብራችንን ያገኘንበት በመሆኑ መስቀል ትምክህታችን ነው፡፡

https://youtu.be/snLLsdXxotg?si=NA6vRSIcebwPdhW8
25/09/2025

https://youtu.be/snLLsdXxotg?si=NA6vRSIcebwPdhW8

ዓውደ ጥበባት ሚዲያ ትኩረቱን በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ ትምህርቶችና ጉዳዮች ላይ ትኩረት አድርጎ በጥበብ ቃለ ወንጌልን ለማዳረስ ለጥያቄዎችዎ ምላሽ በቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት ለማሰጠት ያልታዩና...

https://youtu.be/EVqmZJ8mD5s?si=vnntyMhmkFQQu_L0
17/09/2025

https://youtu.be/EVqmZJ8mD5s?si=vnntyMhmkFQQu_L0

ዓውደ ጥበባት ሚዲያ ትኩረቱን በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ ትምህርቶችና ጉዳዮች ላይ ትኩረት አድርጎ በጥበብ ቃለ ወንጌልን ለማዳረስ ለጥያቄዎችዎ ምላሽ በቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት ለማሰጠት ያልታዩና...

ርኅወተ ሰማይ እና ጳጉሜ 3 የሊቀ መላእክት ቅዱስ ሩፋኤል መታሰቢያ                                                                              ...
08/09/2025

ርኅወተ ሰማይ እና ጳጉሜ 3 የሊቀ መላእክት ቅዱስ ሩፋኤል መታሰቢያ ጳጉሜ የሚለው ስያሜ “ኤፓጉሜኔ” ከሚለው የግሪክ ቃል የመጣ ሲሆን ትርጉሙም “ጭማሪ” ማለት ነው ፡፡ በግእዝ “ወሰከ – ጨመረ” ከሚለው የግእዝ ግስ የወጣ ተውሳክ (ተጨማሪ) ማለት ነው፡፡ ምዕራባዊያኑ ጳጉሜን የወር ተጨማሪ ቀን አድርገዋታል፡፡ እኛ ግን የዓመት ተጨማሪ ወር አድርገናታል፡፡ በኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ወርኃ ጳጕሜን የዓለም ፍጻሜ መታሰቢያ ተደርጋ ትታሰባለች፡፡ ይህም ጳጉሜ ከአሮጌው ዓመት ወደ አዲሱ ዓመት፣ ከክረምት ወቅት ወደ ጸደይ መሸጋገሪያ እንደሆነች ሁሉ ምጽአትም ከጊዜያዊው ወደ ዘላለማዊ፣ ከምድራዊ ወደ ሰማያዊ፣ ከዚህ ዓለም ወደ ወዲያኛው መሸጋገሪያ ነትና ነው፡፡ ጳጉሜ የክረምቱ ማብቂያ እንደሆነች ሁሉ ምጽአትም በመጨረሻው ዘመን መከራ የሚበዛበት የዚህ ዓለም ማብቂያ ናት፡፡ ወርኃ ጳጉሜ አዲሱን ዓመት ለመቀበል የዝግጅት ጊዜ እንደሆነች ሁሉ ምጽአትም ጻድቃል አዲሲቷን ምድር (መንግስ ሰማያትን) ለመውረስ ተዘጋጅተው “ኑ የአባቴ ብሩካን ዓለም ሳይፈጠር የተዘጋጀላችሁን መንግስት ውረሱ” የሚባሉባት ናት፡፡
በዚህም የተነሣ ብዙ ምእመናን በጾምና በጸሎት (በሱባዔ) ያሳልፏታል፡፡ በተለይም በቅዱስ ሩፋኤል ዕለት ሰማያት የሚከፈቱበት (ርኅዎተ ሰማይ) መኾኑን በማመን ምእመናን የጸሎታቸውን ማረጊያ (ማሳረጊያ) መሆኑን በማመን ከምንጊዜውም በበለጠ በእምነት ይጸልያሉ፡፡ ርኅወተ ሰማይ የስሙ ትርጉም የሰማይ መከፈት እንደማለት ሲሆን በክርስቶስ ክርስቲያን የተባሉ ሁሉ ፀሎት፣ ልመናቸው ምልጃቸው የሚያርግበት ዕለት ነው፡፡ ቅዱሳን መላእክት የምእመናንን ልመና መስዋእቱን የሚያሳርጉበት እና የአምላካችንን ምህረት ቸርነት ለሰው ልጆች የሚያወርዱበት ዕለት ነው፡፡ ከዚህም የተነሳ ውኆች እንደሚባረኩ በሚረዳ ጽኑ እምነት ምዕመናን ወደ ወንዞች በመሔድና በሚዘንበው ዝናብ ይጠመቃሉ፡፡
በቅድስት ቤተክርስቲያን ካሉት ሁለት የፈቃድ አጽዋማት መካከል አንዱ በዚህ በጳጉሜ ወር የምንጾመው ጾመ ዮዲት ነው፡፡ የዮዲት ጾም የሚባለውም እርሷ ስለ ጾመችው ነው፡፡ የፋርስ ንጉስ ናቡከደነጾር በሠራዊቱ ተመክቶ ጠላት አጥፋ ድንበር አስፋ ካመነው እጅ መንሻ እየተቀበልህ ያላመነውን እያሳመንህ ና ብሎ ለጦር አበጋዙ ለሆሎፎርኒስ ትዕዛዝ ሰጠ (ዮዲ ፪፡-፪)፡፡ እርሱም እንደታዘዘው በኃይላቸው የታመኑ ፲፪ ሺህ እግረኞችንና በፈረስ የተቀመጡ ፲፪ ሺህ ጦረኞችን እየመራ ዘምቶ ካመነው እጅ መንሻ እየተቀበለ ያላመነውን እያሳመነ ብዙ ሀገሮችን እያጠፋ ሲሔድ ከአይሁድ ከተማ ደረሰ በዚህም ብዙ ጥፋት በመድረሱ የእስራኤል ልጆች አለቀሱ፡፡
ዮዲት ባለቤቷ ምናሴ ሞቶባት ከወንድ ርቃ ንጽሕናዋን ጠብቃ በጾም በቀኖና በሀዘን ተወስና ትኖር ነበር:: በተፈጠረው ጥፋት ህዝቡ ላይ ለመጣው መከራ ማቅ ለብሳ በራስዋ ላይ ትብያ ነስንሳ ወደ እግዚአብሔር አለቀሰች፡፡ የፍጥረቱን ጥፋት የማይሻ እግዚአብሔር አምላክም ሕዝቡን የሚያድኑበትን መንገድ ለመጠየቅ ሱባኤ በገባች በሦስተኛው ቀን ገለጸላት (ዮዲ ፰፡፪)፡፡ ከዚህ በኋላ ጠላታቸውን በዮዲት ምክንያት እስራኤላውያን እስከ ዮርዳኖስ እየተከተሉ አጥፍተዋቸዋል፡፡ ዮዲት ጠላቷን ለማጥፋት የቻለችው በጾምና በጸሎት ከእግዚአብሔር አምላክ ኃይል አግኝታ ነው፡፡ ስለዚህ ምዕመናን ጥንተ ጠላታችን ሰይጣንንና ፈቃደ ሥጋን ለማሸነፍ በጾም ከፈጣሪያችን ኃይልን መጎናጸፍ አለብን ብለው ጳጉሜን በፈቃድ ይጾማሉ፡፡
በወርኀ ጳጉሜን ከሚታሰቡ እና ከሚከበሩ በዓላት መካከል በየዓመቱ ጳጕሜን ፫ ቀን የሚከበረው የሊቀ መላእክት የቅዱስ ሩፋኤል ዓመታዊ ክብረ በዓል በታላቅነቱ በልዩ ልዩ መንፈሳዊ ሥነ ሥርዓት ይከበራል፡፡ “ሩፋኤል” የሚለው የስሙ ትርጓሜ “ደስ የሚያሰኝ፣ ቸር፣ መሐሪ፣ ቅን የዋህ” ማለት ነው፡፡ በሌላም መልኩ ይህ የከበረ ታላቅ መልአክ ሰሙ የዕብራይስጥ ሁለት ቃላት ጥምረት ውጤት ነው፡፡ “ሩፋ” ማለት ጤና፣ ፈውስ፣ መድኃኒት ማለት ሲሆን “ኤል” ሚለው በሌሎቹም መላእክት ስም ላይ የሚቀጠል ስመ አምላክ ነው:: ይህም “መልአኬን በፊትህ እሰዳለሁ….. ስሜ በእርሱ ስለሆነ አታስመርሩት” (ዘጸ.23÷20-22) እንዳለው ነው፡፡ ታዲያ “ሩፋኤል” የሚለው በጥምረት “ከአምላክ ለሰዎች የተሰጠ ፈውስ” የሚለውን ይተካል፡፡ ቅዱስ ሩፋኤል ከሰባቱ ሊቃነ መላእክት አንዱ ሲሆን ስሙም ከሚካኤልና ከገብርኤል ቀጥሎ በሦስተኛ ደረጃ ይቀመጣል፡፡ “ከከበሩ ከሰባቱ አለቆች አንዱ አለቃ እኔ ሩፋኤል ነኝ” እንዲል (ጦቢት ፲፪፥፲፭)፡፡ ይህ መልአክ እንደሌሎቹ ሊቃነ መላእክት ሁሉ የሰው ልጆችን ይጠብቃቸዋል (ዳን.4÷13 ዘጸ. 23÷20 መዝ. 90÷11-13 ) ያማልዳል፣ ከፈጣሪ ያስታርቃቸዋል፡፡ (ሉቃ. 13፡6-9፣ ዘካ.1÷12) ሊቀ መላእክት ቅዱስ ሩፋኤል ያለ ማቋረጥ ፈጣሪያቸው ልዑል እግዚአብሔርን ከሚያመሰግኑ ቅዱሳን መላእክት አንዱ ነው፡፡ ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን ቅዱሳት መጻሕፍትን መሠረት አድርገው መልአኩ ቅዱስ ሩፋኤልን በሚከተሉት ሰባት አንኳር ነጥቦች ይገልጡታል፡፡
ፈዋሴ ዱያን፡ ሕሙማንን የሚፈውስ
ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዚህች ምድር ላይ እየተመላለሰ ሲያስተምር ድውያነ ሥጋን በተአምራት ድውያነ ነፍስን ደግሞ በትምህርቱ ይፈውስ ነበር፡፡ ለምሳሌ ለሠላሳ ስምንት ዘመን በአልጋ ላይ የነበረውን መጻጉዕን ተነስተህ አልጋህን ተሸክመህ ሄድ በማለት ከደዌው ፈውሶታል (ዮሐ ፭፡í-፲)፡፡ ማዳን (መድኃኒትነት) ለእርሱ የባህሪው ነው፡፡ የማዳንን ጸጋ ለቅዱሳን ሰጥቷል፡፡ ስለዚህም ነው ቅዱስ ጴጥሮስና ቅዱስ ጳውሎስ ድውያንን ሲፈውሱ የነበረው፡፡ ከቅዱሳን መላእክትም ቅዱስ ሩፋኤል የሰው ልጆች ከተያዙበት የኃጢአት ቍስል ይፈወሱ ዘንድ በአማላጅነቱና በጸሎቱ የሚረዳ መልአክ ነው፡፡ “በበሽታ ዅሉ ላይ በሰው ልጆችም ቍስል ላይ የተሾመው ቅዱስ ሩፋኤል ነው” በማለት ሄኖክ ከእግዚአብሔር መልአክ ያገኘውን የምስክርነት ቃል ጽፏል (ሄኖክ ፲፥፲፫)፡፡ ቅዱስ ሩፋኤል በሰውነታችን ላይ የሚወጣውን ደዌም ኾነ ቍስል ይፈውስ ዘንድ ከልዑል እግዚአብሔር ሥልጣን ተሰጥቶታል፡፡ “በሰው ቍስል ላይ የተሾመ ከከበሩ መላእክት አንዱ ቅዱስ ሩፋኤል ነው” እንዳለ ሄኖክ (ሄኖክ ፮፥፫)፡፡ ለቈሰሉ ፈውስን የሚያሰጣቸው መልአክ ነው፡፡ ዛሬም ሁላችንን በአማላጅነቱ ከደዌ ሥጋ ከደዌ ነፍስ ይፈውሰናል፣ ይጠብቀናልም፡፡
ፈታሔ ማኅፀን፡ ማኅፀንን የሚፈታ
በብሉያና በአዲስ ኪዳን ብዙ እናቶች ከመካንነት የተነሳ ሀዘን ጸንቶባቸው ቢቆይም ምንም የማይሳነው አምላክ እጅግ ድንቅን ያደረጉ የተባረኩ ልጆችን ሰጥቷቸዋል፡፡ ከእነዚህም ውስጥ የይስሐቅ እናት ሣራ፣ የያዕቆብ እናት ርብቃ፣ የዮሴፍ እናት ራሄል፣ የሶምሶን እናት እንትኩን፣ የነቢዩ ሳሙኤል እናት ሐና፣ የመጥምቀ መለኮት የዮሐንስ እናት ኤልሳቤጥ፣ የድንግል ማርያም እናት ሐና ይገኙበታል፡፡ እግዚአብሔር የመካኒቱን ማኅፀን ፈትቶ የተባረከ ልጅን የሚሰጥ አምላክ ነው፡፡ ይህንንም ጸጋ ለቅዱሳን መላእክት ሰጥቷል፡፡ ይህም ስልጣን ከተሰጣቸው ቅዱሳን መላእክት ቅዱስ ሩፋኤል አንዱ ነው፡፡

የወላድ ማኅፀን እንዲፈታ ስለተሾመ ከጌታ አዋላጅ ብትኖር ባትኖርም ሐኪም ሩፋኤል አይታጣም በምጥ ጊዜ ሲጨነቁ ሴቶች ሁሉ የመልአኩን መልክ አንግተው ማርያም ማርያም ይላሉ ማየጸሎቱን ጠጥተው ቶሎ ፈጥነው ይወልዳሉ፡፡ የይስሐቅን እናት ሣራን፣ የሶምሶንን እናት (እንትኩይን) ምክነታቸውን የቆረጠ ወልዶ ለመሳም ያበቃቸው ይኸው ፈታሔ ማኅጸን የልዑል እግዚአብሔር መልአክተኛ ቅዱስ ሩፋኤል ነው፡፡ ለነፍሰጡር ሴቶች ረዳታቸው ቅዱስ ሩፋኤል ነው፡፡ ሴት በፀነሰችበት ወቅት ቅዱስ ሩፋኤል አይለያትም፡፡ ሕፃኑ (ኗ) በማኅፀን እያለ (ች) ተሥዕሎተ መልክዕ (በሥላሴ አርአያ መልኩ /ኳ/ መሳል) ከጀመረበት ቀን አንሥቶ እስከሚወለድበት ቀን ድረስ ቅዱስ ሩፋኤል በጥበቃው አይለያቸውም፡፡ በመውለጃቸው ቀን ሴቶች ከሚደርስባቸው ጭንቀትና ሕመም ስሙን ጠርተው ይማጸኑታል፡፡ ፈታሔ ማኅፀን ነውና ቅዱስ ሩፋኤልም ጭንቀታቸውን ያቀልላቸዋል፡፡ ሕጻናትን በእናታቸው ማኅፀን የሚጠብቃቸው እናቶችንም ከመፅነስ እስከ መውለድ የሚራዳቸው፣ የመካኖችንንም ማኅፀን የመፍታት ጸጋ የተሰጠው መልአክ ነው፡፡
ሰዳዴ አጋንንት፡ አጋንንትን የሚያሳድድ
ከጌታችን ሠላሳ ሦስት ታላላቅ ተአምራት ውስጥ አራቱ አጋንንትን ማስወጣት ነበሩ፡፡ ይህ ስልጣን ለቅዱሳን ሰዎችና መላእክት በጸጋ ተሰጥቷቸዋል፡፡ ቅዱስ ሩፋኤልም በተሰጠው ስልጣን አጋንንትን የሚያሳድድ መልአክ ነው፡፡ አስማንድዮስ የተባለ ጋኔን በሣራ (ወለተ ራጉኤል) ላይ አድሮ ባሎቿን እየገደለ ቢያሰቃያት ቅዱስ ሩፋኤል ጋኔኑን አስጨንቆ አስወጥቶላታል (ጦቢት ፫፥፰-፲፯)፡፡ ቅዱስ ሩፋኤል “ዳግመኛም እግዚአብሔር ሩፋኤልን፣ አዛዝኤልን እጁን እግሩን አስረህ በጨለማ ውስጥ ጣለው አለው” ተብሎ እንደ ተጻፈ (ሄኖክ ፫፥፭-፯) ለቃየን ልጆች ሰይፍና ሾተል መሥራትን፣ የምንዝር ጌጥ ማጌጥን፣ መቀንደብን ያስተማረ አዛዝኤል የተባለውን ጋኔን በእሳት ሰይፍ እየቀጣ በረቂቅ አስሮ ወደ ጥልቁ የጣለው ይኸው መልአክ ቅዱስ ሩፋኤል ነው (ሄኖክ ፪፥፲፰)፡፡ ዛሬም ከእግዚአብሔር ተልኮ ለሰው ልጆች የተንኮልን፣ የጥላቻን፣ የመገዳደልን ሀሳብ እንዲያፈልቁ የሚያደርገውን የመልካም ነገር ጠላት የሆነውን ጠላታችንን አስጨንቆ የሚያባርር መልአክ ነው፡፡
አቃቤ ኆኅት፡ የምህረትን ደጅ የሚጠብቅ
ቅዱሳን መላእክት የሰውን ልጅን ጸሎት ከምድር ወደ ሰማይ የእግዚአብሔርን ምህረት ደግሞ ከሰማይ ወደ ምድር የሚያደርሱ መልእክተኛች ናቸው (ራዕ ፰፡፪)፡፡ ቅዱስ ሩፋኤልም ስለራሱ ማንነት በሰጠው ምስክርነት “የቅዱሳንን ጸሎት ከሚያሳርጉ ወደ ከበረ ወደ ገነነ ወደ እግዚአብሔር ጌትነትም ከሚያገቡ ከከበሩ ከሰባቱ አለቆች አንዱ አለቃ እኔ ሩፋኤል ነኝ አላቸው” (ጦቢት ፲፪፥፲፭)፡፡ ስለዚህም ቅዱስ ሩፋኤል መዝገበ ጸሎት እና አቃቤ ኆኅት ይባላል፡፡ ከዚህ ጋርም በቅዱስ ሩፋኤል ተራዳዒነት ከተደረጉ ተአምራት መካከል በእስክንድርያ አቅራቢያ በምትገኝ ደሴት በታነጸች ቤተ ክርስቲያኑ ያደረገው ተአምር አንደኛው ነው፡፡ በመጽሐፈ ስንክሳር እና በድርሳነ ሩፋኤል እንደ ተጻፈው በሊቀጳጳሳት ቴዎፍሎስ ዘመን አባቶች ለሊቀመናብርቱ ክብር በአሣ አንበሪ ጀርባ ላይ ያሳነጹትን መታሰቢያ ቤተ መቅደስ በወደቡ አጠገብ በእስክንድሪያ ነበረች፡፡
ብዙ ምእመናን በቤተ ክርስቲያን ውስጥ እያሉ ጠላት ዲያቢሎስ አነዋውጾ ለምስጋና የታደሙትን ምዕመናን ሊያጠፋ አሣ አንበሪውን ቢያውከው ቤተክርስቲያኒቱ ፈጽማ ተናወጠች፤ ያቺ ደሴት በታላቅ አንበሪ ጀርባ ላይ የቆመች ናትና፡፡ የሰዎች ብዛትም በከበደው ጊዜ ዓሣ አንበሪው ቤተ ክርስቲያኒቱን ያፈርሳት ዘንድ ሰይጣን አነሣሣው፡፡ ምእመናኑም ወደ ክብር ባለቤት እግዚአብሔር በከበረ መልአክ ሩፋኤል ስም ጮኹ፡፡ ያን ጊዜ ቅዱስ ሩፋኤል ያንን አንበሪ በበትረ መስቀሉ (ዘንጉ) ገሥጾ “እግዚአብሔር አዝዞሃልና ከቦታህ ሳትናወጥ ጸጥ ብለህ ቁም!” ባለው ጊዜ አንበሪው ጸጥ ብሎ ቆሟል፡፡ ምዕመናኑንም ከጥፋት ታድጓቸዋል፡፡
መራኄ ፍኖት፡ መንገድ መሪ
ጦቢት በፋርስ ንጉሥ በስልምናሶር ዘመን የተማረከ ከነገደ ንፍታሌም የተወለደ ጽኑዕ እሥራኤላዊ ነው፡፡ እግዚአብሔር በስልምናሶር ፊት የመወደድን ግርማና ባለሟልነትን ስለ ሰጠው አለቃ አድርጎ ሾሞት ነበር፡፡ ለወገኖቹ ምጽዋት በመስጠት ሕገ ርትዕን በመሥራት የተጋ ሰው ነበር፡፡ ሐና የምትባል ሚስት አግብቶ አንድ ልጅ ወልዷል፡፡ ስልምናሶር ሞቶ ሰናክሬም በነገሠ ጊዜ ከሹመቱ ስለሻረው ደግሞ ወደ ምድያም መሔድ አልቻለም፡፡
ሣራ ወለተ ራጉኤል ከፍተኛ ችግር ደርሶባት ነበር፡፡ ችግሯም ሕፃናት ወልጄ ቤት ንብረት ይዤ እኖራለሁ በማለት ባል አገባች ነገር ግን በዚች ሴት አስማንድዮስ የሚባል ጋኔን አድሮ ያገባችውን ሰው ገደለባት ሌላም ባል ብታገባ ሞተባት እንደዚህ እየሆነ በጠቅላላ ሰባት ድረስ ያሉትን ባሎችን ገደለባት፡፡ የራጉኤል ልጅ ሣራ በዚህ ሁኔታ በኀዘን ተውጣ ስትኖር በነበረበት ጊዜ ጦቢት ሸምግሎ ስለ ነበር ልጁ ጦብያን ጠርቶ በዚህ ዓለም እስካለ ድረስ ሊሠራው የሚገባውን መንፈሳዊ ሥራ እንዲሠራ በጥብቅ ከመከረው በኋላ በመጨረሻ ልጄ እኔ ሳልሞት የኑሮ ጓደኛህን ፈልግ፣ ስትፈልግም ዕወቅበት፣ እኛ የአብርሃም የይስሐቅና የያዕቆብ ዘሮች ነን ስለዚህ ከእነርሱ ወገን የሆነችውን እንድታገባ ከዚህም ሌላ ከገባኤል ዘንድ በአደራ ያስቀመጥኩት ገንዘብ አለና እኔ በሕይወት እያለሁ ብታመጣው የተሻለ ነው አለው፡፡
“በመንገድ ይጠብቅህ ዘንድ ወዳዘጋጀሁትም ስፍራ ያገባህ ዘንድ፥ እነሆ፥ እኔ መልአክን በፊትህ እሰድዳለሁ (ዘጸ ፳፫፡፳)።” ተብሎ ለመላእክት ሰውን መንገድ የመምራትና የመጠበቅ ስልጣን እንደተሰጣቸው የጦቢትን ልጅ ጦቢያን ከነነዌ የሜዶን ክፍል ወደ ምትሆነውና ራጌስ ወደምትባለው ሀገር ሲሄድ አዛርያስ (ቅዱስ ሩፋኤል) በመንገድ ይመራው ነበር፡፡ በዚህም ቅዱስ ሩፋኤል “መራኄ ፍኖት” (መንገድ መሪ) ይባላል፡፡ ጦቢያና አዛርያስ ሲሄዱ ውለው ማታ ጤግሮስ ከተባለው ታላቅ ወንዝ ደረሱና ከዚያም ለማደር ወሰኑ፡፡ በዚህ ጊዜ ከድካሙ ጽናት የተነሣ ጦብያ ሊታጠብ ወደ ወንዙ ወረደና ልብሱን አውልቆ መታጠብ ሲጀምር አንድ ዓሣ ሊውጠው ከባሕር ወጣ፡፡ ወዲያውም መልአኩ ቅዱስ ሩፋኤል ጦብያን ያዘው፤ ዓሣውን እንዳትለቀው አለው፤ ጦቢያም ከዓሳው ጋር ግብ ግብ ገጥሞ እየጐተተ ወደ የብስ አወጣው፡፡ ከዚህ በኋላ ቅዱስ ሩፋኤል ጦብያን እንዲህ ሲል አዘዘው፡፡ ዓሣውን እረደው ጉበቱንና ሐሞቱን ተጠንቅቀህ ያዘው ሌላውን ግን ጠብሰን እንበላዋለን አለው፡፡ ዛሬም በመንገዳችን እንዲመራን በጉዞአችንም ፈተና ሲገጥመን እንዲራዳን መልአኩ ቅዱስ ሩፋኤልን ሊልክልን አምላካችን የታመነ ነው፡፡
መልአከ ከብካብ: ጋብቻን የሚባርክ መልአክ የራጉኤል ልጅ ሣራ ሰባት ሰዎች አግብተዋት ሰባቱም ባገቧት ሌሊት ደርቀው /ሞተው/ አድረዋል፡፡ ይህንንም ከነነዌ ወደ ራጌስ የመጣው የጦቢት ልጅ ጦቢያ ያውቅ ነበር፡፡ ለአዛርያስም “ስለዚህ እኔ ላባቴና ለእናቴ አንድ ልጅ ነኝ እርስዋን አግብቼ ከዚህ በፊት እንዳገቧት ሰዎች እኔም የሞትኩ እንደሆነ አባቴንና እናቴን የሚረዳቸው የለም ቢሞቱም የሚቀብራቸው አያገኙምና እፈራለሁ” አለው፡፡ መልአኩ ቅዱስ ሩፋኤል ግን ‹አባትህ ከዘመዶችህ ወገን ካልሆኑ በስተቀር ሌላ ሴት እንዳታገባ ሲል የነገረህን ረሳኸውን? በል ሰባት ባሎቿ ሙተውባታል ስለምትለው እኔ መድኃኒቱን አሳይሃለሁ ፤ አይዞህ አትፍራ አትሞትም የዓሣውን ሐሞትና ጉበቱን ለምን ያዘው ያልኩህ ለምን ይመስልሃል? እንግዲህ ሐሞቱንና ጉበቱን ከዕጣን ጋር ጨምረህ ስታጤስበት በሣራ አድሮ የነበረው አስማንድዮስ የተባለው ጋኔን ወጥቶ ይሄዳል ፈጽሞም ወደ እርሷ በገባህም ጊዜ ሁለታችሁ ይቅር ባይ ወደ ሆነው እግዚአብሔር ጸልዩ እርሷም የተዘጋጀች ናት፡፡ ከእኛ ጋርም ወደ ሀገርህ ይዘናት እንሄዳለን› አለው፡፡ ጦብያም ይህንን ቃል በሰማ ጊዜ ደስ አለውና ከእርሷ በስተቀር ሌላ እንዳያገባ በሙሉ አሳቡ ወሰነ፡፡
ከዚህ በኋላ ወደ ራጉኤል ቤት እንደ ደረሱ ሣራ በደስታ ተቀበለቻቸው የሣራ አባትም ጦብያን ገና እንዳየው ሚስቱ አድናን “ይህ ልጅ የእኔ ዘመድ ጦቢትን ይመስላል” አላት ከዚያም ጋር አያይዞ “ልጆች ከየት ሀገር መጣችሁ?” አላቸው፡፡ እነሱም “ከነነዌ ሀገር ነው የመጣን” አሉት፡፡ “ከዚያም ሀገር ጦቢት የሚባል ወንድም ነበረኝ ታውቁት ይሆን?” ሲል ጠየቃቸው፡፡ በዚህ ጊዜ ጦቢያ አባቱን ሲጠራለት “እናውቀዋለን፡፡ እኔም ራሴ የጦቢት ልጅ ነኝ” አለው፡፡ ከዚያ በኋላ ራጉኤል “የወንድሜ ልጅ ነህን?” ብሎ እቅፍ አድርጐ ሳመው፡፡ አድናም ሳመችውና ሁሉም ተያይዘው የናፍቆት ልቅሶ ተላቀሱ፡፡ ከወንድሙ እንደ መጡም ሲገነዘብ በግ አርዶ በጥሩ ሁኔታ ጋበዛቸው፡፡
እራትም ከበሉ በኋላ ጦብያ ቅዱስ ሩፋኤል በመንገድ የነገረውን በልቡ ሲያወጣ ሲያወርድ ስለ ዋለ ቅዱስ ሩፋኤልን ያንን በመንገድ የነገርከኝን አሁን ፈጽምልኝ ሲለው ሰምቶ ስለ ልጅቷ መሆኑን ስለ ገባው ራጉኤል ጦብያን ‹ልጄ ይህች ልጅ ላንተ የምትገባ ናት ሰጥቸሃለሁ አይዞህ አትጠራጠር አሁንም ብላ ጠጣ ለዛሬም ደስ ይበልህ አለውና ሣራ ካለችበት የጫጉላ ቤት አግብተው ዘጉት፡፡ ጦብያም ሣራን በይ እኅቴ ኑሮዋችን እንዲቃናልንና ጋብቻችን እንዲባረክልን አስቀድመን ወደ ፈጣሪያችን ጸሎት እናድርግ› አላትና አብረው ጸሎት ካደረጉ በኋላ ያንን የያዘውንና የዓሣ ጉበትና ሐሞት ከዕጣን ጋር ጨምሮ ቢያጤስበት በሣራ አድሮ ባሎችዋን ይገድልባት የነበረው አስማንድዮስ የተባለው ጋኔን ከሣራ ለቆ ወጥቶ ሄደ ሁለተኛም ሊመለስ አልቻለም፡፡ እነርሱም በሰላምና በጤና አደሩ፡፡
ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በቃና ዘገሊላ ከእናቱ ከቅድስት ድንግል ማርያምና ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ተገኝቶ በዶኪማስ ቤት የነበረውን ሠርግ ባርኮታል፡፡ የወይን ጠጅ ቢያልቅባቸውም ውኃውን ወደ ወይን ጠጅ ለውጦ ቤቱን በበረከት ሞልቶታል (ዮሐ ፪፡í)፡፡ ቅዱሳንም ከእግዚአብሔር በተሰጣቸው ጸጋ ጋብቻን በጸሎታቸው ይባርካሉ፡፡ በመሆኑም የጦብያንና የሣራን ጋብቻ የባረከ ቅዱስ ሩፋኤል ስለሆነ “መልአከ ከብካብ” ይባላል፡፡ ዛሬም በምልጃው ላመኑት ጋብቻን ይባርካል፣ ትዳርንም ያጸናል፡፡
ከሳቴ እውራን፡ ዓይነ ስውራንን የሚያበራ
ራጉኤልና ሐና የሣራንና የጦቢያን የጤንነታቸውን ነገር ሲረዱ የሰርጉ ቀን የሚሆን የአሥራ አራት ቀን በዓል እስኪፈጸም ድረስ ጦብያ ወደ ሀገሬ እሄዳለሁ ብሎ እንዳያውከው በማለት አማለው፡፡ የአሥራ አራት ቀን በዓለ መርዓ ከተፈጸመ በኋላ ግን ጥሬ ገንዘብና የከብት ስጦታ አድርጐ መርቆ ወደ ሀገሩ ሰደደው፡፡ ወላጆቹ ጦቢትና አድና ግን በመዘግየቱ ልጃችን ምን አግኝቶት ይሆን? እያሉ ለጊዜው ሳያዝኑ አልቀሩም፡፡ ከጥቂት ቀናት በኋላ ሚስቱንና ግመሎቹን ይዞ ሲመጣ በክብርና በደስታ ተቀበሉት፡፡ የጦብያ አባት ጦቢትም ልጅህ መጣ ሲሉት ዓይነ ሥውር ስለ ነበር እርሱን እቀበላለሁ ሲል ስለ ወደቀ ወዲያው ጦብያ የዓሣውን ሐሞትና ጉበቱን ይዞ ስለ ነበር የአባቱን ዓይን ቀባው ወዲያውም ዓይኖቹ ተከፈቱ፡፡ በምራቁ አፈር ለውሶ በደረቅ ግንባር ላይ ዓይንን የሚሠራው እግዚአብሔር (ዮሐ ፰) በመልአኩ ቅዱስ ሩፋኤል አማካኝነት የጦቢያን አባት የጦቢትን ዓይን በራለት፡፡ ቅዱስ ሩፋኤል ዛሬም በምልጃው ለሚያምኑት ሥጋዊ ዓይንና መንፈሳዊ ዓይንን (ዓይነ ልቡናን) የሚያበራ መልአክ ነው፡፡
ማጠቃለያ
በኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያን የበዓላት ቀኖና መሰረት ወርኃ ጳጉሜ የዕለተ ምጽአት መታሰቢያ ተደርጋ ትታሰባለች፡፡ በወርኃ ጳጉሜ የአሮጌውን ዘመን የኃጢአት ቆሻሻ በንስሃ አጥበን ከዕለተ ምጽዓት በኋላ ለምትገለጠው የእግዚአብሔር መንግስት ምሳሌ ለሆነ አዲስ የምህረት ዓመት እንዘጋጅባታለን፡፡ የታደሉትም በፈቃድ ጾምና በሱባኤ እንደሚያሳልፏት ይታወቃል፡፡ በወርኃ ጳጉሜ በገናንነት የሚከበረው የሊቀ መላእክት የቅዱስ ሩፋኤል በዓል የአሮጌው ዘመን በዓላት መዝጊያ ለአዲሱ ዘመን ርዕሰ አውደ ዓመት ለቅዱስ ዮሐንስ በዓልም መሸጋገሪያ ነው፡፡ ስለሆነም ኢትዮጵያውያን ክርስቲያኖች የሊቀ መልአኩን የቅዱስ ሩፋኤልን በዓል በማሰብ በወርኃ ጳጉሜ ውኆች እንደሚባረኩ በእምነት በመረዳት “ሩፋኤል አሳድገን (እርዳን፣ ጠብቀን)” እያልን በሃይማኖት እንጠራዋለን፡፡ ቅዱስ ሩፋኤል ከሰባቱ ሊቃነ መላእክት አንዱ ሲሆን በመጽሐፈ ጦቢት፣ በመጽሐፈ ሄኖክ፣ ቅዱስ ኤጲፋንዮስ በጻፈው አክሲማሮስ በተባለው መጽሐፍና በድርሳኑ ላይ እንደተገለጠው ከእግዚአብሔር በተሰጠው ጸጋ ድውያነ ሥጋንና ድውያነ ነፍስን የሚፈውስ፣ የሚካኒቱን ማኅፀን የሚያለመልም፣ ሕጻናትንም በእናታቸው ማኅፀን ሳሉ የሚጠብቃቸው፣ የክፋት አባት የሆነውን ጠላት ሰይጣንን የሚያሳድድ፣ በመንገድ ያሉትን የሚመራ፣ ምህረትን ለሚሹ ፈጥኖ የሚደርስ፣ በጋብቻና በትዳር የሚፈተኑትን የሚረዳ መልአክ ነው፡፡ የሊቀ መልአኩ የቅዱስ ሩፋኤል ጸሎትና አማላጅነት ልጅ በማጣት ለተጨነቁ መልካም ፍሬን፣ ለተወለዱት በሃይማኖት ማደግን፣ ለታመሙት ፈውስን፣ ለባለትዳሮች እግዚአብሔር የሚደሰትበት ትዳርን እንዲሰጥልን የሰራዊት ጌታ የአምላካችን እግዚአብሔር ቅዱስ ፈቃዱ ይሁንልን፡፡ አሜን ሩፋኤል አሳድገን፡፡

ጳጕሜን«ጳጉሜ» ማለት ጭማሪ ማለት ነው፡፡ ይህም በዓመቱ መጨረሻ ላይ አምስት ወይም ስድስት ቀን በመሆን የምትመጣ ናት፡፡ ጳጕሜን በአራት ዓመት አንዴ ማለትም በዘመነ ሉቃስ መጨረሻ በዘመነ ዮ...
06/09/2025

ጳጕሜን

«ጳጉሜ» ማለት ጭማሪ ማለት ነው፡፡ ይህም በዓመቱ መጨረሻ ላይ አምስት ወይም ስድስት ቀን በመሆን የምትመጣ ናት፡፡ ጳጕሜን በአራት ዓመት አንዴ ማለትም በዘመነ ሉቃስ መጨረሻ በዘመነ ዮሐንስ ቅበላ ስድስት ቀን ትሆናለች። በዚህም ሃገራችን ኢትዮጵያ የአስራ ሦስት ወራት ጸጋ (Thirty months of sunshine) በመባል ትታወቃች፡፡

ጳጉሜ በዘመነ ዮሐንስ ስድስት በምትሆንበት ጊዜ ጾመ ነቢያት (የገና ጾም) ህዳር ፲፬ ቀን ይገባና ታህሳስ ፳፰ ቀን ጾሙ ተፈትቶ የልደት በዓል ይከበራል፡፡

በቅድስት ቤተክርስቲያን ካሉት ሁለት የፈቃድ አጽዋማት መካከል አንዱ በዚህ በጳጉሜ ወር የምንጾመው የፈቃድ ጾም ነው፡፡ ይህም «ጾመ ዮዲት» በመባል ይታወቃል፡፡ ይህ ግን እንደ አንደኛው የፈቃድ ጾም (የጽጌ ጾም) በብዙዋኑ ዘንድ የታወቀ አይደለም፡፡ የዮዲት ጾም የሚባለውም እርሷ ስለ ጾመችው ነው፡፡ እዚህ ላይ ዮዲት ተብላ የተጠቀሰችው በቤተክርስቲያን ታሪክ ትምህርት ላይ በጥፋት ሥራዋ በተደጋጋሚ የምትጠቀሰው ዮዲት ጉዲት አይደለችም፡፡

ወደ ታሪኩ ስንመለስ የፋርስ ንጉስ ናቡከደነጾር በሠራዊቱ ተመክቶ ሹም ጠላት አጥፋ ድንበር አስፋ ካመነው እጅ መንሻ እየተቀበልህ ያላመነውን እያሳመንህ ና ብሎ ለጦር አበጋዙ ለሆሎፎርኒስ ትዕዛዝ ሰጠ፡፡ መጽሐፈ ዮዲት ፪፥፪-፯፡፡ እርሱም እንደታዘዘው በኃይላቸው የታመኑ ፲፪ሺህ እግረኞችንና በፈረስ የተቀመጡ ፲፪ሺህ ጦረኞችን እየመራ ዘምቶ ካመነው እጅ መንሻ እየተቀበለ ያላመነውን እያሳመነ ብዙ ሀገሮችን እያጠፋ ሲሔድ ከአይሁድ ከተማ ደረሰ በዚህም ብዙ ጥፋ በመድረሱ የእስራኤል ልጆች አለቀሱ፡፡

ዮዲት ባሏ ሞቶባት ከወንድ ርቃ ንጽሕናዋን ጠብቃ በጾም በቀኖና በሀዘን ተወስና ትኖራለች በተፈጠረው ጥፋት ህዝቡ ላይ ለመጣው መከራ ማቅ ለብሳ በራስዋ ላይ ትብያ ነስንሳ ወደ እግዚአብሔር አለቀሰች፡፡ የፍጥረቱን ጥፋት የማይሻ እግዚአብሔር አምላክም ሕዝቡን የሚያድኑበትን መንገድ ለመጠየቅ ሱባኤ በገባች በሦስተኛው ቀን ገለጸላት፡፡ ዮዲ ፰፥፪ ፡፡ ከዚህ በኋላ ጠላታቸውን በዮዲት ምክንያት እስራኤላውያን እስከ ዮርዳኖስ እየተከተሉ አጥፍተዋቸዋል፡፡

ዮዲት ጠላቷን ለማጥፋት የቻለችው በጾምና በጸሎት ከእግዚአብሔር አምላክ ኃይል አግኝታ ነው፡፡ ስለዚህ ምዕመናን ጥንተ ጠላታችን ሰይጣንን ፈቃደ ሥጋን ለማሸነፍ በጾም ከፈጣሪያችን ኃይልን መጎናጸፍ አለብን ብለን ጳጉሜን በፈቃድ እንጾማለን፡፡

በተጨማሪም የጳጉሜ ወር ዕለተ ምጽአት የሚታሰብበትም ወር ነው፡፡ ይህም ጳጉሜ የዓመታት መሸጋገሪያ ጨለማው የክረምት ወቅት ወደ ማብቂያው የምናልፍባት እንደሆነች ሁሉ ምጽአትም ከጊዜያዊው ወደ ዘለዓለማዊ ከምድራዊ ወደ ሰማያዊ ከዚህ ዓለም ወደ ወዲያኛው መሸጋገሪያችን ነውና።

ክርስቲያኖች ሁሉ በየዓመቱ በጳጉሜ ወር ሁሉም ተሰብስበው ከሌሊት ጀምረው በቤተክርስቲያን ተገኝተው ጸበል ይጠመቃሉ፡፡ ይህንን የምናደገውም እግዚአብሔር የተባረከ ዓመት እንዲሰጠን፣ ባሳለፍነው ዓመት የሰራነውን ኃጢአት ይቅር እንዲለን ነው፡፡ የምንጠመቀውም ንስሐ ገብተን ነው፡፡ በእግዚአብሔር ስም የተቀደሰው ጸበል ደግሞ ከበሽታችን ያድነናል፣ የተቀደስንም ያደርገናል፣ መጪውንም ህይወታችን የተባረከ ያደርግልናል፡፡

በነገራችን ላይ ጳጉሜን ፭ ቀን በቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት ዘንድ «ዕለተ ምሪያ» ወይም የተመረጠች ቀን ትባላለች፡፡ የጌታችን ልደት ለመጠበቅ ሊቃውንቱ ሲያሰሉባት የቆየችው ዕለት በመሆኗ ነው ይህንን ስያሜ ያገኘችው፡፡ የጌታችንን ልደት ቀን የምትወስነው ጳጉሜ ፭ ቀን ናት፡፡ ልደት የሚውለው ጳጉሜ ፭ በዋለበት ቀን ነው፡፡ ለምሳሌ ዘንድሮ ጳጉሜን ፭ ቀን ረቡዕ ነው የምትውለው፤ ስለዚህም በ፳፻፲፱ ዓም ልደት የሚውለው ረቡዕ ነው፡፡ በየአራት ዓመቱ አንድ ጊዜ ጳጉሜን ፮ ስትሆን ልደት በ፳፷ የሚከበረው ዕለተ ምሪያን ስለማይለቅ ነው፡፡ ስድስተኛዋ ቀን ልደትን በአንድ ቀን ስታዘልለው እኛ በ፳፰ እናከብረዋለን፡፡ ልደት ጳጉሜ ፭ ቀንን(ዕለተ ምሪያን) ስለማይለቅ፡፡ ታድያ ምነው እነ ጥምቀትና ግዝረት አይለወጡም? ቢሉ፡፡ ሊቃውንቱ የሚሰጡት መልስ ❝ትውልድ ሱባኤ እየቆጠረ በተስፋ የጠበቃት ዕለተ ልደትን ስለሆነ ነው፤ ሌሎቹ የመጡት በልደቱ ምክንያት ነው❞ የሚል ነው፡፡

መልካም የአዲስ ዓመት ዋዜማ (ዻጉሜ) ይሁንላችሁ/ይሁንልን።

https://youtu.be/59M3aMheYfY?si=6Ckrlbiz23PxrrrJ
27/08/2025

https://youtu.be/59M3aMheYfY?si=6Ckrlbiz23PxrrrJ

ዓውደ ጥበባት ሚዲያ ትኩረቱን በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ ትምህርቶችና ጉዳዮች ላይ ትኩረት አድርጎ በጥበብ ቃለ ወንጌልን ለማዳረስ ለጥያቄዎችዎ ምላሽ በቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት ለማሰጠት ያልታዩና...

https://youtu.be/vQVdFIxUxJk?si=Thw2q3oJ4cktdGSG
21/08/2025

https://youtu.be/vQVdFIxUxJk?si=Thw2q3oJ4cktdGSG

ዓውደ ጥበባት ሚዲያ ትኩረቱን በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ ትምህርቶችና ጉዳዮች ላይ ትኩረት አድርጎ በጥበብ ቃለ ወንጌልን ለማዳረስ ለጥያቄዎችዎ ምላሽ በቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት ለማሰጠት ያልታዩና...

ጽንሰታ ለማርያምነሐሴ ፯ ቀን እግዚአብሔር የመላእክት አለቃ ቅዱስ ገብርኤልን ወደ ከበረና ከፍ ከፍ ወዳለ ጻድቅ ኢያቄም ላከው፡፡ አምላክን የወለደች የእመቤታችን የድንግል ማርያምን ፅንሰቷንና...
13/08/2025

ጽንሰታ ለማርያም

ነሐሴ ፯ ቀን እግዚአብሔር የመላእክት አለቃ ቅዱስ ገብርኤልን ወደ ከበረና ከፍ ከፍ ወዳለ ጻድቅ ኢያቄም ላከው፡፡ አምላክን የወለደች የእመቤታችን የድንግል ማርያምን ፅንሰቷንና ልደቷን በእርሱም ለዓለሙ ሁሉ ድኅነትና ተድላ ደስታ እንደሚሆን ነገረው፡፡

ይህ ጻድቅ ሰው ኢያቄምና የከበረች ሚስቱ ሐና ልጅ ሳይወልዱ ሸመገሉ፡፡ የከበረች ሐና መካን ሁናለችና ስለዚህም እጅግ ያዝኑ ነበር፤ የእስራኤል ልጆች ልጅ ያልወለደውን ከእግዚአብሔር በረከትን ያጣ ነው እያሉ ያቀልሉት ነበርና፡፡ እነርሱም ልጅ ይሰጣቸው ዘንድ ወደ እግዚአብሔር ዘወትር ፈጽሞ ይለምኑ ነበር፡፡ ከዚህም በኋላ ወንድ ልጅን ወይም ሴት ልጅን ቢወልዱ ለእግዚአብሔር ቤት አገልጋይ ሊያደርጉት ስዕለትን ተሳሉ፡፡ የልቡናቸውን መሻት የሆነውን ልጅ እንዲሰጣቸው እግዚአብሔርን ዘወትር በቤተ መቅደስ ተገኝተው ዕንባቸውን እያፈሰሱ መማጸናቸውን አላቋረጡም፡፡

ከዕለታት በአንድ ቀንም የከበረ ኢያቄምም በተራራ ላይ ሳለ ሲጸልይና ሲማልድ እነሆ እንቅልፍ እንቅልፍ ብሎት ተኛ፡፡ ያን ጊዜ የመላእክት አለቃ ቅዱስ ገብርኤል ተገለጸለት፡፡ እንዲህም አለው፡- “ሚስትህ ሐና ትፀንሳለች ዓለም ሁሉ ደስ የሚሰኝባትን የብዙዎችም ዐይነ ልቡናቸው በእርሷ የሚበራላቸውን በእርሷም ድኅነት የሚሆንባትን ሴት ልጅን ትወልድልሃለች” አለው፡፡

ሐናም በበኩሏ “አቤቱ ጌታዬ የአባቶቼ የእስራኤል አምላክ እኔ ባርያህ እለምንሃለሁ፤ ስማኝ ለዓይኔ ማረፊያ ለልቤ ተስፋ የምትሆነኝ የተባረከች ሴት ልጅ የማኅፀኔን ፍሬ ስጠኝ” ብላ ስትለምን ዋለች፡፡ ርግብ ከልጆቿ ጋር ስትጫወት ዓይታም በተሰበረ ልብ ውስጥ ሆና “አቤቱ ጌታዬ ለዚች ግእዛን ለሌላት እንስሳ ልጅ የሰጠህ አምላክ ምነው ለኔ ልጅ ነሳኸኝ?” ብላ ምርር ብላ አለቀሰች፡፡

ሐና እና ኢያቄም ከካህኑ ዘካርያስ ዘንድ ሄደው “አቤቱ ጌታችን ሆይ ወንድ ልጅ ብንወልድ ተምሮ ቤተ እግዚአብሔርን አገልግሎ እንዲኖር እንሰጣለን፤ ሴት ልጅም ብንወልድ ማይ(ውኃ) ቀድታ፣ መሶበ ወርቅ ሰፍታ፣ መጋረጃ ፈትላ፣ ካህናትን አገልግላ እንድትኖር እንሰጣለን” ብለው ስዕለት ገቡ፡፡ ካህኑ ዘካርያስም “እግዚአብሔር ጸሎታችሁን ይስማችሁ፤ ስዕለታችሁን ይቀበልላችሁ፤ የልቡናችሁን መሻት ይፈጽምላችሁ” ብሎ ቡራኬ ሰጥቶ ሸኛቸው።

ሐና እና ኢያቄም ዕለቱን ራእይ ዓይተው አደሩ፡፡ ራእዩም እንዴት ነው ቢሉ፡- ኢያቄም ፯ቱ ሰማያት እንደ መጋረጃ ተገልጠው ከላይኛው ሰማይ ነጭ ርግብ ወርዳ በሐና ራስ ላይ ስታርፍ፤ በጆሮዋም ገብታ በማኅፀኗ ስትተኛ አየ፡፡ ሐናም የኢያቄም መቋሚያ ለምልማ አፍርታ ፍጥረት ሁሉ ሲመገባት አየች፡፡ ከዚህም በኋላ ኢያቄም ያየውን ራእይ ለሐና፣ ሐና ያየችውን ራእይ ደግሞ ለኢያቄም በመንገር ራሳቸውን እግዚአብሔር ለገለጸላቸው ነገር ለማዘጋጀት ተስማሙ፡፡

ሁለቱም በአንድ ልብ ሆነው ዕለቱን በሩካቤ ሥጋ አልተገናኙም፤ ፈቃደ እግዚአብሔር ቢሆን ነው ብለው “አዳምንና ሔዋንን ብዙ ተባዙ ምድርንም ምሉአት ብሎ ያበሰረ አምላክ ለኛስ ይልክልን የለምን?” ብለው ዕለቱን መኝታ ለይተው እስከ ፯ ቀን ድረስ ሰነበቱ፡፡ ነሐሴ በባተ በሰባተኛው ቀን መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ከእግዚአብሔር ተልኮ “ከሰው የበለጠች፤ ከመላእክት የከበረች ደግ ፍጥረት ትወልዳላችሁ” ብሎ ለሐና ነገራት፡፡

በፈቃደ እግዚአብሔር፣ በብሥራተ መልአክ እመቤታችን እግዝእትነ ማርያም ነሐሴ ፯ ቀን ተፀነሰች፡:

ቅዱስ ያሬድ “ማርያምሰ ተኀቱ እምትካት ውስተ ከርሱ ለአዳም ከመ ባሕርይ ጸዓዳ፤ ማርያምስ ከጥንት ጀምሮ በአዳም ባሕርይ ውስጥ እንደ ነጭ ዕንቁ ታበራለች” በማለት እንደተናገረው እግዚአብሔር ቅድስት ድንግል ማርያምን ለአዳምና ለልጆቹ ሁሉ ድኅነት መሠረት እንዳደረጋት፣ ሊመረመር በማይችል ጥበቡም እንዳዘጋጃት ተናግሯል፡፡ አባ ሕርያቆስም በቅዳሴ ማርያም ድርሰቱ “ኦ ድንግል አኮ በፍትወተ ደነስ ዘተፀነስኪ አላ በሩካቤ ዘበሕግ እምሐና ወኢያቄም ተወለድኪ፤ ድንግል ሆይ በኃጢአት ፍትወት የተፀነስሽ አይደለም፤ በሕግ በሆነ ሩካቤ ከሐና ከኢያቄም ተወለድሽ እንጂ” ብሎ አመስግኗታል፡፡

ቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንም ይህንን መሠረት አድርጋ ዕለቱን በድምቀት ታከብረዋለች፡፡

የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ምልጃዋ በረከቷ በሁላችን ላይ ይደር፡፡ አሜን፡፡

ምንጭ፡- ስንክሳር ነሐሴ ፯ ቀን

Address

አዲስ አበባ
Dire Dawa
ZIPCODE

Alerts

Be the first to know and let us send you an email when ዓውደ ጥበባት ሚዲያ - Awede Tibebat Media posts news and promotions. Your email address will not be used for any other purpose, and you can unsubscribe at any time.

Shortcuts

Share