16/05/2022
መንፈሳዊ መነቃቃት (Revival)
እንዴት ይመጣል???
ለመንፈሳዊ መነቃቃት ወይም ለመለኮታዊ ጉብኝት መሟላት የሚገባቸው ቅድመ ሁኔታዎች እንዳሉ ይታወቃል።
ልዩ የሆነ መንፈሳዊ ጉብኝት ወይም ሪቫይቫል በግለሰብ ደረጃ በቤተክርስቲያን እና በሀገር ደረጃ እንዲሆን የሰው ድርሻ ወሳኝ ነው።
ከሰው የሚጠበቀው መንፈሳዊ ርሃብ: ጥማትና ምጥ(እርግዝና) ነው
ኢሳይያስ 44:3
" በተጠማ ላይ ውኃን በደረቅም መሬት ላይ ፈሳሾችን አፈስሳለሁና፤ መንፈሴን በዘርህ ላይ በረከቴንም በልጆችህ ላይ አፈስሳለሁ፥"
በተጠማ ላይ እርካታን የሚሰጥ እግዚአብሔር ሲሆን መሻቱና ጥማቱ ግን የሰው ድርሻ ነው።
ዮሐንስ 7: 37
" .. ማንም የተጠማ ቢኖር ወደ እኔ ይምጣና ይጠጣ። በእኔ የሚያምን መጽሐፍ እንዳለ፥ የሕይወት ውኃ ወንዝ ከሆዱ ይፈልቃል።"
ስለዚህ ሀገርችንን ትውልዳችንን ሊታደግ የሚችል መለኮታዊ ጉብኝት እንዲሆን በብርቱ ርሃብና ጥማት የአምላካችንን ፊት አብዝተን እንፈልግ
*ሉቃስ 11:10, 13
" የሚለምን ሁሉ ይቀበላልና፥ የሚፈልግም ያገኛል፥ መዝጊያውንም ለሚያንኳኳው ይከፈትለታል። .... በሰማይ ያለው አባት ለሚለምኑት እንዴት አብልጦ መንፈስ ቅዱስን ይሰጣቸው?
ሪቫይቫል እንዲመጣ ከላይ ያየናቸው የመጽሐፍ ቅዱስ ሃሳቦች በቅድሚያ መሆን ይገባዋል እነዚህ ምጥ:ርሃብና ጥማት በሌለበት ሁኔታ ጉብኝት ሊሆን አይችልም።
በ20ኛው ክ/ዘመን በታላቋ ብሪታኒያ (ስኮትላንድ) የተከሰተው መነቃቃት ህዝብን እንደ ሞገድ ወደ ቤ/ክ እንዲተምም ያደረገው ምክንያት ጆን ኖክስ የተባለ ሰው በነፍሱ ተወራርዶ እንዲህ በማለት ወደ አምላኩ ጸለዬ " ስኮትላድን ስጠኝ አለበለዚያ ግደለኝ" አለ። በተጨማሪም ሚስቱን ወይ እግዚአብሔር ይመጣልኛል አለዚያም እሬሳዬ ይወጣል " በማለት በመጾም ከእንጀራ ጋርና ከእንቅልፍ ጋር ተጣልቶ አብዝቶ በመጮኽ ስኮትላንድን ለክርስቶስ አስወረሳት።
በ1904 በዌልስ ምድር የተከሰተው ሪቫይቫል በአንድ የድሃ ቤተሰብ ከተገኘ ብዙ የትምህርት ዝግጅት በሌለው ኢቫን ሮበርትስ ምጥና ርሃብ የተነሳ ነው። አውሮፓን ያጥለቀለቀው እስከ 20 ሚሊዮን ለሚሆን ህዝብ እንደ ሰደድ እሳት የተመመ ታላቅ ጉብኝት ነው።
የተወደዳችሁ የጽሁፌ ቁም ነገር " በሚገኝበት ፈልጉት ቀርቦም ሳለ ጥሩት" ኢሳ 55:6 እንደሚል ምጥ: ርሃብና ጥማት ሲኖረን ከሰማይ እንጎበኛለን።
ሐዋ. ሥራ 2:17
" እግዚአብሔር ይላል፦ በመጨረሻው ቀን እንዲህ ይሆናል፤ ሥጋ በለበሰ ሁሉ ላይ ከመንፈሴ አፈሳለሁ፤ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻችሁም ትንቢት ይናገራሉ፥ ጎበዞቻችሁም ራእይ ያያሉ፥ ሽማግሌዎቻችሁም ሕልም ያልማሉ፤"
ፓ/ር ዳንኤል መኮነን