25/07/2022
✍️ ፈሶ ወደ ሰማይ
*********************
የተላጠ ጀርባህ ፣ የተገሸለጠው
ለጨካኞች ጅራፍ ፣ ታልፎ የተሰጠው
የተተለተለው ፣ በደም አሸብርቆ
የሚታይ ገላህ ፣ ከገላዎች ልቆ
በኃጢአተኞች እጅ ፣ እየተዋረደ
ምህረት አዝንቦ ፣ ፍቅር ያዥጎደጎደ
በደዌ የደቀቀ ፣ ህማም የበዛበት
ጥፊና ግርፋት ፣ ምራቅ ያረፈበት
ዕርቃን ሰውነትህ ፣ ግፍ የተቀበለው
አንዱ ንጹህ ገላህ ፣ ሁሉን የሰቀለው
በጦሩ ጎንህን ፣ በችንካር እጅህን
በጥፊ ፊትህን ፣ በጅራፍ ጀርባህን
ጭንቀትና ስቃይ ፣ ዝምታ በአንድ ላይ
የተቆለለብህ ፣ በማይስብ መልክህ ላይ
ወደኸኝ ነውና ፣ ልሙትለት ብለህ
እንኳን ስቃይ ገባህ ፣ እንኳን ጭንቅ አለህ
ያለርህራሄ ፣ ያለሀዘኔታ
መስቀል ያሸከመህ ፣ ወደ ጎልጎታ
አባትህ ነውና ፣ ጨክኖ የገደለህ
ኤሎሄ ኤሎሄ ፣ ስትለው ዝም ያለህ
ምነው የዛን ጊዜ ፣ በሰማህ አልልም
አንተ ባትሞት ኑሮ ፣ እኔ ልጅ አልሆንም
ምነው የዛን ጊዜ ፣ ወይ ባለህ አልልም
አንተ ባትቆስልልኝ ፣ የኔ ቁስል አይድንም
እንደውም እንደውም ፣ እንኳንም አልሰማህ
እንኳንም ተላጠ ፣ እንኳን ደማ ጀርባህ
እንኳን ተሰቃየህ ፣ እንኳንም ተጠማህ
እንኳንም ተፉብህ ፣ እንኳን ሲዖል ገባህ
እንኳን አፌዙብህ ፣ እንኳን አንተን ጠሉ
እንኳን ቀሚስህ ላይ ፣ ዕጣ ተጣጣሉ
ኧረ እንደው እንደውም ፣ እንኳን ወይ አላለህ
እንኳን አደቀቀህ ፣ እንኳን አቆሰለህ
እንኳን ውበት አጣህ ፤ እንኳን ደግ እሰየው
አብ እንደሚወደኝ ፣ እንኳን ሰይጣን አየው
ባትጨነቅ ኑሮ
ባትወጋ ኑሮ
ባትገረፍ ኑሮ
ባያደቅህ ኑሮ
አንተ ባትሰቀል ፣ ተተክተህ በ'ኔ
አንፋታም ነበር ፣ እኔና ኩነኔ
ሞተህ ባትነሳ ፣ ጽድቅ ባላገኘሁ
ሞቼ እቀር ነበረ ፣ ሞት እየተመኘሁ
ይብላኝ እንጂ ለሞት ፣ አንተ እንኳን ተሰቀልክ
መልክህን እንድይዝ ፣ እንኳን መልኬን መሰልክ
ከአባትህ ዕቅፍ ፣ እንኳን ወ'ተህ መጣህ
እንኳን ባልሰራኸው ፣ ቅጣቴን ተቀጣህ
በፍቅር እያየህ ፣ ወንድሜ ልትለኝ
ከወዳጅ የሚበልጥ ፣ ወዳጅ ልትሆነኝ
እዛ መስቀሉ ላይ ፣ ተቸንክረህ ሳለ
እዛ መስቀሉ ላይ ፣ ደምህ ሲፈስ ሳለ
እዛ መስቀሉ ላይ ፣ እያማጥክ ሳለ
እዛ መስቀሉ ላይ ፣ ዝለህ ደክመህ ሳለ
ይቅር በለው እያልክ ፣ የበዛ በደሌን
የጠራኸው አንተ ፣ አቤት ያለው እኔን
በእኔ ህመም ቆስለህ ፣ እያከምክ ቁስሌን
ኤሎሄ ያልከው አንተ ፣ አቤት ያለው እኔን
እናማ ምን ሆነ......
በእርግማን ሞትህ ፣ በረከት ሆነኸኝ
ከጽዮን መጥተህ ፣ ከሲዖል ነጥቀኸኝ
በአብ ቀኝ ተገኘሁ ፣ ሞትን ዳግም ላላይ
የደምህ ጅረቱ ፣ ፈሶ ወደ ሰማይ
https://t.me/joinchat/RrbSCabYHAXQ6nx7