03/08/2026
የአዲስ አበባ መጅሊስ ሀገራዊ ተሳትፎ ቀጥሏል፤ ክፍለ ከተሞችም በከተማቸው ንቅናቄ ላይ በልዩ ሁኔታ እየተሳተፉ ነው።
ዛሬ በተጀመረው የአንድ ጀምበር የ800 ሚሊየን ችግኝ ተከላ ላይ የተለያዩ አካባቢዎችና ተቋማት ተግባሩን በስፋት እያከናወኑ ይገኛሉ። ሁሉም የክፍለ ከተማ መጅሊሶች የዚህ ንቅናቄ አካል በመሆን በንቃት እየተሳተፉ ሲሆኑ በኮልፌ ክፍለ ከተማ በነበረው መርሃ ግብር ላይ የአዲስ አበባ መጅሊስ አመራሮችና ስራ አስፈጻሚዎች፤ የከተማው፤ የፌደራል እና የሁሉም ክልል ሙስሊም ወጣቶች ካውንስል አመራሮች፣ የኮልፌ መጅሊስ ስራ አስፈጻሚዎችና ሌሎች እንግዶች ተገኝተዋል።
ለህፃናት በተደረገ የችግኝ ማበርከት ስነ ስርዓት የተጀመረው ችግኝ ተከላው ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞች በተዘጋጀው ቦታ ላይ ተተክሏል።
በዚህ መድረክ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የአዲስ አበባ ከተማ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ፕሬዝደንት ሼህ ሱልጣን ሐጂ አማን ኤባ የአረንጓዴ አሻራ ተግባር የተጀመረው ለመጪው ትውልድ ምቹ፣ ውብና አረንጓዴ የለበሰች ሀገር ለማስረከብ በማሰብ መሆኑን ተናግረዋል።
ተግባሩ የአፈር መሸርሸርን ብቻ ለመከላከል ሳይሆን፣ የውሃ ሃብታችንን ለመጠበቅ፤ የዓለም አየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም ጭምር መሆኑን ፕሬዝደንቱ ሼህ ሱልጣን አማን ገልፀዋል።
ተግባሩ በዲናችን የታዘዝንበት በመሆኑ የአዲስ አበባ መጅሊስ እንደቀደመው ሁሉ የዘንድሮውን የክረምት መርሃ ግብር ከሐምሌ 15/2018 ጀምሮ በተለያየ ዘርፍ አጠናክሮ ቀጥሏል ያሉት ሼህ ሱልጣን አማን ሀገራችንን ማልማት፤ ሠላሟን ማስጠበቅና ለሀገራችን ጥሪ ምላሽ መስጠት ቀዳሚ ኃላፊነታችን ነው በማለት ተናግረዋል።
ችግኝ ስንተክል፤ ትውልድን መትከል፤ ሀገራችንን ማልማት ነውና በተግባሩ ላይ በንቃት መሳተፍ ያስፈልጋል በማለት አሳስበዋል።
ችግኝ መትከል ምድርን መጠበቅ መሆኑን ያስታወሰው የኢትዮጵያ ሙስሊም ወጣቶች ካውንስል ፕሬዝደንት ኡስታዝ ሐይደር ከድር ሲሆን ችግኝ ተከላው ተፈጥሮን ንፁህ ማድረግና ትልቅ ተግባር መሆኑን ገልጿል። ዓለምን እያስጨነቀ ያለው የአየር ንብረት ለውጥን ተፅዕኖ ለመቋቋምና ተፈጥሮን ለመጠበቅ ችግኝ ተከላ ወሳኙ መፍትሔ መሆኑንም አንስቷል።
የአዲስ አበባ መጅሊስ ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዝደንት ሼህ ሙሐመድ ሸሪፍ ችግኝ ስንተክል ሰላምንና አብሮነትን መትከል ያስፈልጋል ብለዋል።
የአዲስ አበባ መጅሊስ አስተዳደራዊ ጉዳዮች እና ተቋማዊ ልህቀት ምክትል ፕሬዝደንት ኡስታዝ ሺሐቡዲን ሼህ ኑራ ተፈጥሮን መንከባከብ ከዲነል ኢስላም አንፃር ሲታይ ተሻጋሪ መሆኑንና ቀጣዩን ትውልድ እንዲጠቅም መደረግ ላይ ማተኮርና ልብ ማለት ያስፈልጋል ብሏል።
ኡስታዝ ሺሐቡዲን ሼህ ኑራ ወጣቶች ከዚህ ኢስላማዊ ትዕዛዝና ተግባር መማር ያለባቸው፤ የሚሠሯቸው ስራዎች ለሌሎች ሰዎች የሚጥቅሙ መሆናቸውን ማረጋገጥና ቀጣይነቱን ማሰላሰል ያስፈልጋል ብለዋል።
ተቋም ስንገነባ እኔ ባልኖር እንዴት ለሌሎች ጠቃሚ መሆን ይችላል የሚለውን ጥያቄ በተገቢው መመርመርና ሂደቱንም በንቃት መከታተል ይገባል ያሉት ኡስታዝ ሺሐቡዲን ችግኝ ተከላውንም በዚህ የተሻጋሪ እሳቤ መስራት ያስፈልጋል ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
የኮልፌ ክፍለ ከተማ እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ዋና ስራ አስፈጻሚ ኡስታዝ ሐሺም ሺፋ የዛሬው ተግባር በቀረበው ብሔራዊ ጥሪ መሠረት ነብያዊ አስተምህሮን መነሻ አድርገን፤ ተፈጥሮን ስለመንከባከብ ለትውልድ አስተምረንበት የሚያልፍ ተግባር መሆኑን ተናግረዋል።
ይህ መርሃ ግብር በዛሬው ዕለት በዘመቻ መልኩ የሚከናወን ቢሆንም በዲናዊና ትዕዛዝነቱ ምክንያት በመጅሊስ በኩል ተጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል።