28/01/2026
"የቅድስት ድንግል ማርያም፡ ኣርያማዊ ፍልሰቷ ዜና!"
እኛ የእትዮጵያ ልጆች፡ ቀድሞ፡ በሥነ ፍጥረት፥ ኋላም፡ በእየሱስ መሲሕ ተገልጾ፡ ብዛታቸው፡ ሊቆጠር የማይቻል፡ መልካካም ነገሮችን፡ ላበረከተልን ፈጣሪያችን፡ ለእግዚኣብሔር፡ እንደምናደርገው ኹሉ፥ "እግዝእተብሔራችን እና መድኃኒታችን፣ እናታችንና ሃይማኖታችን፥ ኣገራችንና ንግሥታችን" ስለኾነችው፡ ስለቅድስት ድንግል ማርያምም፡ በየኅሊናችን የምናስበው፥ በኣንደበታችን የምንናገረውና በየሕዋሳታችን የምንፈጽመውም ኹሉ፡ በየሕይወታችን ውስጥ፡ ዓብሮን ሕያው ኾኖ፡ ለዘወትር፡ ባለማቋረጥ የሚካኼድ እንጂ፡ በኣንድ ቀን፥ ወይም፡ በኣንድ ሳምንት፥ ወይም፡ በኣንድ ወር፥ ወይም፡ በኣንድ ዓመት ብቻ፡ የተወሰነ ኣይደለም።
ኣኹንም፡ እዚህ ላይ ኣቅርበን የምንጽፍላችሁ፡ የእግዝእተብሔር እም፡ ድንግል ማርያምን ዜና መዋዕሏን፡ በተለይ፡ በኣዲስ ኪዳኑ መጽሓፍ ውስጥ፡ ተመዝግቦ የሚነበበውን፥ ልጇ ሰላማችን እየሱስ መሲሕ፡ እስካረገበትና መንፈስ ቅዱስ፡ በሓዋርያት ላይ፡ እስከወረደበት ቀን ድረስ ያለውን ሳይኾን፡ ከዚያ በኋላ፡ በዚያው መልክና ይዘት የቀጠለው፡ ምድራዊ ሕይወቷ፡ በ፷፬ ዓመታት ዕድሜዋ ካበቃበት፡ ከ"ፍልሰቷ"፡ ማለትም፡ ሕያው በኾነው በኣካለ ሥጋዋ፡ ከምድር፡ ወደገነት ተነጥቃ ከተወሰደችበት ቀን ተነሥተን፡ የመጨረሻ የኾነውን፡ ዜናዋን ብቻ ይኾናል፤ እርሱም፡ ይህንኑ፡ የፍልሰቷን ዝክረ ነገር በምናስታውስባቸው፡ በነሓሴ ወር የሱባዔያችን ኹለት ሳምንታትና የፍልሰትዋን በዓል በምናከብርባት፡ በዚያች ዕለት፡ እንዲህ በሚለው ቃል ይገለጻል፦
በመጀመርያ ነገር፡ "ፍልሰታ" ምንድር ነው?
የእናታችን፣ የቅድስት ድንግል ማርያም ፍልሰት የኾነው፡ "ኣስተርእዮ ማርያም" ብለን በምናከብረው በጥር ፳፩ ቀን፥ በዕለተ እሑድ ነው። "ፍልሰት"፥ ወይም፡ "ፍልሰታ" የሚባሉት ኣርእስት ቃላት፡ "ፈለሰ" ('ለ' ሳይጠብቅ) ከሚለው፡ "ከቦታ ወደቦታ መዘዋወርን"፡ ማለትም፡ "ኣንድ ሰው፡ ካለበት ቦታ ተነሥቶ፥ ወይም፡ መኖሪያውን ነቅሎ፡ ወደሌላ ኼደ፤ ወይም፡ ተወሰደ!" የሚል ትርጕምን ከሚያመለክተው፡ ከግእዝ ዘር የተገኘ ዘይቤ ነው፤ በእትዮጵያኛ፡ "ለ" ጠብቆ፡ "ፈለ ሰ" ያሰኛል። ከዚህ የተነሣ፡ የቅድስት ድንግል ማርያም ሕያው ሰውነት፡ ከምድር፡ ወደሰማያዊቷ ገነት የመወሰዱን ተኣምር ለማስረዳት፡ "ፍልሰታ" እንላለን።
ይህ፡ "ፍልሰታ" የሚለው ቃል፡ በቅዱሱ ኪዳን የእትዮጵያ ልጆች ዘንድ መነገር የጀመረው፡ የመለኮትና የትስብእት ተዋሕዶ ተፈጽሞበት፡ እግዚኣብሔር ወልድን ፀንሶ የወለደውንና ዓጥብቶ ያሳደገውን፡ ያን፡ የእግዝእተብሔር እም፡ የቅድስት ድንግል ማርያምን ሕያው ሰውነት፡ ኣይሁድ፡ እጅግ በከፋው ኣላዋቂነታቸውና ሰይጣናዊ ኣስተሳሰባቸው፡ የሚቻላቸው መስሏቸው፡ በእሳት ኣቃጥለው ሊገድሏት በሞከሩበት ጊዜ ነው።
ለእነርሱ መዳን ሲል፡ በሰውነት መጥቶ፡ ያን፡ የሰላመ-መስቀል ቤዛነት ተልእኮውን ፈጽሞ፡ ወደክብሩ በተመለሰው፡ በልጇ በወዳጇ፡ በእየሱስ መሲሕ ሰውነት ላይ፡ ኣድርገውት የነበረውን፡ ያንኑ ግፍና ጭካኔያቸውን፡ ኣኹንም፡ በዚያ፡ በእርሷ መለኮታዊ ሰውነት ላይ ለመፈጸም ባሰቡበት፥ በማሰብም ብቻ ሳይወሰኑ፡ ኣዎን! በሞከሩበት ጊዜ እንጂ።
እርሷንስ፡ እንኳን ሞት፡ ኣንዳችም ጉዳት፡ የጨረፍታ ያህል እንኳ፡ ሊያልፍባት እንደማይቻል፡ ኣይሁድ፡ ኣኹንም፡ ኣላወቁም። ገና ከመጀመሪያው፡ በፍጹም ሃይማኖቷና ምግባሯ፡ ሰውነቷን ለኣምላክነት በማብቃቷ፡ እግዝእተብሔር እም የተዋሓደቻትን፥ የእግዚኣብሔር ኣብ ሙሽሪት፡ በእግዚኣብሔር መንፈስ ቅዱስ ግብር፡ ኣንድዬ ልጃቸውን፡ እግዚኣብሔር ወልድ እየሱስ መሲሕን፡ ከፍጥረተ-ዓለም በፊት፡ በመለኮትነት፥ ከፍጥረተ-ዓለም በኋላም፡ በሰውነት የወለደችለትን፡ የእርሷን፡ መለኮታዊና ትስብእታዊ ሰውነት፡ እንዴት፡ ክፋትና ኃጢኣት፥ ሞትና መቃብር፥ መበስበስና ሌላውም ዓይነት ጕዳት፡ እንኳንስ ሊደርስበት፡ ሊቀርበውም እንኳ፡ ኣዎን! እንዴት ይቻለዋል? ፈጽሞ ኣይቻለውም። እንኳንስ እርሷ፡ በእርሷና በልጇ በማመን፡ እየራሳቸውን፡ ለእውነተኛው የቅዱሱ ኪዳን እትዮጵያዊነት ያበቁት ኹሉ እንኳ፡ በእርሷና በልጇ መሥዋዕትነትና ቤዛነት ምክንያት፡ ከክፋትና ከኃጢኣት፥ ከሞትና ከመቃብር መበስበስ ሳይቀር፡ ነጻ ኾነው፡ ምንም ዓይነት ጉዳት በሌለበት፡ በዘለዓለሚቱ የሰንበት ዓለም፡ ቅድስቲቱን የትንሣኤ ሕይወት፡ እንደሚኖሩ፡ ኣዎን! ገና ኣላወቁም።
እርሷም፡ እነዚያ ኣይሁድ፡ በእርሷ ሰውነት ላይ ሊያደርጉ ያሰቡትን፥ ኣስበውም ኣልቀረ፡ የቃጡትን፡ ያን ጉዳት ሊያደርሱ እንደማይቻላቸው፡ በመለኮታዊው ኃይሏ፡ እንደሚሰማቸው ኣድርጋ፡ ኣሳወቀቻቸው። ከዚህ በኋላ፡ በመላእክት ተነጥቃ፡ ወደገነት ተወሰደች። ይህ፡ "ፍልሰታ" የሚለው ቃል፡ በቅዱሱ ኪዳን የእትዮጵያ ልጆች ዘንድ መነገር የጀመረው፡ ኣዎን! ይህ መለኮታዊ ትንግርት ከተፈጸመበት፡ ከፍልሰቷ ዕለት፡ ከጥር ፳፩ ቀን፣ ፵፰ ዓመተ-ምሕረት ኣንሥቶ ነው።
"መንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ"፥ "እትዮጵያ፡ የእግዚኣብሔር መንግሥት" የምንላት፡ እግዝእተብሔር እም፡ ድንግል ማርያም፡ እንዲህ፡ በመላእክት ተነጥቃና በሰማያዊ ይባቤ ታጅባ፡ ወደገነት በፈለሰች፥ [በተወሰደች] ጊዜ፡ የኾነውን ደግሞ እንስማ!
ልጇ ወዳጇ እየሱስ መሲሕ፡ በመስቀል ላይ ተቸንክሮ፡ ቅዱስ ሥጋውን እየቆራረሰና ክቡር ደሙንም እያፈሰሰ፡ የሰላም ቤዛነቱን ተልእኮ እየፈጸመ ባለበት ሰዓት፡ ከመስቀሉና ከቅድስት እናቱ ድንግል ማርያም ኣጠገብ ሳይለይ፡ የዚሁ ልጇን ኣደራነት ተቀብሎ፡ እርሷን፡ እናት፥ ራሱንም፡ ልጇ ኣድርጎ፡ ይጠብቃት የነበረው፡ ወንጌላዊው ዮሓንስ፡ ኣኹንም፡ ዓብሯት ኾኖ፡ ይህንኑ የፍልሰቷን ምስጢር ለማየት የበቃ ኾነ።
ሌሎቹ ሓዋርያት ግን፡ ይህን ታላቅ ተኣምር ባለማየታቸው፡ በሚቀጥለው፡ በነሓሴ ፩ ቀን፡ የኹለት ሳምንት ሱባዔን ጀመሩ። ይኼም ሱባዔያቸው፡ የነገሩን ኹሉ፡ እውነተኛ ምስጢር ስለገለጠላቸው፡ ፍሬያማውን ምላሽ ማግኘት እንደቻሉ ኣረጋገጡ። እግዝእተብሔር እም፡ ቅድስት ድንግል ማርያም፡ በነሓሴ ፲፬ ቀን፡ በዕለተ እሑድ፡ በዚያው፡ በሕያዉ ሰብኣዊ ኣካሏ እንደገና፡ ወደምድር መጥታላቸዋለችና። በልጇ ትንሣኤ ጊዜ እንደኾነውም፡ በመካከላቸውም ተገኝታ፡
"ሰላም ለኵልክሙ!"፡ ማለትም፡ "ሰላም፡ ለእናንተ ይኹን!" ኣለቻቸው። ያም ኹኔታ፡ ለሓዋርያት፡ ያን፡ የኣምላካቸውንና የፈጣሪያቸውን፥ የመምህራቸውንና የሰላማቸውን፡ የእየሱስ መሲሕን ትንሣኤ ኣስታወሳቸው። የእርሷንም፡ በዚህ፡ እውን በኾነው ሕያው ማንነቷ፡ ድንገት ተገልጣ፡ በመካከላቸው የመገኘቷን ዕፁብ ድንቅ ነገር፡ እንደትንሣኤዋ ኣድርገው፡ በታላቅ ሓሤት ተቀበሉት።
እርሷም፡ ከዚያ ኣያይዛ፡ በብዙ የምሥራች ቃላት፡ እኒህኑ ሓዋርያትን፡ ኣጽናናቻቸው። እነርሱም፡ እጅግ ደስ ብሏቸው፡ ከእርሷ ጋር፡ እስከነሓሴ ፲፮ ቀን ድረስ፡ ለሦስት መዓልትና ለሦስት ሌሊት፡ ዓብራቸው ቆየች። በዚያኑም ዕለት ተሠወረቻቸው። ከዚህ በኋላ፡ ኣልፎ ኣልፎ፡ በየግላቸውም ኾነ፡ በጋራ እየተገለጠችላቸው፡ እርሷ ስላወቀቻቸውና ስላየቻቸው፡ ስለብዙዎች መለኮታውያት ምሥጢራት፥ ደግሞም፡ ኣኹን እርሷ፡ ለእነርሱ የተገለጠችበት ኹናቴ፡ እንደልጇ ትንሣኤ ኾኖ መቅረቡን ኣምነው እንዲቀበሉት፡ ለዓርባ ቀናት ያህል፡ ስታሳውቃቸውና ስታነቃቃቸው ሰነባበተች። ይህን ሕያው ፍልሰታዋን፡ እንደልጇ ትንሣኤ ኣድርጋ እንደገለጠች ኹሉ፡ ዕርገቷንም እንዲሁ፡ እንደልጇ ታደርግ ዘንድ ፈቃዷ ስለኾነ፡ የሕያው ትንሣኤዋን እውነታ፡ ማሳወቅ የጀመረችበትን፡ ነሓሴ ፲፬ ቀንንና የጨረሰችበትን፡ ነሓሴ ፲፮ ቀንን፡ እነዚህን፡ ሦስት መዓልታትና ሦስት ሌሊታት መነሻ በማድረግ፡ በኣርባኛው ዕለት፡ በመስከረም ፳፩ ቀን፡ እንደልጇ እየሱስ መሲሕ፡ ወደሰማይ ዓረገች። በጥር ፳፩ ቀን ተጀምሮ፡ በመስከረም ፳፩ ቀን ያበቃውን፡ የፍልሰቷን ነገር ኣካትቶ ለማዘከር ተብሎ፡ የተመደበ ቃል ነው፡ ይህ፡ "ፍልሰታ" የሚለው ዘይቤ።
የመለኮት ድንቅ ምሥጢራዊ ኃይል የኾነው፥ በልጇ፡ በወዳጇ፡ በእየሱስ መሲሕ ብኵርናና ቀዳሚነትም የተጀመረው፡ ይህ፡ የትንሣኤና የዕርገት ነገር፡ ኣኹን ደግሞ፡ በእርሷ፡ በእናቲቱ ድንግል ማርያም፡ ገሃድና እውን ኾኖ የታየበትን፡ ይህን ዕርገቷን ለማየትና ምስክር ለመኾን የታደለው፡ ቀድሞ፡ የልጇን ትንሣኤ የመጀመሪያ ምሥራች፡ ከቀሩት ሓዋርያት ጋር ለመስማትና ለማየት፡ ሳይታደል ቀርቶ የነበረው፡ ሓዋርያው ቶማስ ብቻ እንደነበረ ይታወሳል።
ኣኹን ግን፡ የፍልሰት ትንሣኤዋን ባያይም፡ ዕርገቷን ለማየት፡ ከቀሩት ሓዋርያት መካከል፡ ተለይቶ የታደለው፡ ይኸው፡ ሓዋርያው ቶማስ ብቻ ኾኖ ተገኘ። ከቶማስ ጋር የተያያዘው፡ የዚህ ርእስ ዝክረ ነገር፡ እንዲህ የሚል ነው፦ "ይህ ኹሉ ሲኾን፡ ማለትም፡ በመጀመሪያው ሱባዔ ጊዜ፡ ሓዋርያው ቶማስ፡ በቦታው ኣልነበረም። ለሓዋርያት በተሰጣቸው፡ የመንፈስ ቅዱስ ጸጋና ኃይል፡ እርሱም እንደለመደው፡ ደመና ጠቅሶ፡ እግዚኣብሔር ባወቀውና ባደረገው ምክንያት፡ ዘግይቶ፡ በዚያ በደመናው እየተጓዘ፡ ከሃገረ ስብከቱ፡ ወደወንድሞቹ ሓዋርያት ሲመጣ፡ እግዝእተብሔር እም፡ ቅድስት ድንግል ማርያም፡ እያረገች ሣለች፡ እርሷ ባሰበችው በጎ ምክንያት፡ ለእርሱ፡ ለቶማስ ተገለጠችለት። "ያችም ዕለት፡ ለሓዋርያት፡ እንደልጇ እየሱስ መሲሕ፡ የእርሷም፡ የፍልሰት ትንሣኤዋ የኾኑላቸውን፡ ከነሓሴ ፲፬ እስከ ፲፮ ቀን ያሉትን፡ ሦስት መዓልታትና ሦስት ሌሊታት መነሻ በማድረግ፡ እንደልጇ ዕርገት በኣርባኛው ዕለት፡ ወደሰማይ ያረገችባት መስከረም ፳፩ ቀን እሑድ ናት።
"ቶማስም፡ ከደመናው ሊወድቅ እስኪናወጽ ድረስ፡ ሰውነቱ ታውኮበት፡ 'ቀድሞ፡ ሌሎቹ ወንድሞቼ ኹሉ ታድለው፡ የልጅሽን ትንሣኤ ሲያዩ፡ እኔ ብቻ ሳላይ ቀረሁ። አኹን ደግሞ፡ እነርሱ፡ ኹላቸው፡ ይኸው፡ የኣንቺን የፍልሰት ትንሣኤ፡ ቀድመውኝ ሲያዩ፡ እኔ ብቻ ሳላይ ቀረሁ!' ብሎ፡ ማዘኑን ገለጠላት። "ቅድስት ድንግል ማርያምም፡ 'ኣይዞህ! ኣትዘን! እኒያ ወንድሞችህ፡ በልጄ ጊዜ፡ በመጀመሪያ፡ የእርሱን የትንሣኤ ምሥራች፡ ከሌሎች ሴቶች ሓዋርያት ሰምተው ሳያምኑ በመቅረታቸው፡ ኋላ፡ ከኣንተ በፊት፡ እነርሱ ያዩት ቢኾንም፥ ኣንተ፡ ለጊዜው፡ በዚያ ባለመኖርህ፡ ሳታየው ብትቀርም፡ ዕርገቱን፡ ዓብረሃቸው ኾነህ ኣይተሃል። ኣኹንም፡ እነርሱ፡ የእኔን፡ የፍልሰት ትንሣኤዬን ያዩ ኾነው፡ ኣንተ፡ ያላየህ ብትኾንም፡ ይኸው፡ አኹን ደግሞ፡ ዕርገቴን ያየህ፡ ኣንተ ብቻ እንጂ፡ እነርሱ ኣላዩም። ስለዚህ፡ ከእነርሱ ይልቅ፡ በበለጠ የታደልህ፡ ኣንተ ነህ፤ ፍልሰቴንም፣ ዕርገቴንም፡ ኹለቱንም፡ በኣንድነት ኣይተሃልና።' ብላ ኣጽናናችው። ቀጥላም፡ እንዲህ ኣለችው፦ 'ኣኹንም፡ ወደእነርሱ ኼደህ፡ ‹ዓረገች!› ብለህ፡ ንገራቸው።' ይህንም ብላ፡ የውስጥ መጐናጸፊያዋን ሰጥታ፡ ሰደደችው። እርሱም፡ በግንባሩ ሰግዶና በእጇ ተባርኮ ተሰናበታት። ቶማስ፡ ከቦታው ደርሶ፡ በሱባዔና በጉባኤ የሰነበቱ ወንድሞቹን ሓዋርያትን ሲገናኛቸው፡ "ኧረ! የእመቤታችን ነገር፡ እንደምን ኾነ?" ብሎ ጠየቃቸው። እነርሱም፡ የኾነውን ኹሉ፡ ነገሩንም፡ ኣንድ በኣንድ እየተቀባበሉ፡ ምንም ሳያስቀሩ ነገሩት። እርሱም፡ ነገራቸውን፡ ካስጨረሳቸው በኋላ፡ "ታዲያ! ኣኹን፡ ቅድስት እናታችን፡ የት ነው ያለችው? እጅግ ናፍቃኛለችና፡ ኼጄ፡ እንድሳለማት፣ እንድሰግድላትም፡ ያለችበትን መካን ኣሳውቁኝ!" አላቸው።
በዚህ ጊዜ፡ ቅዱስ ጴጥሮስ፥ ዓብረውት ያሉት፡ የቀሩት ሓዋርያትም፡ ኹሉም፡ የሚመልሱት ኣጥተው፥ ኣቀርቅረው፡ ዝም ኣሉ። ቶማስም፡ ጥያቄውን በመቀጠል፡ "እንዳበሠራችሁኝ፥ በትንሣኤ መልክ ከታየችበት፡ ከመጀመሪያው ኣስተርእዮቷ በኋላ፡ እስካኹን እንዳስለመደቻችሁ፥ ልጇ መሲሓችንም፡ እስከዕርገቱ ድረስ፡ ኣልፎ ኣልፎ እየተገለጠ ያነጋግረን እንደነበረው ኹሉ፡ ምናልባት፡ ድንገት፡ በመካከላችን፡ ትገኝ እንደኾነ፡ እንጠብቃት ይኾን?" ኣላቸው፡ እያንዳንዳቸውን፡ ተዘዋውሮ እየተመለከተ።
እነርሱም፡ ኹሉም ማለት ይቻላል፡ "አዎን! ልክ ነህ። ይህ ያልከው ነገር፡ 'ኣይኾንም!' ኣይባልም። እንዳልኸው፡ ምናልባት፡ ሊኾን ይችል ይኾናል!" በሚል ስሜት ይመስላል፡ ቀና ብለው እያዩት፡ ወደዝምታቸው ተመለሱ። በዚህን ጊዜ፡ ቶማስ፡ ባጭር ቃል፡ "መቼም፡ 'ኣታምኑኝም!' ብዬ ነው እንጂ፡ ደስ ይበላችሁ! ቅድስት እናታችን ዓርጋለች! በልጇ ጊዜ፡ በራሴ ድክመትና ጥፋት፡ በራሴ ላይ ያሳደርሁትን፡ የዘለዓለም የፀፀት እሳት፡ በርኅራኄዋና በቸርነቷ ልታስወግድልኝ ፈቃዷ ኾኖ፥ ለዚያ በደሌ፡ ዋጋዬን እኔ መክፈል ሲገባኝ፡ እንዲያውም፡ ይህ ካሣ ይኹንህ!' ብላ፡ ይህን ቸርነት ኣደረገችልኝ! በማለት፡ ወንድሞቹ ሓዋርያት ትኩር ብለው እየተመለከቱት፡ በግንባሩ ተደፍቶ፡ ሥቅሥቅ ብሎ ኣለቀሰ፤ የደስታ እንባውንም ኣፈሰሰ። ሓዋርያትም፡ ባንድነት ኾነው፡ ከወደቀበት ካነሡት በኋላ፡ "እንኳን ደስ ኣለህ!" ከሚል ቃል ጋር በፍቅር ኣጽናኑት።
ቶማስም፡ በደስታ ፈክቶ፡ "እኔ በሌለሁበት ስለኾነው ኹሉ፡ እናንተ፡ ኣኹን ያላችሁኝን ጨምሮ፡ ከእርሷ ሰምቼዋለሁ። ለኹላችንም የሚኾን የእናትነት ምክሯንም ለግሣኛለች። በብዙ ኣጽናንታኛለች። ይህን የውስጥ ተደራቢ መጐናፀፊያዋን፡ ለኹላችንም፡ ለበረከት እንዲኾነን፡ በእኔ እጅ ሰድዳላችኋለችና፡ ተረከቡኝ!" ብሎ ሰጣቸው። ሓዋርያትም፡ ያን፡ የእናትነት ስጦታዋን በማየታቸውና በማግኘታቸው፡ እጅግ ደስ ብሏቸው ተቀብለው፡ ለበረከት ተካፈሉት። ይህ በኾነ፡ ልክ በዓመቱ፡ የቀሩት ሓዋርያት፡ "ቶማስ፡ ዕርገትሽን ኣይቶ፡ እኛ ሳናይ፡ እንዴት እንቀራለን? እኛንም፡ ለዚህ ዕድል ኣብቅተሽ ኣሳዪን!" ብለው፡ ወደፈጣሪያቸው የሚቀርብ፡ ኹለተኛውን፡ የ፪ ሳምንት ሱባዔያቸውን፡ ቶማስ ጭምር፡ ዓብሮኣቸው በተገኘበት፡ በነሓሴ ፩ ቀን፡ በተገቢው ጾምና ጸሎት፥ ትህርምትና ብሕትውና፡ በኣንድነት ጀመሩ። የኹለተኛው ሳምንት ሱባዔ፡ በነሓሴ ፲፬ ቀን፡ ከተፈጸመ በኋላ፡ በነሓሴ ፲፭ ቀን፡ ሓዋርያት ያደረጉት ይህ ነው፦
በመጀመርያ፡ ከእየግል በኣታቸው ወጥተው፥ በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴነቷና በእግዚኣብሔር መንግሥትነቷ፣ በኪዳነ ምሕረትነቷም፡ ኹሉን ኣንድ ኣድርጋ በምትመለከውና በምታስመልከው፡ በእግዝእተብሔር እም፡ ድንግል ማርያም ዙሪያ፡ በኣንድነት ተሰብስበው፡ ሱባዔያቸውን፡ በሰላምና በፍቅር ስላስፈጸመቻቸው፡ ምስጋናቸውን፡ በኅብረት ጸሎታቸው ውዳሴና ቅዳሴ ኣቀረቡ። በመጨረሻ፡ በነሓሴ ፲፮ ቀን፡ የሚከበረው በዓል፡ ፍልሰታን በሚመለከት፡ እስካኹን የተነገረውን ኹሉ፡ የሚያካትት ኾኖ፡ ፍጻሜው፡ በሰማያት ኾነ በምድር ዓለማት፥ በሥጋዊዉ ኾነ በመንፈሳዊው ፍጥረት ዘንድ፡ ምን እንደኾነ፥ ከምን ዓይነቱ የብቅዓት ደረጃም እንደደረሰ፡ ኣረጋግጦ የሚያሳየውን መለኮታዊና ፍጥረታዊ ክንውን፡ መመልከት ነው። ይህንም እውነታ፡ እንዲህ የሚለው፡ የመጨረሻ ኣጭር የማጠቃለያ ቃል ይገልጸዋል፦
በነሓሴ ፲፮ ቀን በሚውለው፡ በፍልሰታ ለማርያም መታሰቢያ ዕለት፡ ሓዋርያትና እነርሱን የመሰሉት ኹሉ፡ በእግዚኣብሔር መንፈስ ቅዱስ፡ ወደሰማያዊቷ እትዮጵያ፡ የእግዚኣብሔር መንግሥት ተነጥቀው ኼደው፡ እግዝእተብሔር እም፡ ቅድስት ድንግል ማርያም፡ በመንበረ ጸባዖትነቷና በቅዱሱ ኪዳን የእግዚአብሔር መንግሥት እትዮጵያነቷ የምትገኝበትን ክብርና ምስጋና ኣዩ! ያያሉም። ልጇ ወዳጇ እየሱስ መሲሕ፡ እርሷን፡ ቅድስት እናቱን፡ መንበር፥ ራሱን፡ ሠራዒ (ዋና) ካህን፥ ሊቀ ሓዋርያት ጴጥሮስን፡ ንፍቅ (ረዳት) ካህን፥ ቀዳሜ ሰማዕት እስጢፋኖስን፡ ሠራዒ ዲያቆን፣ ፊልጶስንም፡ ንፍቅ ዲያቆን ኣድርጎ፡ ቀድሶ፥ ራሱም ቆርቦ፥ እናቱንም ኣቍርቦ፥ ካህናቱንና ሓዋርያትን፣ እነርሱን የመሰሉትንና በዚያ የታደሙትን ኣማኞቹን ኹሉ ኣቆረበ። ያቆርባልም። በዚያን ጊዜ፡ በመላው ፍጥረታተ ዓለማት ዘንድ፡ በሥጋም፥ በነፍስም፥ በመንፈስም፡ ታላቅ ደስታ፥ ታላቅ ሓሤት ኾነ! ይኾናልም።
(ራእ. ፲፩፥ ፲፱፤ ፲፪፥ ፩-፲፯።)
+ + +