Rhema FM Eth. /Apostolic Mission/

Rhema FM  Eth. /Apostolic Mission/ Contact information, map and directions, contact form, opening hours, services, ratings, photos, videos and announcements from Rhema FM Eth. /Apostolic Mission/, Religious organisation, Rhema Faith ministry, Addis Ababa.

23/09/2021
ሰላም የተወደዳችሁ የገጻችን ተከታታዮች ይህንን ጽሁፉ ያጋሩንን ወገኖች እያመሰገንን በቀጣይ በኢሉባቡር ዞን ቡሬ ከተማ አብረውት ያገለገሉና በአገልግሎቱ ወደ ጌታ የመጡ ወገኖች የሰጡንን ምስክ...
23/09/2021

ሰላም የተወደዳችሁ የገጻችን ተከታታዮች ይህንን ጽሁፉ ያጋሩንን ወገኖች እያመሰገንን በቀጣይ በኢሉባቡር ዞን ቡሬ ከተማ አብረውት ያገለገሉና በአገልግሎቱ ወደ ጌታ የመጡ ወገኖች የሰጡንን ምስክርነት እናቀርብላችኋለን ።
ተባረኩ

!!
©ዘሪሁን ግርማ

አንድ ከሰአት ከአንድ ወዳጄ ከሆነ መጋቢ ጋር አንድ አገልጋይ ልናገኝ "ምስክር ምግብ ቤት" ሔድን ፡፡ እዚያ ሆነን እያወራን እያለ የቤቱ ባለቤት ወንድም (ጋሽ) እንዳለ ሳይታሰብ በመሐላችን ተከሰቱና ጫወታ ጀመርን፡፡ ከዚያ እርሳቸው እነ ሐዋሪያው ዘውዴ፤ መጋቢ ዮናስ ሰይፋ፥ ወንጌላዊ ገብሩ ወልዱ፤ መጋቢ ታሪኩ ቴዎድሮስ ወዘተ የእርሳቸው ቤት ይደረግ የነበረ ፕሮግራም ፍሬዎች መሆናቸውን ተናገሩ፡፡ እኔም ስለ እርሱ ስሰማ አገልግሎቱና ህይወቱ ይስበኝ ስለ ነበረውና ስለ እርሱ ብዙ ጊዜ ሲነገር ስለምሰማው ግን በአካል አግኝቼው ስለማላውቀው እንዲሁም ሲያገለግል አይቼ ስለማላውቀው ሐዋሪያው ዘውዴ ጠየኳቸው፡፡ እርሳቸውም፦

" እንደ እርሱ ያለ ለወንጌል የኖረ ፤ በገንዘብም በህይወትም በምንም የማይከሰስ ሰው አላየሁም" አሉኝ፡፡ ከዚያ ውይይት በኃላ ስለ ሐዋሪያው ዘውዴ ለመጻፍ አሰብኩ። መጀመሪያ ያደረገኩት ስለ እርሱ የሚያውቁትን መጠየቅ ነው። መጀመሪያ አብሮት ብዙ ዘመን ያገለገለው መጋቢ ታሪኩ ቴዎድሮስን ጋር ሄድኩ ጠየኩት። ስለ ሐዋሪያው ዘውዴ ከመጋቢ ቴዎድሮስ ጋር ባደረኩት ቃለ መጠይቅ "እኔ በሞራል በለው፥ በገንዘብ በለው፥ ለወንጌል በመኖር በለው እንደ ዘውዴ ያለ ሰው አላየሁም፥ እኔ እስከ አሁን ድረስ ቢገስጸኝ ደስ የሚለኝ ዘውዴ ብቻ ነው" አለኝ፡፡

ሐዋሪያው ንጉሴ ሮባ ስለ ሐዋሪያው ዘውዴ ሲነሳ እንደ ምሳሌው የሚያየው መሆኑን ይናገራል፡፡ ስለ ሐዋሪያው ዘውዴ ህይወትና አገልግሎት ስጠይቀው "ትክክለኛ የእግዚአብሔር ሰው ማለት ሐዋሪያው ዘውዴ ነው "ብሎኛል፡፡ ፓስተር ክንፈገብርኤል ደግሞ በአንድ ወቅት ስለ ሐዋሪያው ዘውዴ በአጋጣሚ ስናወራ "የኢትዮጵያን መንፈሳዊ አቅጣጫ የቀየረ ነው፤ ብዙዎቻችን የተለወጥነው በእርሱ አገልግሎት ነው" ብሎኛል፡፡ በስልክ ከጋሽ በቀለ ወልደኪዳን (መጋቢ) ጋር ስለ ሐዋሪያው ዘውዴ ለመጻፍ እንዳሰብኩ ስጠይቀው " ሊጻፍለት የሚገባ ብዙ ያልተነገረለት ሰው ነው " ብሎኛል፡፡

ሐዋሪያው ዘውዴ አዲስ አበባ አገልግሎቱ ከመጀመሩ በፊት በጋምቤላ አካባቢ ቤተክርስቲያን ተክሏል በዛም ብዙ አገልግሏል። ሐዋሪያው ዘውዴ ራሱን ለሰዎች አይግለጥ እንጂ አሁንም ድረስ ከእንግሊዝ ወደ ባሌና አርሲ በመመላለስ ወንጌልን የሚሰራ፣ ትምህርት ቤት ሳይቀር የከፈተ አገልጋይ ነው። ሐዋሪያው ዘውዴ በመንፈስ ቅዱስ የመመራት ህይወቱና ፤ በድንገት የሚወስዳቸው ያልተለመዱ ልምምዶቹ ብዙዎቹን ያስደነግጥ ነበር፡፡ ጋሽ እንዳለ ሲነግሩኝ " በሰርጉ ዕለት ሐይለኛ ዝናብ ሊጥል እያጉመተመተ መጣውና የሰርጉ ስርአት ቶሎ ቶሎ እንዲሆን ስነግረው ዘውዴም " ዝናቡ አይመጣም ብሎ ገሰጸው ዝናቡ ሔደ" ብለውኛል፡፡ በመቀጠልም " እኛም ጋር ይኖር ስለነበር ክፍሉ ውስጥ እየጸለየ ከቆየ ክፍሉ ውስጥ ድንገት ከገባን ደስ የሚል የመንፈስ ቅዱስ ጠረን በሐይል እንደ ሽቶ ይሸት ነበር" ብለውኛል።

"አንድ ክፍለ ሐገር ልናገለግል ሔደን" ይላል ሐዋሪያው ንጉሴ ሮባ "በሔድንበት ቀን የቅዳሜ ገበያ ቀን ነበር ሰው ኮንፍራንሱ ላይ አልተገኘም፤ እኛ ምን እናድርግ እያልን ስናስብ ዘውዴ እያፏጨ ወደ ገበያው ሮጠ ብታምንም ባታምንም እያፏጨ ሲመለስ አብረውት ገበያ ውስጥ የነበሩ ሰዎች ተከትለውት መጡ፡፡" ብሎኛል። ሐዋሪያው ዘውዴ በትምህርት ንቅናቄ አብሶ አቅጣጫ በእምነት አስተምሮ ዙሪያ በአገራችን የመጀመሪያው ሰው ነው፡፡ የመጀመሪያውም የተቃውሞ ገፈት ቀማሽ ነው፡፡ ሐዋሪያው ዘውዴ ከጽድቅ ውጪ ምንም እንደማይታየው ጌታንና ቅዱሳንን እንደሚወድ ብዙዎች ይናገራል፡፡ ስለ ራሱ ምንም መናገር አይፈልግም፡፡ ብዙ ሚዲያዎች ለቃለ መጠይቅ እንኳ ፈቃደኛ አይሆንም።

!!

" እኔ በመጀመሪያ ከዘውዴ ጋር ከመተዋወቃችን በፊት ስለ እርሱ እሰማ ነበር፡፡ በኃላ አንድ ቀን በአገልግሎት ላይ ተገናኘን " ይላል ፓስተር ታሪኩ ቴዎድሮስ " በዚያው ሰሞን ደግሞ ከመጋቢ ዮናስ ሰይፉ ጋር በአንድ የአዳር አገልግሎት ላይ ተዋወቅን ነበር ከዚያ ዘውዴን ጨምረን አንድ ፕሮግራም ለማድረግ ተነጋገርን። ለቤተክርስቲያን መሪዎች ስናሳውቅ አልተፈቀደም....ከዚያ ዘውዴም ለአገልገሎት ወደ ክፍለ ሐገር ሔደ፡፡ በመሐል ሾኔ ላይ የሚደረግ ብዙ ሰው የሚገኝበት አንድ ኮንፍራንስ ነበር ፤ እዛ ላይ ብዙ ሰዎች እነ ወንጌላዊ ገብሩ ወልዱ፤ ወንጌላዊ ዳንኤል ጣሰው ወዘተ ያገለግሉ ነበር፡፡ እዛ ላይ እኔ አገለገልኩ በዚያው ምሽት የቤተክርስቲያናችን መሪ ፓስተር መርዕድ ፕሮግራሙን መጣና የጠየቅነውን ፕሮግራም እንድንጀምር አናገረኝ፡፡ በጣም ደስ አለኝ፤ ከዚያም ለሰይፉ ነገርኩት ፤ ዘውዴም ሲመጣ ነገርነው፤ የቀጠና ሁለት የፈውስ ፕሮግራም ተጀመረ..

ሐዋሪያው ዘውዴ መጋቢ ታሪኩ ቴዎድሮስ እና መጋቢ ዮናስ ሰይፉ ከቤተክርስቲያ ተረክበው አስከ አሁንም ድረስ ያለውን የቅዳሜ የቀጠና ሁለት ሙሉ ወንጌል የፈውስ ፕሮግራም ተጀመረ፡፡ ያኔ የተጀመረው የቀጠና ሁለት ሙሉ ወንጌል የቅደሜ ጠዋት የፈውስ ፕሮግራም ላይ፥ ብዙዎች ይፈወሱ ፤ ብዙዎች ነጻ ይወጡ ፤ ብዙዎች ጌታ ይቀበሉ፥ ብዙዎች በመንፈስ ቅዱስ ይሞሉ ነበር። አስደናቂ መልዕክቶች ይመጡ ነበር ድንቅ። የአምልኮ ፕሮግራሞች ይደረጉ ነበር፡፡ በዚህ አገልግሎቱ ሐዋሪያው ዘውዴ ካለው መፅሐፍ ቅዱስ መረዳት በተጨማሪ የፈውስ፤ የመገለጥ ፤ መንፈስ ቅዱስን ሰዎች እንዲሞሉ ይጸልይ ነበር ብዙዎች በመንፈስ ቅዱስ ይሞሉ ነበር። በሐይል ያገለግል ነበር፡፡ አብረውት በፓስተር ታሪኩና ከፓስተር ዮናስ ጋር እየተቀባበሉ ያገለግሉ ነበር፡፡ ሐዋሪያው ዘውዴ የተለየው ባህሪው ብዙዎች የሚረዱት ባይሆንም ለጌታ ያለው ፍቅር ፤ እንዲሁም የመለኮት እጅ ግን በላዩ በከበደ ሁኔታ ይገለጥ ነበር፡፡ በጽድቅ በቅድስናው የተመሰከረት አገልጋይ ነው፡፡ " በሞራል ሆነ በገንዘብ ከሰዎች ጋር ባለው ጉዳይ እንከን አይገኝበትም" ይላል መጋቢ ታሪኩ ቴዎድሮስ፡፡

፨ የንባብ ህይወቱ

ሐዋሪያው ዘውዴ በጣም አንባቢ እንደሆነ ብዙዎች ይናገራሉ፡፡ ሐዋሪያው ዘውዴ በዚያ ዘመን የወጡ መንፈሳዊ መጽሔትና መጽሐፍት አማርኛና እግሊዝኛ በሙሉ ያነብ ነበር፡፡ እንደ ሰማሁት ለሬማ አገልግሎት መሰረት የጣለለት የተባለው የኬኒት ኢ ሔገን ሚኒስትሪ "Word of faith" የተባለው ወርሃዊ መጽሔትና እንደሆነ ይነገራል፡፡ አንባቢ መሆኑ የህይወቱን አቅጣጫ እንዲቀይር አድርጎታል፡፡ ቤቱ በመጽሐፍት የተሞላ ከመሆኑም በላይ ለብዙ ሰዎች መጽሐፍትን እንዲያነቡ በመግዛት በመስጠት ይታወቃል፡፡

፨ የቤት ህብረት አገልግሎቱ

ሐዋሪያው ዘውዴ የሬማ ቤተክርስቲያንን ከመትከሉ በፊት እንዳንድ ቦታዎች አብሶ የቤት ህብረት አገልግሎቶች ላይ ብዙ ወጣቶችን ያነቃቃ ትምህርቶችን ያስተምር ነበር፡፡ በተለያዩ ቤት ህብረቶች ላይ ብዙ አገልግሏል። ፓስተር ክንፈገብርኤል በቤት ለቤት አገግሎቱ ተጠቃሚ እንደሆነ አጫውቶኛል። የቀድሞ የሙሉ ወንጌል ቤተክርስቲያን መጋቢና ሐዋሪያው ዘውዴን ወደ ቀጠና ሁለት አገልግሎት እንመጣ ካደረጉት መሐል ፓስተር መርዕድ ናቸው። ፓስተር መርዕድ ሲናገሩ "ሐዋሪያው ዘውድ ብዙ ወጣቶችን ለአገልግሎት ያነሳሳ አገልጋይ ነው። በዚያ ዘመን ያገለግላቸው የነበሩ ወጣቶች አሁን ብዙዎቹ አገልጋዮች ናቸው" ብለውኛል።

፨የሬማ አገልግሎት
በ1987 የሬማ ቤተክርስቲያንን በጀመረ ጊዜ በጣም ብዙ ወጣቶች በትምህርቱ ተማርከው ነበር፡፡ ሬማ የመጀመሪያ በፍትህ ሚኒስቴር ላይሰንስ ያወጣ በባለራዕይ የተተከለ ቤተክርስቲያን ነው፡፡ በዚያ ዘመን ሬማ በሐገር አቀፍ አልፎም አስመራና፣ ካርቱም ሱዳን ውስጥ ሁሉ ሰፎቶ ነበር፡፡ ሐዋሪያው ዘውዴ በኢትየጵያ ቤተክርስቲያን የእምነት አገልግሎት ጀማሪና ፈር ቀዳጅ እንዲሁም ብዙ ስድብና የቅዱሳን ማጥላላት በህይወቱ ያለፈበት የመጀመሪያውን ዱላ ቀማሽ ማለት ይቻላል፡፡ በአሁን ሰአት የእምነት አገልግሎት የሚያስተምሩ ድሮ እርሱ ሲሰብክ የተሰደባበቸውን ትምህርቶች አሁን በነጻነት የሚያስተምሩ ብዙ ቤተክርስቲያናትና አገልጋዮች አሉ፡፡ በዚያ ዘመን በወጣቱ መሐል አብሶ በትምህርት ንቅናቄ ያመጣ የሐዋሪያው ዘውዴ አገልግሎት ነው፡፡ ሐዋሪያው ዘውዴ ላይ ሰልፍ ካመጡበት ነገሮች መሐል "Man is the spirit" ሰው መንፈስ ነው የሚለው አስተምሮት ነው፡፡ በዚያ ዘመን የሐዋሪያው ዘውዴ ተማሪ የነበረ አንድ ወንድም እንደነገረኝ " ብዙዎቹ ወጣቶች ሙሉውን ትምህርት ሳይማሩ የትምህርቱን ሐሳብ በተሳሳተ ነገር ተረድተው ስለነበር ነው ስደቱ የመጣው" ብሎኛል። ብዙዎቹ በዚያ ዘመን የነበሩ ሰዎች ሐዋሪያው ዘውዴ ያስተማረውን ትምህርት በስህተት ያስረዱ ስለነበር ችግሩ ተፈጥሮአል ይላሉ።

የሐዋሪያው ዘውዴ አገልገሎት ለብዙ ወጣት ባለራዕዮች ፈር ቀዳጅ ነበር ማለት ይቻላል፡፡ ከዚያ በኃላ ለተነሱ ድፍረት የሰጠ ነው፡፡ አሁንም ላሉ አገልጋዮች ዘንድም ሐዋሪያው ዘውዴ እንደምሳሌ የሚታይ ነው፡፡ ሐዋሪያው ዘውዴ የእምነት አገልግሎት ያስተዋወቀን በመንፈስ ቅዱስ አገልግሎት አስገራሚ ልምምድ የገለጠ ፤ ሰዎችን በመንፈስ ሐይል በመሙላት፥ የሚታይ የፈውስ አገልግሎቱ ፤ ወንጌልን በየስፍራው እየሔደ የሚሰብክ ፤ እንደዚሁም መጸለይ የህይወቱ መርህ እንደሆነ ይነገራል።

አንድ ከእርሱ ጋር በቅርበት የሚያገለግል መጋቢ " ሐዋሪያው ዘውዴን በስብዕናው ከሚያውቁት ይልቅ የተረዳውን መረዳት የተረዱ ጥቂት ሰዎች ቢኖሩ ኖሮ ምድሪቱ ላይ ታላቅ ለውጥ ይመጣ ነበር" ብሏል፡፡

፨የወንጌል ሰባኪነት አገልግሎቱ

ሐዋሪያው ዘውዴ አስተማሪ፤ የሐይል አገልጋይ፤ ብቻ ሳይሆን የወንጌል አገልጋይም ነው። አሁን ከሚኖርበት እንግሊዝ አገር እየተመላለሰ በየገጠሩ እየሆነ ወንጌልን ይሰብካል። ወንጌልን መስበክ ለእግዚአብሔር የምናደርግለት ውለታ ሳይሆን የምንኖርለት ስራችን ቢሆንም፤ ያንን በታማኝነት ማድረስ ግን መሰጠትን ይፈልጋል። ለገበሬዎች ላልተማሩ ገጠር ድረስ በመሔድ ወንጌልን ይሰብካል።

፨በመንፈስ ቅዱስ ምሪት ለአንድ ሰው መላክ

እግዚአብሔር ለአንድ ሰው ብቻ ሊልክህ ይችላል
የእግዚአብሔር የምንጊዜም ጉዳዩ ሰው ነውና። እግዚአብሔር አንድን ሰው ብቻ ሊለውጥ ትልቅ ፕሮግራም እንድታዘጋጅ ሊያደርግህ ይችላል። የሐዋሪያው ዘውዴ በጣም የሚገርመኝ አገልግሎቱ መንፈስ ቅዱስ ከላከው አንድ ሰውን ለማገልገል አገርን ብቻ ሳይሆን አህጉርን አቋርጦ ይሄዳል።

ሐዋሪያው ዘውዴ ካሉት፥ በምስክርነት ከሰማኃቸው ነገሮች መሐል አንድ ሰው ለማገልገል ብቻ ከአንድ ሐገር ወደ አንድ ሐገር ይሄዳል። ለዛ ጉዳይ ብቻ። ለአንድ ሰው ብቻ። በአንድ ወቅት አሜሪካ ውስጥ ላለ በካንሰር ለተያዘ ሰው መንፈስ ቅዱስ ሂድና ጸልይ አለው። ከእንግሊዝ ተነስቶ በራሱ ወጪ ለዛ ሰው አሜሪካን ሐገር ሔዶ ጸለየ።
መጋቢ ሜሮን ወልደሐዋሪያት የሐዋሪያው ዘውዴ መንፈሳዊ ልጅ ሲነግረኝ ተመርቶ ለማገልገል አውስትራሊያ ድረስ ሄዷል ብሎኛል።

በአንድ ወቅት በሳውዝ አፍሪካ ስላደረገው አግልግሎቱ ሰምቻለሁ። ሳውዝ አፍሪካ ሲያገለግል አንድን ወጣት ልጅ በመገለጥ ወደ ጉባኤ እንዲወጣ አደረገው። ልጁ ከአህምሮ በሽታ ተፈወሰ። መልካም ጊዜ ሆነ። ከዚያም ሐዋሪያው ዘውዴ ወደ እንግሊዝ ሐገር ተመለሰ። ከተመለሰ በኃላ መንፈስ ቅዱስ "ተመለስና ወደ ሳውዝ አፍሪካ ሂድ፣ ያንን ልጅ ይዘህ እያስተማርክ እየጸለይክ ለሶስት ወር ያዘው" አለው። ተነስቶ ወደ ሳውዝ አፍሪካ ሄዶ ያንን አደረገ። መቶዎችን፣ ሺዎችን ማገልገል መልካም ነው አንድን ሰው ማገልገል ደግሞ መታመን ነው። ይህ ትውልድ ከፊቱ ሊማርባቸው የሚችላቸው የእግዚአብሔር ሰዎች አሉት። ከህይወታቸውና ከአገልግሎት ተምሮ አገልግሎቱን ማስቀጠል ይችላል።

(ይህ ጽሑፍ የተዘጋጀው የዛሬ ሶስት አመት ሲሆን ጥቂት ሐሳቦችን ጨምሬ እንደገና ጻፍኩት)...
ሌሎች ጽሑፎቼን ለማግኘት የቴሌግራም ቻናሌን ይቀላቀሉ
https://t.me/theideaofs

23/09/2021

“.... ስሙም ድንቅ መካር፥ ኃያል አምላክ፥ የዘላለም አባት፥ የሰላም አለቃ ተብሎ ይጠራል።”
— ኢሳይያስ 9፥6

Address

Rhema Faith Ministry
Addis Ababa

Telephone

+251916823934

Website

Alerts

Be the first to know and let us send you an email when Rhema FM Eth. /Apostolic Mission/ posts news and promotions. Your email address will not be used for any other purpose, and you can unsubscribe at any time.

Contact The Place Of Worship

Send a message to Rhema FM Eth. /Apostolic Mission/:

Share