29/08/2025
+ ቅዳሴ የማይችሉት ካህን +
ታሪኩ የኾነው በግብጽ ሀገር ነው። የተወሰኑ ምዕመናን ተሰብስበው ቀሲስ ዳንኤል ዮሐና የተሰኙትን ካህን ለሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ከሰሷቸው። የክሱ ጭብጥ "ካህኑ የቅዳሴውን ጸሎት በቅብጥ ቋንቋ ለማለት ተቸግረዋል፤ በአግባቡ በቃላቸው ማድረስ አይችሉበትም" የሚል ነበር። መቼም "ቅዳሴ መቀደስ አይችልም" የሚል ክስ በካህን ላይ ሲመጣ ከባድ ነውና፤ የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ቶማስ ጉዳዩን እንደሰሙ ካህኑ በአስቸኳይ እንዲመጡ መልእክት ላኩባቸው። ቀሲስ ዳንኤል ዮሐናም ጥሪው በደረሳቸው በማግስቱ ለጉዞው መዘጋጀት ጀመሩ። አህያቸውን እየጫኑ እያለም ባለቤታቸው በመንገድ ላይ ረሃብ ከጸናባቸው እንዲበሉት በሚል የጋገረችላቸውን ኅብስት በመሀረብ ጠቅልላ ሰጠቻቸው። ካህኑ ቀሲስ ዮሐናም ኅብስቱን ተቀብለው የሀገረ ስብከቱ መቀመጫ ወደ ሆነው አል-ሚኒያ ጉዞ ጀመሩ።
በመንገድ ላይ እየሄዱ ሳለም ሊቀ ጳጳሱ ሊጠይቁኝ ይችላሉ ብለው ያሰቧቸውን የቅዳሴ ክፍሎች በቅብጥ ቋንቋ እያዜሙ መለማመድ ጀመሩ። በዚህ ሁኔታ ተጉዘውም ወደ አል-ሚኒያ ደረሱ።
ቀሲስ ዳንኤል ዮሐና ወደ ሊቀ-ጳጳሱ ብጹዕ አቡነ ቶማስ ቢሮ ሲገቡ ግን ሊቀ-ጳጳሱ ባዩት ሁኔታ ተደናገጡ። ቀሲስ ዳንኤል በእጃቸው በመሃረብ የተጠቀለለ እና በደም የራሰ ኅብስት ይዘዋል። ሊቀ ጳጳሱም በመንገዳቸው ምን እንዳጋጠማቸው ቀሲስ ዳንኤልን ጠየቁ። ቀሲስ ዳንኤልም በትህትና መንፈስ ኾነው "በዚህ መሀረብ የተጠቀለለው ኅብስት ነው። በመንገድ እየመጣሁ እያለሁ ቅዳሴውን በቅብጥ ቋንቋ እየተለማመድኩ ነበር" ብለው መለሱ። ብጹዕ አቡነ ቶማስ በሁኔታው ተደነቁ። ለካስ በካህኑ ጸሎት ኅብስቱ የጌታችንን አማናዊ ቅዱስ ሥጋ ሆኖ ነበር።
ሊቀ ጳጳሱ የጌታችንን አማናዊ ቅዱስ ሥጋ በቦታው ለነበሩት ሰዎች ካቀበሉ በኋላ ወደ ቀሲስ ዳንኤል ዮሐና በመዞር "በሉ ወደመጡበት ቤተክርስቲያን ይመለሱ፤ ከዚህ ቀደም ሲያደርጉ እንደነበረው አገልግሎትዎን ይቀጥሉ" ብለው አሰናበቷቸው። እርሳቸውን ለመፈተን ተሰብስቦ የነበረውም ጉባዔ ተበተነ።
ምንጭ፦ “Mallawy’s Blessed Priest: The Late Hegumen Daniel Youhanna Maqa" by Fr. Youannis Kamal