በ ኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ ማኅበረ ጽዮን ጠቅላላ ማኅበር

በ ኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ ማኅበረ ጽዮን ጠቅላላ ማኅበር በስብከተ ወንጌል፣ በአብነት ት/ቤት ግንባታ ፣ በበጎ አድራጎት፣ በመንፈሳዊ ጉዞና በመሳሰሉት መንፈሳዊ አገልግሎቶችን የሚፈጽም ማኅበር ነው፡፡
(1)

25/08/2026

መንፈሳዊ ጉዞ ወደ ግሸን ደብረ ከርቤ

24/08/2026
24/08/2026

እውነተኛ የእግዚአብሔር ሰዎች ተዓምርን ማድረግ ነፍሳቸው እጅግ ትፀየፈዋለች።

23/08/2026

ትኬቶቹን በተጠቀሱት አድራሻዎች ያገኛሉ። ለበለጠ መረጃ በእነዚህ ስልክ ቁጥሮች ይደውሉ።

+251935997957
+251911628039
+251 92 489 5702

ነሐሴ 30 ከቀኑ 7:00 በቦሌ መድኃኔዓለም እንገናኝ!

እንኳን አደረሰን!!!ድንግል ማርያም በእውነት ተነሥታለች ዐርጋለችም!!የአምላክ እናት ድንግል ማርያም በልጇ ሥልጣን ተነሥታለች ዐርጋለችም ሲባሉ ተናጋሪውንም እርሷንም በስድብ የሚያጥረገርጉ ሰ...
22/08/2026

እንኳን አደረሰን!!!

ድንግል ማርያም በእውነት ተነሥታለች ዐርጋለችም!!

የአምላክ እናት ድንግል ማርያም በልጇ ሥልጣን ተነሥታለች ዐርጋለችም ሲባሉ ተናጋሪውንም እርሷንም በስድብ የሚያጥረገርጉ ሰዎች ቁጥር ቀላል አይደለም:: የአምላካችን እናት የሆነች እርሷን ሲሳደቡ መስማት በእውነት ያማል:: ልበ አምላክ ክቡር ዳዊት ስለ ልጇ " የቤትህ ቅንአት በልታኛለች የሰደቡህም ስድብ በላዬ ወድቋል።" እንዳለ እውነተኛ ክርስቲያኖች የአማናዊት ቤቱ የድንግል ማርያም ቅንአት ትበላቸዋለች የሚሰድቧትም ስድብ በላያቸው ይወድቃል:: (መዝ 68(69)፥8) ጌታችን በወንጌል እንኳን የእናቱ የምእመናን መራብ የእርሱ መራብ፤ የእነርሱ መጠማት የእርሱ መጠማት፤ የእነርሱ መታረዝ የእርሱ መታረዝ እንደሆነና እነርሱንም ማሳደድ እርሱን ማሳደድ እንደሆነ ተናግሯል። (ማቴ 25፥42፣ የሐዋ 9፥1-9)

የእመቤታችንን የሞት የትንሣኤና የዕርገት ታሪክ ለጊዜው እናቆየውና ትንሣኤዋን በተመለከተ መጽሐፍ ቅዱስንና አዋልድ መጻሕፍትን መሠረት አድርገን አንድ እንበል ከዚያ በፊት ግን :-

+++ ስለምንጮቻችን +++

መጽሐፍ ቅዱስ ብቻ (solascriptura) የሚሉ ክፍሎች መጽሐፍ ቅዱስ ብቻ ይላሉ እንጂ መጽሐፉ የሚላቸውን አይሰሙም መስማትም አይፈልጉም:: "እርሱን ብቻ" ያሉት ታላቅ መጽሐፍ በመጽሐፍ ቅዱስ ተሟልተው ያልተጻፉ አያሌ ታሪኮች እንዳሉና ቀሪ ታሪኮችን ለማግኘት ሌሎች መጻሕፍትን ማንበብ እንደሚገባ ይነግሩናል:: ለምሳሌም የሰሎሞንን ታሪክ በስፋት የነገረን መጽሐፈ ነገሥት የሰሎሞንን ታሪክ ተርኮ ሲያጠናቅቅ "የቀረውም የሰሎሞን ነገር ያደረገውም ጥበቡም እነሆ በሰሎሞን ታሪክ መጽሐፍ ተጽፏል።" ይለናል። (1ኛነገ 11፥41 በዚህ ክፍል የሰሎሞንን ነገር (ነገረ ሰሎሞን) ያደረገውን ተአምራቱን የተሰጠውን ጥበብ አብራርቶ አስፍቶ የሚናገር የሰለሞን ታሪክ የሚባል መጽሐፍ እንዳለ እንረዳለን:: ስለ ዳዊትም "የንጉሡም የዳዊት የፊተኛውና የኋለኛው ነገር እነሆ በባለ ራእዩ በሳሙኤል ታሪክ በነቢዪም በናታን ታሪክ በባለ ራእዩም በጋድ ታሪክ ተጽፏል።" ይላል። (1ኛዜና 29፥29) ሰዎቹ ይህን ማንበብም ሆነ መስማት ባይፈልጉም መጽሐፉ ግን የዳዊትን ነገር ለመረዳት የሳሙኤልን፣ የናታንና የጋድን የታሪክ መጻሕፍት አንብቡ ይለናል:: ሁሉን ዘርዝሮ በመግለጽ ነገር እንዳናረዝም በመጽሐፍ ቅዱስ የተጠቀሱና እንድናነባቸው የተጠቆምናቸውን የሚከተሉትን መጻሕፍት እንጥቀስ

☞ እግዚአብሔር የጦርነት መጽሐፍ (ዘኁ 21፥14)
☞ የአዶ ራእይ (2ኛዜና 9:29)
☞ የነቢዩ ሸማያና የአዶ የትውልድ ታሪክ መጽሐፍ (2ኛ ዜና 12፥15)
☞ የሜዶንና የፋርስ ነገሥታት ታሪክ (አስቴር 10፥2)

በሐዲስ ኪዳንም ቢሆን ጌታችን የፈጸማቸው ተአምራቶች፣ ያስተማራቸው ትምህርቶች በሙሉ ተጽፈው እንዳልተጠናቀቁ መጻሕፍት ይመሰክራሉ። (ዮሐ 10፥30፣ ዮሐ 21፥25)

ጌታችን ከትንሣኤው በኋላ ዐርባ ቀን ሙሉ ለደቀ መዛሙርቱ እየተገለጠ በምልክቶችና በተአምራት ጭምር እንዳስተማራቸው ተጽፏል። (የሐዋ 1፥1-6) የዐርባ ቀናቱ ትምህርቶች የት ደረሱ?

ቅዱስ ማቴዎስም የጌታችንን ከስደት መመለስና በናዝሬት ከተማ ያደገበትን ምክንያት ሲናገር "በነቢያት ናዝራዊ ይባላል የተባለው ይፈጸም ዘንድ ናዝሬት የምትባል ከተማ ኖረ።" (ማቴ 2:23) ይህን ትንቢት የተናገረው ነቢይ ማነው? ወንጌላዊውስ ከዬት አመጣው?

መጽሐፍ ቅዱስ ብቻ በማለት አዋልድ መጻሕፍትን የሚያብጠለጥሉ ምን ያህል ስሑታን ናቸው? ቅዱስ ጳውሎስም ሙሴን የተቃወሙት ጠንቈዮች "ኢያኔስና ኢያንበሬስ ናቸው" ብሏል። (2ኛጢሞ 3፥8፣ ዘጸ 7፥1-15) የሙሴን ታሪክ የሚተርከው መጽሐፍ ታሪካቸውን እንጂ ስማቸውን አይነግረንም ሐዋርያው ግን ስማቸውን ነገረን ከዬት አመጣው?

የያዕቆብ ወንድም ይሁዳ ሊቀ መላእክት ቅዱስ ሚካኤል ስለ ሙሴ ሥጋ ከዲያብሎስ ጋር እንደተነጋገረ ሲግልጽ "እግዚአብሔር ይገሥጽህ አለው እንጂ የስድብን ፍርድ ሊናገረው አልወደደም።" ይላል። (ይሁዳ 9) ሰይጣን የሙሴን ሥጋ በተመለከተ ያደረገው ነገር ምን ነበር? መልአኩስ ለምን ገሠጸው? ይህንስ ታሪክ ሐዋርያው ከዬት አመጣው?

እነዚህ ኃይለ ቃላት አባቶቻችን ሐዋርያት ሌሎች መጻሕፍትንና ትውፊተ አበውን በስፋት እንደተጠቀሙ ይነግረናል:: ጌታችንም በምሳሌና በምሥጢር ካስተማራቸው ትምህርቶች አብራርቶ ተርጉሞ ያለፋቸው እንዳሉ ሳይተረጉም ለመተርጉማን የተዋቸውም ትምህርቶችም አሉ። (ሉቃ 13፥6-9)

እግዚአብሔር ወልድ ኢየሱስ ክርስቶስ ያደረገው ነገር እያንዳንዱ ቢጻፍ ለተጻፉት መጻሕፍት ዓለም ራሱ አይበቃቸውም ነበር ተብሏል። (ዮሐ 20፥30) የሰሎሞን፣ የዳዊትና የሌሎችም ቅዱሳን ታሪክ ከመጽሐፍ ቅዱስ በሐሳብ በማይለዩ የታሪክ መጻሕፍት ከተጻፉ እነርሱንም እንድናነባቸው ከተነገረን፥ በእነዚህም መጻሕፍት እነዚህ አባቶች ያደረጉት ነገር ጥበባቸውም እንደተጻፈ ከተነገረን ድንግል ማርያም ያደረገችው ነገር ልደቷ፣ አስተዳደጓ፣ አሟሟቷና ትንሣኤዋንም የሚነግረንን መጽሐፍን ከማንበብ ማን ይከለክለናል?

መጽሐፈ አስቴር፣ መጽሐፈ ኢዮብንና መጽሐፈ ሩትን ያነበበ፥ አንብቦም ክብራቸውን የተረዳ መጽሐፈ ማርያምን ማንበብ እንዴት ይከብደዋል?

++ የመቅደሱ ታቦት በእውነት ተነሥታለች ++

የክርስቶስ እናቱ ድንግል ማርያም በ64 ዘመኗ የሥጋ ሞትን ቀምሳለች በልጇም ሥልጣን ሞትን ድል አድርጋ ተነሥታለች:: እንዲህ ሲባሉ "ተነሣች የሚል መጽሐፍ ቅዱስ ላይ አለ ወይ?" ብለው የሚጠይቁ ሰዎች አሉ:: እኛም ለጥያቄያቸው ቀጥታ መልስ ከመስጠት የክርስቶስ እናቱ እመቤታችን ክብር ይግባትና "ሞተች" የሚል በመጽሐፍ ቅዱስ አለን? ብለን እንጠይቃቸዋለን:: እንዲህ ሲባሉ ሰው ስለሆነች "ሞተች የሚል ማስረጃ አያስፈልግም ምክንያቱም ሰው ናትና ትሞት ዘንድ ግድ ነው" ሊሉ ይችላሉ። ቅዱሳት መጻሕፍትን በእምነት ለመረመረና ለተረዳ ግን እንኳን የእርሷን የሌሎችንም ቅዱሳን መጨረሻ መጽሐፍ ቅዱስ ወይም ዜና ገድላቸው ካልነገረን በእርግጠኝነት ቅዱስ እገሌ ሞቷል ብሎ መናገር እንደማይቻል ይገነዘባል:: ለምን ? ቢሉ በመጽሐፍ ቅዱስ መጨረሻቸው በሥጋ ሞት መወሰድ ያልሆነ ብዙ ቅዱሳን ሰዎች አሉና ነው:: ለምሳሌም:-

☞ የነቢዩ ሄኖክ መጨረሻ የሥጋ ሞት እንዳልነበር መጽሐፍ ሲነግረን "ሄኖክም አካሄዱን ከእግዚአብሔር ጋር ስላደረገ አልተገኘም እግዚአብሔር ወስዶታልና።" ይለናል:: (ዘፍ 5፥24) ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም የሄኖክን በሥጋ አለመሞትና ምክንያቱን ነግሮናል። (ዕብ 11፥5)

☞ በክህነቱ የጌታችን ምሳሌ የተባለ መልከጼዴቅ እንኳን ልደቱም ( ጅማሬው) ፍጻሜውም በዕብራውያን ዘንድ እንደማይታወቅ በመጽሐፍ ቅዱስም እንዳልተነገረን መጽሐፍ ይመሠክራል። (ዕብ 7፥4)

☞ ነቢዩ ኤልያስም በሞት ሳይወሰድ በእሳት ሠረገላ ወደ ሰማይ ወጥቷል። (2ኛነገ 2፥11)

☞ በሐዲስ ኪዳንም ወንጌላዊው ቅዱስ ዮሐንስ በሥጋ እንደማይሞት ጌታችን ተናግሮለታል። (ማቴ 16፥28፣ ዮሐ 21፥23) እነዚህ ቅዱሳን ሞተው የተነሡ ሳይሆኑ ሞተ ሥጋ ያላገኛቸው ናቸው። እመቤታችን ግን ሞታ በልጇ ሥልጣን ሞትን ድል አድረጋ ተነሥታለች:: የሄኖክ፣ የኤልያስ፣ የዮሐንስን አምላክ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን የወለደች ድንግል ማርያም ሞተ ሥጋ አግኝቷት ሞትን በልጇ ሥልጣን ድል አድርጋ ተነሥታለች ዐርጋለችም የሚለውን መቀበል ምን ይከብዳል?

+አቤቱ ወደ ዕረፍትህ ተነሥ አንተና የመቅደስህ ታቦት+
(መዝ 131፥8)

ልበ አምላክ ክቡር ዳዊት በዚህ ክፍል ስለ ክርስቶስ ልደት "እነሆ በኤፍራታ (ቤተልሔም) ሰማነው በዱር ውስጥም (በቤተልሔም ዋሻ በከብቶች በረት ) አገኘነው።" ይላል:: (ሚክ 5፥2፣ መዝ 131፥6) ስለ ስቅለቱም " ወደ ማደሪያዎቹ እንገባለን እግሮቹ በበሚቆሙበት ሥፍራ (በመስቀሉ) እንሰግዳለን" ቁ ፯ ይልና አስከትሎም ስለ ትንሣኤው ሲናገር "አቤቱ ወደ ዕረፍትህ ተነሥ አንተና የመቅደስህ ታቦት" ይላል :: ነቢዩ ወደ ዕረፍትህ ተነሥ ያለው ጌታችንን መሆኑ ግልጽ ነው:: ዕረፍትህ ያለው ለምእመናን ዕረፍትን የሚሰጥባት ሰማያዊ መንግሥቱ ናት። (ዕብ 3፥11፣ 4፥1) ተነሥ ማለቱም የጌታችን ሞትን ድል አድርጎ መነሣት ያመለክታል:: ነቢዩ ሞትን ድል አድርገህ ተነሥ ያለው ጌታችንን ብቻ አይደለም "አንተና የመቅደስህ ታቦትም" አለ እንጂ:: አዎ የመቅደሱ ታቦትም ተነሥታለች!!

+++ የመቅደሱ ታቦት +++

የመቅደሱ ታቦት የተባለችው እናቱ ማደሪያው ድንግል ማርያም ናት:: እንዴት? ቢሉ ጌታችን ራሱን ቤተ መቅደስ ብሏል "ይህን ቤተመቅደስ አፍርሱት በሦስተኛውም ቀን አነሣዋለሁ....ስለ ሰውነቱም መቅደስ ይል ነበር።" ተብሏል። (ዮሐ 2፥19-21)

ታቦት ማለት ቤተ አደረ ካለው የግእዝ ቃል የወጣ ሲሆን ትረጉሙም ማደርያ ማለት ነው:: "የመቅደስህም ታቦት ትነሣ" ማለትም "ማደርያህ፣ እናትህም ትነሣ" ማለት ነው:: እንደ እርሷ የወልድ ማደሪያ የሆነ ማነው? እርሷ እኮ እናቱ ማደሪያው በተዋሕዶ የተገለጠባት መዲናው መገለጫው ናት:: "የእግዚአብሔር ክብር ይገለጣል ሥጋ ለባሽ ሁሉ በአንድነት ያየዋል።" እንደተባለ እግዚአብሔር ወልድ የተገለጠባት ዙፋኑ ናት::(ኢሳ 40፥5) እርሱ ከእርሷ ተወልዷልና ወንጌላዊው "ቃልም ሥጋ ሆነ (ሰው ሆነ) ጸጋንና እውነትን (የባሕርይ ክብሩን፣ የነቢያት ትንቢትን) ተመልቶ በኛ አደረ።" ሲል ቅዱስ ጳውሎስም "የአብርሃምን ዘር ይዟል እንጂ የያዘው የመላእክትን አይደለም።" አለ:: (ዮሐ 1፥14፣ ዕብ 2፥14-16)

የታንሽዋ ታቦት ማደርያ ቤተ መቅደስ ነው:: "በሰማይ ያለው የእግዚአብሔር መቅደስ ተከፈተ የኪዳኑም ታቦት በመቅደሱ ታየ" እንዲል። (ራእይ 11፥19) አምላክ ሰው በሆነ ጊዜ ግን ራሱን "መቅደስ" ያለ ሰማይና ምድርን የሞላ እግዚአብሔር ወልድ ኢየሱስ ክርስቶስ ከአባቱ ሳይለይ በታናሽዋ ታቦት በእመቤታችን ማኅፀን ተወሰነ። (ኤር 23፥23፣ ኤፌ 4÷10)

መቅደስ እርሱ ሞትን ድል አድርጎ በሥልጣኑ እንደተነሣ ታቦቱ እናቱም በእርሱ በልጇ ሥልጣን ሞትን ድል አድርጋለችና ነቢዩ "አቤቱ ወደ ዕረፍትህ ተነሥ አንተና የመቅደስህ ታቦት" ብሎ ተናገረ "ከመ ትንሣኤ ወልዳ እንደ ልጇ ትንሣኤ " የተባለውም ለዚሁ ነው::

ቢትወደድ ወርቁ
ነሐሴ 2018 ዓ ም

Address

አራት ኪሎ ቱሪስት ሆቴል ወረድ ብሎ ንግድና ኢንዱስትሪ ህንፃ ፊት ለፊት በሚያስገባው ኮብልስቶን
Addis Ababa

Alerts

Be the first to know and let us send you an email when በ ኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ ማኅበረ ጽዮን ጠቅላላ ማኅበር posts news and promotions. Your email address will not be used for any other purpose, and you can unsubscribe at any time.

Contact The Place Of Worship

Send a message to በ ኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ ማኅበረ ጽዮን ጠቅላላ ማኅበር:

Shortcuts

Share