15/09/2026
ይህን “ተፍሲር” ተጠንቀቁት!!
በቅርቡ ሸህ መሀመድ ዘህረዲን በእነ ሀጅ መሀመድ ሳኒ ሀቢብ እውቅ የቁርአን ተፍሲር ላይ በፈፀሙት ድፍረት እየተነሳ ያለው ጉዳይ ቀለል ተደርጎ የሚታይ ሳይሆን በሃይማኖታዊ፣ በህግ እንዲሁም በስነ-ምግባር መመዘኛዎች ተቀባይነት የሌለውና ትልቅ ትኩረት የሚሻ አጀንዳ ነው።
አንድ ሰው የአቂዳ ወይም የትርጉም ልዩነት ካለው የመረጠውን ሃሳብ የሚያንጸባርቅበት መንገድ አለ።
ነገር ግን በመላ ሐበሻ የተውጣጡ ጉምቱ ዑለሞች ለአመታት የደከሙበትን እና በህዝብ ዘንድ ተቀባይነት ያለውን ታሪካዊ ስራ ሰርዞ፣ ደልዞ፣ ጨምሮና ቀንሶ የወሀቢይ አስተሳሰብን በሚያንጸባርቅ መልኩ መበረዝ በምንም መስፈርቶች ተቀባይነት የለውም።
ከሙያዊ እና ከስነ-ምግባር አኳያ: የሌላውን ባለሙያና አሊም ስራ ይዘት በመቀየር የራሱ አስመስሎ ማቅረብ የአእምሯዊ ንብረት ስርቆት (Plagiarism) ነው።
ከህግ አኳያ: የቅጂ መብትን (Copyright) መጣስ ትልቅ ወንጀል የሚያስጠይቅ አሰራር ነው።
ከኢስላማዊ መመሪያ እና ከሸሪዓ አንፃር: የኡለማዎችን ድካም ባለቤትነት ሳያከብሩ የመጽሐፍ ይዘትን መለወጥ "አማናን" መጣስ ሲሆን፣ በኢስላም ታሪክም ላይ በጁሃላ የተፈፀመ ትልቅ ነውርና ሌብነት ተደርጎ ይወሰዳል።
በመሰረቱ በሳቸው ደረጃ ያለ ጃሂል ዝቅ ብሎ እንዲማር እንጂ እንኳን የዐሊሞችን ልፋት "ማረም" የራሱን የቁርአን ተፍሲር ኪታብ ማዘጋጀት አለበት ብለንም እናምንም።
ከዚህ ውጪ የተፍሲሩ አዘጋጆች የማይደግፉትንና አጥፊ የሆነን የወሀቢይ ትርጓሜ በዋናው ሥራ ውስጥ አስገብቶ ቃላትንና አረፍተ ነገሮችን መበረዝና ኪታቡን በነፃ ማደል ግን በታሪክ እና በእስልምና ላይየተፈፀመ ውንብድና እንጂ ታሪክ ሰሪነት አይደለም።
የእውነተኛ ዐሊም እና ታሪክ ሰሪ አሻራው የሚለካው የራሱን ስራ ሰርቶ ሲያስረክብ እንጂ የሌሎችን ድካም እያበላሹ በመበረዝ አይደለም። ታሪክን ለመስራት የራሳችንን መንገድ መሄድ እንጂ የሌሎችን ታሪክና አሻራ ማፍረስ ጎደሎነትን ማመን ነው።
ይህን ጉዳዩንም በዝምታ አናየውም።