06/08/2025
መዝሙር 107
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹ ቸር ነውና፥ ምሕረቱ ለዘላለም ነውና እግዚአብሔርን አመስግኑ፤
² እግዚአብሔር ያዳናቸው፥ ከጠላቶች እጅ ያዳናቸው ይናገሩ።
³ ከምሥራቅና ከምዕራብ፥ ከሰሜንና ከባሕር፥ ከየአገሩ ሰበሰባቸው።
⁴ ውኃ በሌለበት ምድረ በዳ ተቅበዘበዙ የሚኖሩበትንም ከተማ መንገድ አላገኙም።
⁵ ተራቡ ተጠሙም፥ ነፍሳቸውም በውስጣቸው አለቀች።
⁶ በተጨነቁ ጊዜ ወደ እግዚአብሔር ጮኹ፥ ከመከራቸውም አዳናቸው
⁷ ወደሚኖሩበት ከተማ ይሄዱ ዘንድ የቀና መንገድን መራቸው።
⁸ ለሰው ልጆች ስላደረገው ተኣምራት ስለ ምሕረቱም እግዚአብሔርን ያመስግኑ፤
⁹ የተራበችን ነፍስ አጥግቦአልና፥ የተራቈተችንም ነፍስ በበረከት ሞልቶአልና።
¹⁰ በጨለማ በሞትም ጥላ የተቀመጡ፥ በችግር በብረትም የታሰሩ፤
¹¹ የእግዚአብሔርን ቃል ስለ ዐመፁ፥ የልዑልንም ምክር ስለ ናቁ፥
¹² ልባቸው በድካም ተዋረደ፤ ታመሙ የሚረዳቸውም አጡ።
¹³ በተጨነቁ ጊዜ ወደ እግዚአብሔር ጮኹ፥ በመከራቸውም አዳናቸው።
¹⁴ ከጨለማና ከሞት ጥላ አወጣቸው፥ እስራታቸውንም ሰበረ።
¹⁵ ለሰው ልጆች ስላደረገው ተኣምራት ስለ ምሕረቱም እግዚአብሔርን ያመስግኑ፤
¹⁶ የናሱን ደዶች ሰብሮአልና፥ የብረቱንም መወርወሪያ ቈርጦአልና።