Eotc-ጥንታዊ ስዕላተ አድህኖ

Eotc-ጥንታዊ ስዕላተ አድህኖ Contact information, map and directions, contact form, opening hours, services, ratings, photos, videos and announcements from Eotc-ጥንታዊ ስዕላተ አድህኖ, Religious organisation, Addis Ababa.

02/07/2023
+ ተአምረ ማርያምና አንዳንድ ጉዳዮች + (ክፍል አንድ) ተአምረ ማርያምን በተመለከተ ሲነሡ የነበሩ ጉዳዮችን መቼም ሁሉም ሰው ያውቃቸዋል፡፡ ከመቅድሙ ጀምሮ ‘እንዴት ድንግል ማርያም ከዓለም ...
25/12/2022

+ ተአምረ ማርያምና አንዳንድ ጉዳዮች +
(ክፍል አንድ)

ተአምረ ማርያምን በተመለከተ ሲነሡ የነበሩ ጉዳዮችን መቼም ሁሉም ሰው ያውቃቸዋል፡፡ ከመቅድሙ ጀምሮ ‘እንዴት ድንግል ማርያም ከዓለም አስቀድሞ ታስባ ትኖር ነበር ይባላል?’ ‘እንዴት ተአምርዋን የሰማ ሥጋውን ደሙን እንደተቀበለ ይሆንለታል ይባላል?’ ‘ለሥዕልዋ ያልሰገደ ከቆመበት ቦታ ይጥፋ የሚል እርግማን እንዴት በሐዲስ ኪዳን ይነገራል?’ ‘የድንግል ማርያም ባሪያዎች ለመሆን እንሽቀዳደም እንጂ 16ቱን ትእዛዛት በመጠበቅ አይደለም እንዴት ይባላል?’ የሚሉ ጥያቄዎች ከፕሮቴስታንቶች አንዳንዶቹ ሲያነሡ አይተናል፡፡ በዚህ ጽሑፍ የተነሡትን አንዳንድ ጥያቄዎች እንደመግቢያ እንመልከታቸውና በጉዳዩ ላይ ያለውን ዝርዝር ጉዳይና ዘላቂ መፍትሔ ደግሞ አስከትለን ለመዳሰስ እንሞክራለን፡፡

‘‘እንዴት ድንግል ማርያም ከዓለም አስቀድሞ ታስባ ትኖር ነበር ይባላል?’’ የሚለው ጥያቄ ማንም ቢያነሣው ላያስደንቅ ይችላል፡፡ ‘ጸጋ ብቻ’ /Sola gratia/ በሚል አስተምህሮ እግዚአብሔር አስቀድሞ የወሰናቸው ሰዎች ብቻ እንደሚድኑ የሚያምነውን አስተምህሮ /Predestinationን/ እንደ መሠረተ እምነቱ የሚያስተምር ፕሮቴስታንቲዝምን የሚከተሉ የካልቪን ተከታይ የሆኑ ሰዎች /በእርግጥ አንዳንዶቹ አሁን አንቀበለውም እያሉ ነው/ እንዴት ቀድማ ታስባ ትኖራለች የሚል ጥያቄ ሲያነሡ መስማት ትንሽ ያስገርማል፡፡ እኛ ባናምንበትም እንዲያው ድንግል ማርያም ሌላው ቢቀር እነርሱ የሚያምኑበት ‘የPredestination አካል’ የምትሆንበትን ዕድል እንኳን ሊኖር እንደሚችል ቢያስቡ ጥሩ ነበር፡፡

ምክንያቱም የመጀመሪያዋ ክርስቲያን እንደመሆንዋ የተመረጡ /elect/ ከሚሏቸው ውስጥ በመቆጠር እድልዋ ቀዳሚ ናትና ከዓለም አስቀድማ ልትታሰብ ትችል ነበር፡፡
በመሠረቱ እንኳንስ ድንግል ማርያም ማንኛውም ፍጡር በአምላክ ሕሊና ታስቦ ይኖር ነበረ፡፡ ይህም ከፍጡሩ ማንነት አንጻር ብቻ ሳይሆን ከእግዚአብሔር ሁሉን አስቀድሞ ማወቅ ጋር የተያያዘ ጽንሰ ሃሳብ ነው፡፡ እንኳን ድንግል ማርያም እኛ ለሁላችን እንኳን ‘ዓለም ሳይፈጠር፥ በፊቱ ቅዱሳንና ነውር የሌለን በፍቅር እንሆን ዘንድ በክርስቶስ መረጠን ፤ በበጎ ፈቃዱ እንደ ወደደ፥ በኢየሱስ ክርስቶስ ሥራ ለእርሱ ልጆች ልንሆን አስቀድሞ ወሰነን’’ ተብሎ ተነግሮልናል፡፡ ኤፌ. 1፡4

የድንግል ማርያም ጎልቶ የሚነገረው ስለ አንድ ምክንያት ነው፡፡ እግዚአብሔር ከዓለም አስቀድሞ የሰው ልጅን መውደቅ የሚያውቅ እንደመሆኑ የሰውን ልጅም እንዴት እንደሚያድነው ያውቃል፡፡ እንዴት እንደሚያድነው ከዓለም አስቀድሞ ካወቀ ደግሞ በማዳኑ ሥራ ውስጥ እጅግ ወሳኝ የሆነችውን ድንግል ማርያምንም ከዓለም አስቀድሞ ያውቃታል ማለት ነው፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስ ‘በክቡር የክርስቶስ ደም እንደ ተዋጃችሁ ታውቃላችሁ። ዓለም ሳይፈጠር እንኳ አስቀድሞ ታወቀ’ ብሎ ክርስቶስ በደሙ የሚያደርገው ቤዛነት ከዓለም መፈጠር በፊት እንደታወቀ ተናግሯል፡፡ 1ጴጥ. 1፡20 የክርስቶስ በከበረ ደሙ እኛን ማዳኑ ዓለም ሳይፈጠር ከታወቀ ከእርስዋ ሥጋና ደምን ነሥቶ የሚወለድባት ድንግል ማርያም በአምላክ ሕሊና የማትታሰብበት ምንም ምክንያት አይኖርም፡፡

በጉባኤ ኒቅያ ‘ጥበብ ጌታ ፈጠረኝ እግዚአብሔር የመንገዱ መጀመሪያ አደረገኝ’ የሚለውን አርዮስ የካደበት ምሳ. 8፡23 ላይ ያለው ቃል የተብራራው ‘ፈጠረኝ የሚለው ቃል የተዋሐደውን ሥጋ የሚያጠይቅ ነው’ (ወጥበብኒ ዘትብል ፈጠረኒ እግዚእ ያኤምር በእንተ ዘፈጠረ ለርእሱ ሥጋ በከርሰ ማርያም) ተብሎ ነው፡፡ /ሃይማኖተ አበው ዘቄርሎስ 76፡15/ ጥበብ ፈጠረኝ ማለትዋ ቅድመ ዓለም ሥጋን ስለመልበሱ የታወቀ መሆኑን የሚያስረዳ መሆኑ በኒቅያ ጉባኤ እንደ ማስረጃ ከቀረበ ድንግል ማርያም ከዓለም አስቀድሞ በአምላክ ሕሊና ታስባ ለመኖርዋም ትልቁ ማስረጃ ይኼው ጥቅስ ይሆናል፡፡ (ለዝርዝሩ ‘የብርሃን እናት’ ገጽ 324ን ይመልከቱ)

ኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ ያሳተመው የብዙ ምሁራን የነገረ ማርያም ጥናቶች ስብስብ መጽሐፍ ስለዚህ ጉዳይ እንዲህ ይላል፡፡ ‘Mariology is a new creation or, perhaps, a new way of looking at creation. For this reason, the idea arose quite logically that Mary was chosen in eternity to be the Mother of God, and She is associated with Wisdom, who says in Proverbs 8:23 : Ages ago I was set up, at first, before the beginning of the earth’ ‘ነገረ ማርያም አዲስ ፍጥረት ወይም (ምናልባት) ሥነ ፍጥረትን በአዲስ መንገድ መመልከቻ መነጽር ነው፡፡ በዚህም ምክንያት ማርያም የአምላክ እናት ለመሆን ቅድመ ዓለም የተመረጠች የመሆንዋ ሃሳብ ከበቂ አመክንዮ ጋር ይነሣል፡፡ እርስዋም ‘የመንገዱ መጀመሪያ አድርጎ ፈጠረኝ ፤ ምድርን ሳይፈጥር አስቀድሞ ከዓለም በፊት ሠራኝ’ ከምትለው ጥበብ ጋር ተያይዛ ትነሣለች’ /The Oxford Handbook of Mary, Oxford University, UK 2019 Press 2/

ሁለተኛው ጥያቄ ‘ተአምርዋን የሰማ ሥጋ ወደሙን እንደተቀበለ ይሆንለታል’ የሚለውን ቃል በመጥቀስ ‘እንዴት የክርስቶስ ሥጋና ደም ከተአምረ ማርያም ጋር ሊተካከል ይችላል?’ የሚል ጥያቄ ነው፡፡ ይህም ጥያቄ ከፕሮቴስታንት አቅጣጫ መነሣቱ በጣም አስገራሚ ነው፡፡ እኔ መረጃ አጥሮኝ ካልሆነ በቀር ከመቼ ወዲህ ነው አንድ ፕሮቴስታንት የሥጋ ወደሙ ተቆርቋሪ የሆነው? የአስተምህሮ ለውጥ ተደርጎ እንደሆነ አላውቅም፡፡ በብዙ ለዘመናት ጸንቶ እንደተቃወመው ግን ፕሮቴስታንቲዝም በክርስቶስ ሥጋና ደም አማናዊነት ጨርሶ አያምንም፡፡ ጌታችን ‘ይህ ሥጋዬ ነው ይህ ደሜ’ ነው ብሎ የሠጠውን ምሥጢረ ቁርባንም ‘አብሮ ከሚበላ የመታሰቢያ ማዕድነት ያለፈ ፋይዳ የለውም’ በሚል አቋም የፕሮቴስታንቱ ዓለም ከካቶሊክና ኦርቶዶክሱ ዓለም ጋር ሲሟገት የአምስት መቶ ዓመት ዕድሜውን እንዳሳለፈ ሁላችን የምንስማማባቸው የታሪክ መዛግብት ያስረዳሉ፡፡ እነርሱ እንደሚሉት ሥጋ ወደሙ ተራ የመታሰቢያ ማዕድ ከሆነ ደግሞ እውነትም ከመብላት መስማት የተሻለ ጥቅም አለውና ይህንን ቃል ሊቃወሙ የሚችሉበት መሠረት አይኖራቸውም፡፡

የተአምረ ማርያም መቅድም ግን ጉዳዩን የሚጀምረው ተአምርዋን መስማት ምንኛ ከሥጋ ወደሙ ያነሠ መሆኑን በመግለጽ ነው፡፡ ሰው ‘ሥጋውንና ደሙን ይቀበል ፤ ሥጋ ወደሙን ለመቀበል የሚከለክል የታወቀ ምክንያት ከገጠመው ግን ተአምርዋን ሰምቶ ይሒድ’ የሚለው ንግግር ሥጋ ወደሙን ለመቀበል የማይችል ሰው ተአምርዋን መስማት እንደሚችል ያስረዳል፡፡ ተአምረ ማርያም ከሥጋ ወደሙ እኩል ቢሆን ኖሮ ሰውዬውን ሥጋ ወደሙን ከመቀበል የከለከለው ምክንያት ተአምርዋንም ከመስማት ይከለክለው ነበር፡፡ ለምሳሌ ‘በአካል መጥተህ እንድታገኘኝ ነገር ግን በአካል ለመምጣት ከአቅም በላይ በሆነ ምክንያት ባትችል ቢያንስ በስልክ ደውልልኝ ፤ ከደወልህልኝ እንደ መጣህ እቆጥረዋለሁ’ ብለህ ለወዳጅህ ነገርኸው፡፡ ይህ ዓረፍተ ነገር በአካል መምጣትና በስልክ መደወልን እኩል ያደርጋል ማለት አይደለም፡፡

በአጭሩ ዓረፍተ ነገሩ ሥጋ ወደሙን ዘወትር በመቀበል ሕይወት የሚኖርን ክርስቲያን የሚመለከት ቃል ነው፡፡ ይህ ክርስቲያን ፍጹም መንፈሳዊ ሕይወትን እየኖረ እንዳለ ምስክር የሚሆነው ሥጋ ወደሙን ከመቀበል የሚከለክለው ደዌ ወይም የታወቀ ምክንያት እንጂ አልቆርብም የሚል የኃጢአት ሰበብ አይደለም፡፡ እንዲህ ላለው ትጉሕ ቆራቢ ሰው ሁልጊዜ ወደ ቤተ ክርስቲያን እየገሠገሠ መቁረብ ልማዱ ነውና አስቀድሶ አለመቁረብም ኀዘን ይሆንበታል፡፡ ለዚህ ሰው መቅድመ ተአምረ ማርያም ያጽናናዋል፡፡ ‘የታወቀ ምክንያት ወይም ሕመም ስለከለከለህ ባለመቁረብህ አትዘን ቢያንስ ተአምርዋን ሰምተህ ሒድ ፤ በዚያ ዕለት ልትቆርብ ተመኝተሃልና ሰምተህ በመሔድህ ያን ቀን ብትቆርብ የምታገኘውን በረከት አላስቀርብህም’ ነው፡፡ ይህ ግን ንስሓ አልገባም አልቆርብም ተአምርዋን ሰምቼ ይበቃኛል የሚል ብልጣ ብልጥ ትዕቢተኛ ሰው የሚሠራ አይደለም፡፡ ምክንያቱም ይህንን ዓይነቱን ሰው ከመቁረብ የሚከለክለው ‘የታወቀ ምክንያት ወይም ደዌ ሳይሆን’ የኃጢአት ፍቅር ነው፡፡

ሦስተኛው ጥያቄ ‘ለሥዕልዋ ያልሰገደ ከቆመበት ቦታ ይጥፋ የሚል እርግማን እንዴት በሐዲስ ኪዳን ይነገራል?’ ነው፡፡ ‘ለሥዕልዋ ስገዱ’ ማለት ለድንግል ማርያም ስገዱ ማለት ነው እንጂ እርስዋና ሥዕልዋን ነጣጥሎ ለማየት አይደለም፡፡ ምክንያቱም ቅዱስ ዮሐንስ ዘደማስቆ በእንተ ሥዕላት አምላካዊያት (On the Divine Images) ላይ ደጋግሞ እንደገለጸው በሥዕላት ፊት የሚደረግ ማንኛውም አክብሮትና ስግደት ለሥዕሉ ሳይሆን ለሥዕሉ ባለቤት ነው፡፡ ድርሳነ ሚካኤልም ‘ወሶበ ንሰግድ ቅድመ ሥዕላት አምላካዊያት አኮ ዘንሰግድ ለረቅ ወለቀለም ወለግብረ ዕድ’ ‘በእግዚአብሔር ሥዕል በተሳሉ በአምላካዊያት ሥዕላት ፊት ስንሰግድ የምንሰግደው ለወረቀቱ ለቀለሙ ወይንም ለሰው የእጅ ሥራ አይደለም’ ስግደትና ሥዕላትን በሚመለከት እነዚህን ቀደምት ጽሑፎች ይመልከቱ፡፡

‘በሐዲስ ኪዳን እንዴት እርግማን እንሰማለን’ የሚለው ተቃውሞ ‘እንዲህ የሚያደርግ መንፈስ የተወጋ ይሁን’ ‘ወግቼዋለሁ’ ሲሉ ከሚውሉ ሰዎች አቅጣጫ መነሣቱ አሁንም አስደናቂ ነው፡፡ ከዚያ ውጪ ጉዳዩ የሚረገመው አካልና እርግማኑ ተገቢነት ላይ እንወያይ እንጂ ሐዲስ ኪዳን ላይ ጨርሶ የግዝት ቃል ሥራ አቁሞአል ማለት አይቻልም፡፡ ጌታ በለስዋን ‘ለዘላለም ፍሬ አይገኝብሽ ብሏታል’ /ማቴ. 21፡19/ ሐዋርያት ‘ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን የማይወድ ቢኖር የተረገመ ይሁን’ ‘ነገር ግን እኛ ብንሆን ወይም ከሰማይ መልአክ፥ ከሰበክንላችሁ ወንጌል የሚለይ ወንጌልን ቢሰብክላችሁ የተረገመ ይሁን’ ብለዋል፡፡ /ገላ.1፡8፣9/ እግዚአብሔር አያሰማን እንጂ በዕለተ ምጽአትም ‘እናንተ ርጉማን’ የሚለው ቃል የመጨረሻው ቃል ነው፡፡ ይህ ዓይነቱ ቃል ተራ እርግማን ሳይሆን በድርጊቱ የተገኙትን ከክርስትና ኅብረት የሚለይ በምድር ያሰረችው በሰማይ የታሰረ የሚሆንላት ቤተ ክርስቲያን የምትናገረው ቃለ ውግዘት (በግሪኩ Anathema) ነው፡፡ ይህም በተስፋ የምንጠብቃት መንግሥተ ሰማያት እስክትመጣና ‘ከእንግዲህ ወዲህ መርገም ከቶ አይሆንም፡፡ የእግዚአብሔርና የበጉም ዙፋን በእርስዋ ውስጥ ይሆናል ባሪያዎቹም ያመልኩታል ፊቱንም ያያሉ’ የሚለው ቃል እስከሚፈጸምልን ድረስ የሚቀጥል ነው፡፡ (ራእ. 22፡3)

የመጨረሻው ነጥብ ‘የድንግል ማርያም ባሪያዎች ለመሆን እንሽቀዳደም እንጂ 16ቱን ትእዛዛት በመጠበቅ አይደለም እንዴት ይባላል?’ የሚለው ነው፡፡ መደጋገም ይሆንብኛል እንጂ አሁንም ጥያቄው ከእነርሱ መነሣቱ ያስደንቀኛል፡፡ ፕሮቴስታንቲዝም የትእዛዛት ተቆርቋሪ መሆን የጀመረው ከመቼ ወዲህ ነው? በማመን እንጂ ትእዛዝ በመጠበቅ አይዳንም በሚለው ትምህርት ምክንያት ስንት ውዝግብ አልተነሣም? ጳውሎስ የመገረዝን ሕግ ሥራ ለአሕዛብ ጽድቅ የግድ አስፈላጊ አይደለም ብሎ ያስተማረበትን ሮሜና ገላትያ ያለ አገባቡ በአጠቃላይ በጎ ሥራ አያፈልግም እንዳለ አድርገው በያዙት የተሳሳተ መረዳት ምክንያት በሰማይ በክብር አብረው የሚዘምሩትን ጳውሎስና ያዕቆብን ሳይጣሉ ያጣሏቸው እነርሱ አይደሉምን? አሁን ደግሞ ተአምረ ማርያምን ጎዳን ብለው እንዴት ትእዛዝ መፈጸም አያስፈልግም ትላላችሁ? ብለው ሲመጡ ማየት ምንኛ አስገራሚ ነው?

በመሠረቱ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን እነሱ እንደሚሉት ሥራ ብቻውን ያጸድቃል ብላ አምና አታውቅም፡፡ ልጆችዋንም እኔ በጎ ሥራ አለኝ በእርሱ እጸድቃለሁ ብለው እንዳያስቡ ታስጠነቅቃለች፡፡ ጸሎትዋም መዝሙርዋም ‘ምግባር የለኝም’ ነው፡፡ ‘እንበለ ምግባር ተራድእኒ ፍጡነ ፤ ምግባርየሰ ኃጢአተ ኮነ’ ‘እንበለ ምግባር ባሕቱ እመ ኢይጸድቅ አነ ፤ ቦኑ በከንቱ ኪዳንኪ ኮነ’ ‘በምን ምግባሬ ፊትሽን አየዋለሁ’ ‘እኔስ በምግባሬ ደካማ ሆኜያለሁ’ ወዘተ የሚሉት እልፍ ምስጋናዎች ቤተ ክርስቲያን ልጆችዋ በምግባሬ እጸድቃለሁ ብለው ተስፋ እንዳያደርጉና በክርስቶስ በማመናቸው (በሥጋ እንደመጣና ከድንግል ማርያም እንደተወለደ ማመንን ይጨምራል) እና በእግዚአብሔር ጸጋ ወይም ቸርነት እንደሚጸድቁ (እምነት + ሥራ + ጸጋ) ታስተምራለች፡፡

የድንግል ማርያም ባሪያዎች ለመሆን እንሽቀዳደም መባሉ የሚያበሳጨው ካለ መጽሐፍ ቅዱስ ‘ነገር ግን በፍቅር እርስ በእርሳችሁ እንደ ባሪያዎች ሁኑ’ ይላል፡፡ ገላ. 5፡13 እንኳንስ ለአምላክ እናት አጠገብህ ላለው ወንድምህም በፍቅር ባሪያ ብትሆን ትጠቀማለህ እንጂ አትጎዳም፡፡ ለድንግል ማርያም ባሪያዋና ታዛዥዋ ብትሆን ግን ብዙ ትጠቀማለህ፡፡ ክርስቲያኖች ሆይ ልንገራችሁ ሁሉን ትታችሁ ለድንግል ማርያም ብቻ ታዘዙ፡፡ የእርስዋ ትእዛዝ አንድ ነው ‘የሚላችሁን ሁሉ አድርጉ’ ዮሐ. 2፡5


+ ተአምራትን እንዴት እናያቸዋለን? +

መጽሐፍ ቅዱስ ‘የሐዋርያት ሥራ’ን የመሰሉ ሰዎች በእግዚአብሔር ኃይል የሠሩትን ሥራ የሚተርኩ መጻሕፍት ያለበት መጽሐፍ ነው፡፡ ‘የእግዚአብሔርን ቃል የነገሯችሁን ዋኖቻችሁን አስቡ የኑሮአቸውን ፍሬ እየተመለከታችሁ በእምነታቸው ምሰሏቸው’ በማለት ሕያዋን መጽሐፍት ወይም ተንቀሳቃሽ መጽሐፍ ቅዱስ /Living bible or moving bible/ ተብለው የሚጠሩትን የቅዱሳንን ሕይወት እንድናጠና እና በኑሮአቸው እንድንመስላቸው ያሳስበናል፡፡ (ዕብ. 13፡7) ቅዱስ ጳውሎስ ‘እኔ ክርስቶስን እንደምመስል እናንተም እኔን ምሰሉ’ ብሎ እንደነገረን ክርስቶስን ለመምሰል የጳውሎስን የሕይወት ታሪክ ማጥናት የግድ አስፈላጊ ነው፡፡ (1ቆሮ. 11፡1) ራሱ ጳውሎስም ከእርሱ የቀደሙ የእምነት አርበኞችን አስደናቂ ታሪክ ከዘረዘረ በኋላ ‘ሁሉን እንዳልተርክ ጊዜ ያጥርብኛል’ ብሏል፡፡ (ዕብ. 11፡32) ጳውሎስ የቅዱሳኑን ታሪክ ለመተረክ ያጠረው ጊዜ እንጂ ፍቅር አልነበረም፡፡

እግዚአብሔር በቅዱሳኑ አድሮ ያደረገውን መስማትም የቅዱሳን ታሪክ አካል ነው፡፡ ‘በሐዋርያት እጅ ብዙ ድንቅና ምልክት ተደረገ’ ‘እግዚአብሔርም በጳውሎስ እጅ የሚያስገርም ተአምራት ያደርግ ነበር’ እንደሚል እግዚአብሔር በባሪያዎቹ እጅ ታላላቅ ተአምራት ያደርጋል፡፡ (ሐዋ. 2፡42 ፣ 19፡11) የእስራኤል ንጉሥ ‘ኤልሳዕ ያደረገውን ተአምር እስቲ ንገረኝ’ እያለ ግያዝን እየጠየቀ በደስታ ይሰማ እንደነበረ የእግዚአብሔር ቅዱሳን ያደረጉትን ተአምር መስማት ለምናምን ሰዎች እጅግ ደስ የሚያሰኝ ነገር ነው፡፡ (2ነገሥ. 8፡4)

እግዚአብሔር ሁሉን ቻይ ነውና እሱ ያደረገው ተአምር ምንም ቢሆን ከከሃሊነቱ አንጻር የሚጠበቅ ነገር ነው፡፡ ለደካማው የሰው ልጅ ኃይል ሠጥቶ የሚሠራውን ነገር ስንሰማ ግን ኃይሉ በሰው ድካም ሲገለጥ ስናይ የበለጠ እናደንቃለን፡፡ የቅዱሳን ተአምር መቼም ቢደረግ በእግዚአብሔር እጅ የተደረገ ነው፡፡ ‘ሁሉ በእርሱ ሆነ ከሆነውም አንዳችስ እንኳን ያለ እርሱ አልሆነም’ እንደሚል ድንግል ማርያም ያደረገችው ተአምር ሁሉ በእርሱ የተደረገ ነው፡፡ ተአምረ ማርያምም ራሱ ተአምረ ኢየሱስ ነው፡፡ እግዚአብሔር በድንግል ማርያም ተአምር ይሠራል ፤ ያለ ድንግል ማርያምም ተአምር ሊያደርግ ይችላል፡፡ ድንግል ማርያም ግን ያለ እግዚአብሔር አንዳች ተአምር ልትሠራ አትችልም፡፡ ክርስቶስ ‘ያለ እኔ ምንም ልታደርጉ አትችሉም’ ያለው ለዚህ ነው፡፡ (ዮሐ. 15፡5)

ኦርቶዶክሳዊያን ስለ ድንግል ማርያም ወላዲተ አምላክዋን ፣ ዘለዓለማዊ ድንግልዋን ፣ መቼም መች መርገም ያልደረሰባት ንጽሕት መሆንዋ ፣ አማላጅነትዋን እናምናለን ፤ ከዚህ ፈቀቅ ሊያደርገን የሚሻ ቢኖርም እነዚህ የነገረ ማርያም መሠረተ እምነቶቻችን ናቸውና እስከ ሰማዕትነት ድረስ እንጸናለን፡፡ መድኃኔዓለም ክርስቶስ ‘እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ በእኔ የሚያምን እኔ የማደርገውን ሥራ እርሱ ደግሞ ያደርጋል፤ ከዚህም የሚበልጥ ያደርጋል’ ‘የሰናፍጭ ቅንጣት የሚያህል እምነት ቢኖራችሁ፥ ይህን ተራራ፦ ከዚህ ወደዚያ እለፍ ብትሉት ያልፋል፤ የሚሳናችሁም ነገር የለም’ ብሎ ተናግሯል፡፡ (ዮሐ. 12፡14 ፤ ማቴ. 17፡20) ስለዚህ ‘ያመነች ብፅዕት’ የተባለችው ድንግል ማርያም (ሉቃ. 1፡45) በልጅዋ አነጋገር ክርስቶስ የሚያደርገውን ተአምር ታደርጋለች ፣ ከዚያም የሚበልጥ ታደርጋለች ፣ የሚሳናትም የለም፡፡

ተአምራትን የሚያነብ ሰው በእምነት ካላነበበው ብዙ መቸገሩ የማይቀር ነው፡፡ እውነት ለመናገር ይህ ከክህደት የተነሣ ብቻ ሳይሆን ከመንፈሳዊነት ደረጃችን ዝቅ በማለታችን የተነሣ የሚፈጠር ችግር ነው፡፡ በተአምራት መጻሕፍት ላይ ተደረጉ የሚባሉ ተአምራትን በእርግጠኝነት የሚያምን ልብ ቢኖረን ኖሮ ተአምራቱን እኛ ራሳችን ልንፈጽማቸው በቻልን ነበር፡፡ እኛ ግን እንኳንስ ተአምራቱን ልንፈጽማቸው ቀርቶ ተፈጽመዋል ብለን አምነን ለመቀበልም እንኳን ገና ነን፡፡ በዚህ የተነሣ የቅዱሳን ተአምራት ሲነበቡ ልባችን በጥርጣሬ ይናወጻል፡፡ ከኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን ውጪ ያሉ ሰዎች ደግሞ ተአምራት ሲሰሙ ‘አቤት ተረት’ ለማለት ተነቦ እስከሚያልቅ ድረስ አይጠብቁም፡፡

በገድላትና ድርሳናት ላይ ያሉ ታሪኮችንና ተአምራትን ተረታ ተረት ናቸው ብሎ ለመደምደም ከቸኮልክ መጽሐፍ ቅዱስንም ማመንህ አስገራሚ ይሆናል፡፡ ምክንያቱም መጽሐፍ ቅዱስም ብዙ ለማመን የሚከብዱ ታሪኮች አሉበት፡፡ እባብ ከሰው ጋር ሲነጋገር ፣ አህያ ጌታዋን ስትመክር ፣ ኤልያስ ዝናብን እንደ ቧንቧ ውኃ ሲከፍትና ሲዘጋ ፣ ቁራ አስተናጋጅ ሲሆን ፣ ኤልያስ በእሳት ሰረገላ ሲሳፈር ፣ ዮናስ በአሳ አንበሪ ሆድ ውስጥ ሲጸልይ ፣ የኤልሳዕ አጥንት ሙት ሲያስነሳ ፣ የኤልያስ ልብስ ባሕር ሲከፍል ፣ የሙሴ በትር እባብ ሲሆን ፣ ጌታ በምራቁ ዓይን ሲፈጥር ፣ የአራት ቀን ሬሳ በስም ተጠርቶ ሲወጣ ፣ የጴጥሮስ ጥላ ሲፈውስ ፣ የጳውሎስ ጨርቅ ሙት ሲያስነሣ ተጽፎ ታገኛለህ፡፡ ይሄንን ሁሉ እግዚአብሔር ሁሉን ማድረግ ይችላል ብለህ በእምነት ካልተቀበልከው በስተቀር እንዴት ታደርገዋለህ? አንድ አባት ‘ዮናስን አሣ አንበሪ ዋጠው የሚለውን ታሪክ እንዴት ማመን ይቻላል?’ ተብለው ሲጠየቁ ‘የምናወራው ስለ እግዚአብሔር ከሆነ እንኳንስ ዓሣ አንበሪው ዮናስን ዋጠው ተብሎ ይቅርና ዮናስ ዓሣ አንበሪውን ዋጠው ቢባልም አምናለሁ’ ብለዋል፡፡ ‘አይ ይኼ እኮ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተጻፈ ነው’ ካልከኝ እግዚአብሔር መጽሐፍ ቅዱስ ተጽፎ ሲጠናቀቅ ሥራ አቁሞአል ማለት ነው? ‘እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ከእናንተ ጋር ነኝ’ ሲል አብረን አልሰማነውም? (ማቴ. 28፡19)

ወደ ተአምረ ማርያም እንመለስና ለመሆኑ ተአምረ ማርያምን ማን ጻፈው? ከየት መጣ? ተአምረ ማርያም ላይ የሚነሡ ብዙ ጥያቄዎች ሁሉም የተሳሳቱ ናቸው ሊባል ይችላል? ብፁዓን አባቶች "ተአምረ ማርያም ላይ በሊቃውንት ጉባኤ በኩል ሥራዎች እየተሠሩ ነው" ሲሉ ምን ማለታቸው ነው? በቤተ ክርስቲያንዋ በኩልስ በአዋልድ መጻሕፍት ዙሪያ የሚነሡ ጉዳዮች የሉም? ሌሎች የሚያሳዩት ንቀትና ስድብ እንዳለ ሆኖ በአዋልድ በቤተ ክርስቲያንዋ እይታስ ምን እየተሠራ ነው? የዚህ ጽሑፍ ቀጣይ ክፍል ትኩረት ይሆናል፡፡

ክፍል ሁለት - ይቀጥላል
ዲያቆን ሄኖክ ኃይሌ
ታኅሣሥ 12 2015 ዓ.ም.

ለተጨነቀች ነፍስ ዕረፍት የሆነው የእግዚአብሔር ቃል ለሁሉ ይዳረስ ዘንድ :: እኔም ለእናንተ ከሰበክሁ በኁዋላ የተጣልሁ እንዳልሆን አጥብቃችሁ ስለ እኔ ጸልዩልኝ!
በኮሜንት መስጫው ሥር "ለሚሰሙት ጸጋን ይሰጥ ዘንድ፥ እንደሚያስፈልግ ለማነጽ የሚጠቅም ማናቸውም በጎ ቃል እንጂ [ዋጋን በምድር የሚያስቀር ውዳሴም ሆነ ሌላ] ክፉ ቃል ከአፋችሁ ከቶ አይውጣ" (ኤፌ 4:29)

እርገተ እግዚእነ ሃበ ደብረታቦር!!
08/12/2022

እርገተ እግዚእነ ሃበ ደብረታቦር!!

ምስለ ፍቁር ወልዳ !!
02/12/2022

ምስለ ፍቁር ወልዳ !!

ዮሴፍ ወ ኒቆዲሞስ ፆርዎ ስጋሁ ለ ክርስቶስ
02/12/2022

ዮሴፍ ወ ኒቆዲሞስ ፆርዎ ስጋሁ ለ ክርስቶስ

Address

Addis Ababa
33530

Website

Alerts

Be the first to know and let us send you an email when Eotc-ጥንታዊ ስዕላተ አድህኖ posts news and promotions. Your email address will not be used for any other purpose, and you can unsubscribe at any time.

Share