አኮቴት Akotet

አኮቴት Akotet እስትንፋስ ያለው ሁሉ እግዚአብሔርን ያመስግን" መዝ 150÷6

ሰኔ 12   ዓመታዊ በዓል!እንኳን ለመልአኩ ቅዱስ ሚካኤል ለእናታችን ቅድስት አፎሚያ አመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ ። ሰኔ 12 ቅዱስ ሚካኤል እናታችን ቅድስት አፎሚያን ከጠላት ዲያብሎስ ...
19/06/2022

ሰኔ 12 ዓመታዊ በዓል!

እንኳን ለመልአኩ ቅዱስ ሚካኤል ለእናታችን ቅድስት አፎሚያ አመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ ። ሰኔ 12 ቅዱስ ሚካኤል እናታችን ቅድስት አፎሚያን ከጠላት ዲያብሎስ እጅ ያዳነበት ፣ እናታችን ቅድስት አፎሚያ እረፍቷ ነው ።እግዚአብሔር ከቅዱሱ መላእክት ቅዱስ ሚካኤል ፣ ከእናታችን ቅድስት አፎሚያ በረከት ተካፋይ ያድርገን

👉 በወርኃ ሠኔ መታሰቢያ ከሚደረግላቸው ቅዱሳን መካከል እግዚአብሔርን የሚፈራ የአስተራኒቆስ ሚስት የሆነች የቅድስት አፎምያን ታሪክ በአጭሩ እንዳስሳለን

ቅድስት አፎምያ በትዳር በነበረችባቸው ዘመናት እግዚአብሔርን ከሚወድ ባለቤቷ ጋር እግዚአብሔርን ስታገለግለው የኖረች ሴት ነበረች፡፡ በየወሩ በ29 ቀን የጌታችንን የልደቱን፣ ወር በገባ በ21 የእመቤታችንንና ወር በገባ በ12 የቅዱስ ሚካኤልን መታሰቢያ እያደረጉ ነዳያንን ይጎበኙ እንደነበር ታሪካቸው ይነግረናል

ባለቤቷ አስተራኒቆስ ከዚህ ዓለም የሚያርፍበት ጊዜ እንደደረሰ ባወቀ ጊዜ ይሰጡት የነበረውን ምጽዋት እና የሦስቱን በዓላት መታሰቢያ ማድረግ እንዳታስታጉል ከአደራ ጋር አዘዛት፡፡ እሷም የመልአኩን የቅዱስ ሚካኤልን ሥዕል ያሥልላት ዘንድ ባለቤቷን ጠይቃ አሠርቶ ሰጣት፡፡ በከበረ ቦታም አኖረችው

ባሏ ካረፈ በኋላ ያዘዛትን መንፈሳዊ ሥራ ከወትሮው አስበልጣ መሥራት ቀጠለች፡፡ የሰው ልጆች ጠላት የሆነው ሰይጣንም በመልካም አገልግሎት ስትበረታ ባያት ጊዜ ዝም ብሎ ሊተዋት አልወደደም፡፡ በመጀመሪያ ባል ሳታገባ ማገልገሏን ትታ፣ ሌላ ባል አግብታ፣ ልጅ ወልዳ እንድትኖር በብዙ ማባበል ጠየቃት፡፡ ባሏ መንግሥተ ሰማያትን ስለወረሰ ምንም ምጽዋት እንደማይሻ አስመስሎ ነገራት

ቅድስት አፎምያ ግን ዳግመኛ ትዳር ላለመመሥረት ቃል ኪዳን እንደገባች ርግብንና ዖፈ መንጢጥን አብነት አድርጋ፤ እነሱ እንኳ በሕይወት ዘመናቸው ከአንድ ባል ውጪ ሌላ ባል እንደማያውቁ በመጥቀስ አሳቡን እንደማትቀበለው ገለጸችለት፡፡ ሰይጣንም አስመሳይ መሆኑ አላዋጣ ሲለው ማንነቱን ቀይሮ ሊያንቃት ቢሞክር የእግዚአብሔርንና የቅዱስ ሚካኤልን ስም ጠርታ አባረረችው፡፡ እሱም ተመልሶ መጥቶ እንደሚያጠፋት ዝቶባት እንደአቧራ በኖ፤ እንደ ጢስም ተኖ ጠፋ

በሠኔ ፲፪ ቀን የቅዱስ ሚካኤልን መታሰቢያ እያዘጋጀች ሳለች ሰይጣን ብርሃናዊ መልአክ መስሎ መጣ፡፡ የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤል እንደሆነ ገልጾ የመጀመሪያውን የመሰለ ከንቱ ምክሩን አሰማምሮ አቀረበላት፡፡ አሳቡንም የእግዚአብሔር ፈቃድና አሳብ እንደሆነ አድርጎ ለማሳመን ሞከረ፡፡ ሰይጣን አስቀድሞ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን በገዳመ ቆሮንቶስ መጻሕፍትን እየጠቀሰ እንደተፈታተነው ሁሉ ቅድስት አፎምያንም ለማሳመንም አብርሃምን፣ ይስሐቅን፣ ያዕቆብን፣ ዳዊትን የመሳሰሉ ደጋግ አባቶችን ታሪክ እየጠቀሰ ወደ ትዳር እንድትገባ ደጋግሞ ወተወታት

ቅድስት አፎምያም በእግዚአብሔር ኃይል ጸንታ በቅዱስ ሚካኤልም ተራዳኢነት ታምና “የእግዚአብሔር መልአክ ከሆንክ መንፈሳዊ ማረጋገጫህ የሆነው የመስቀል ምልክት የታለ?” በማለት በምድራዊ ንጉሥና በጭፍራው መካከል የሚኖርን የጋራ መግባቢያ መንገድ ዋቢ አድርጋ ጠየቀችው

ለጊዜው “በኛ በመላእክት ዘንድ እንዲህ አይደለም” ብሎ ሊሸነግላትና አቋሟን ሊያስቀይራት ሞከረ፡፡ ከቤቷ ያለ የቅዱስ ሚካኤል ሥዕል ላይ ያለውን ምልክት አብራርታ የእሱ ግን ከዛ ጋር አንድነት እንደሌለው አረጋገጠችበት፡፡ ከቤቷ ላለው ለቅዱስ ሚካኤል ሥዕል እጅ እንዲነሣ ጠየቀችው፡፡ በዚህ ጊዜ መልኩ ወደ ትክክለኛ ማንነቱ ተለወጠና ጨለማ ለብሶ እየዛተ አነቃት፡፡ ቅድስት አፎምያም የከበረ መልአክ ቅዱስ ሚካኤልን “ድረስልኝ” እያለች በጠራችው ጊዜ መልአኩም ፈጥኖ በመድረስ ከሰይጣን እጅ አዳናት

የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤልም ለሰይጣኑ ተገቢውን ቅጣት ሰጥቶ ቅድስት አፎምያን ባረካት፡፡ የዕረፍት ቀኗ በዚህ ቀን መሆኑን ነግሮ ቤቷን እንድታዘጋጅ አዘዛት፡፡ የበዓሉን ዝግጅት አከናውና ሥጋ ወደሙን ተቀብላ ኤጲስ ቆጶሱንና ካህናቱን እንደየመዓርጋቸው ጠርታ በቤቷ አክብራ ተቀበለቻቸው፡፡ ለነዳያንና ለጾም አዳሪዎች በኤጲስ ቆጶሱና በካህናቱ እጅ ገንዘቧን መጽውታ መንገዷን አሳመረች፡፡ ስለ ኃጢአቷ እንዲጸልዩላት ተማፅና በፊታቸው ተንበርክካ ጸለየች፡፡ ባሏ ያሠራላትን የቅዱስ ሚካኤልን ሥዕል አቅፋ ስማ ከተማጸነች በኋላ ሠኔ ፲፪ ቀን በሰላም ዐረፈች

ይህች የታመነች ቅድስት አፎምያ በሰላም እስክታርፍ ጊዜ ድረስ የተጓዘችበትን መንፈሳዊ ጎዳና አስተውለን ይሆን? አስቀድማ ከባሏ ጋር አንድ ሆና በታማኝነት ፈጣሪዋን አገለገለችው፡፡ በኋላም የባሏን ኑዛዜ አክብራ ምንም እንኳን ኃጢአት ባይሆንባትም በሁለተኛ ትዳር ራስዋን ማጠላለፍ አልፈለገችም፡፡ በጎ ሥራ አብልጣ በመሥራት እግዚአብሔርን ደስ ለማሰኘት ተፋጠነች እንጂ

ሰይጣን ልጅ አለመውለዷን ተጠቅሞ ያቀረበላትን የጋብቻ ጥያቄ ውድቅ በማድረግ “መንፈስን ሁሉ አትመኑ፤ መናፍስት ከእግዚአብሔር እንደሆኑ መርምሩ” ተብሎ በቅዱሳት መጻሕፍት የታዘዘውን መመሪያ ተጠቅማ ሰይጣንን በተወክሎ እግዚአብሔር ተቃውማ አሸነፈችው፡፡ የቅዱስ ሚካኤልን ርዳታ ያገኘችውና በሰላም ዐርፋ ወዳገለገለችው እግዚአብሔር በክብር የሔደችው በጽናት ተጋድላ ነው

ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን፤ እኛንም በጸሎቷ ይማረን፤ የቅዱስ ሚካኤል የረድኤቱ ኃይል ሁላችንንም ይጠብቀን፣ ለዘለዓለሙ አሜን ❤️

እንኳን ለእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የመገለጥ በዓል (ደብረ ምጥማቅ) በሰላም አደረሳችሁ አደረሰን ደብረ ምጥማቅ =>የአርያም ንግሥት: የሰማይና የምድር እመቤት: የሰውነታችንም መመኪያ...
29/05/2022

እንኳን ለእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የመገለጥ በዓል (ደብረ ምጥማቅ) በሰላም አደረሳችሁ አደረሰን

ደብረ ምጥማቅ

=>የአርያም ንግሥት: የሰማይና የምድር እመቤት: የሰውነታችንም መመኪያ ቅድስት ድንግል ማርያም በዚሕች ዕለት በምድረ ግብፅ ለተከታታይ ቀናት ተገልጻለች::

+ጥንተ ነገሩስ እንደ ምን ነው ቢሉ:

+ለስም አጠራሩ ስግደት ይሁንና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ምድረ ግብፅና ኢትዮዽያ በተሰደደ ጊዜ ከድንግል እናቱ: ከዮሴፍና ሰሎሜ ጋር ዛሬ ደብረ ምጥማቅ በሚባለው ቦታ ላይ አርፎ ነበር:: ቦታውን ባርኮ ለዘለዓለም ያንቺ መገለጫ ይሁን ብሎም ቃል ኪዳን ገብቶላት ነበር::

+ጊዜው በደረሰ ሰዓት ደብረ ምጥማቅ ተገድሞ የበርካታ መነኮሳት ቤት ሆነ:: እመቤታችንም በልጇ ፈቃድ ግንቦት 21 ቀን አእላፍ መላእክትን: ጻድቃን ሰማዕታትን አስከትላት መጣች::

+በዚያ ሕዝበ ክርስቲያንም: አሕዛብም ተሰብስበው ለ5 ቀናት ከእመ ብርሃን ጋር ይሰነብታሉ:: እንግዲህ ልብ በሉት:-
እንኩዋን የአርያም ንግስት: የአምላክ እናቱ እመቤታችንን ይቅርና በዚሕ ዓለም ሰይጣን ቤቱ ያደረጋቸውን: የመዝናኛው ኢንዳስትሪ ዝነኛ ሰዎችን ለማየት የዘመናችን ሰው እንዴት እንደሚቸኩል::

+እመቤታችንን በአካል መመልከት አይደለም ስሟን መጥራት ነፍስን ከሥጋ መለየት የሚችል ጣዕምና ደስታ አለው:: ባይሆን ይሔ ለሚገባውና ላደለው ብቻ ነው::

+የደብረ ምጥማቅና የአካባቢዋ ሰዎች ከእመቤታችን ጋር የሚቆዩባቸው ቀናት የዘለዓለም የሕይወት ስንቅ የሚይዙባቸው ናቸው:: ፈልገው የሚያጡት: ጠይቀው የማይፈጸምላቸው ምንም ነገር አልነበረም:: ነቢያት: ሐዋርያት: ጻድቃን: ሰማዕታት: ደናግል: መነኮሳት: መላዕክትና ሊቃነ መላእክት ለድንግል ማርያም ሲሰግዱ ይታዩ ነበርና:: እመ ብርሃንም እየመላለሰች ትባርካቸው ነበር::

+እነዚያ እርሷን ያዩ ዐይኖች: በፊቷ የቆሙ እግሮች ክብር ይገባቸዋል:: 5ቱ ዕለታት ሲፈጸሙ ሕዝቡ እመቤታችንን በዕንባ ይሰናበቷታል:: እመ ብርሃንም በብርሃን መስቀል ባርካቸው ከቅዱሳኑ ጋር ታርጋለች::

††† አባ መርትያኖስ †††

=>አባ መርትያኖስ በበርሃ ከ68 ዓመታት በላይ በቅድስና የኖሩ አባት ናቸው:: ሰይጣን እርሳቸውን ፊት ለፊት ተዋግቶ መጣል ቢያቅተው በዝሙት በተለከፉ ሴቶች ያስቸግራቸው ነበር::

+አንድ ቀን አንዷ ሽቶ አርከፍክፋ በዝሙት ልትጥላቸው ብትል እግራቸውን እሳት ውስጥ ጨምረው እግራቸው እየተቃጠለ በሚወጣው ጠረን አጋንንትን አርቀዋል:: እሷንም በንስሃ መልሰው ለቅድስና አብቅተዋታል:: ጻድቁ ከፈተና ለመራቅ በ108 ሃገራት 108 በዓቶች የነበሯቸው ብቸኛ አባት ናቸው::

††† ለአባት እናቶቻችን የተገለጠች እመቤታችን ለእኛም በረድኤት ትገለጽልን:: ጣዕመ ስሟ በአንደበታችን: ጣዕመ ፍቅሯ በልባችን ይደርብን:: †††

ወስብሐት ለእግዚአብሔር
ወለወላዲቱ ድንግል
ለወለመስቀሉ ክቡር አሜን

ጥር ፳፩ አስተርእዮ ማርያምወላዲተ አምላክ ምንም እንኳን የአምላክ እናት ብትሆንም ሞተ ሥጋ ለሁሉም ዕጣ ፈንታ በመሆኑ በስድሳ አራት አመቷ ከሞት ወደ ሕይወት ከመከራ ወደ ደስታ የተሸጋገረችበ...
29/01/2022

ጥር ፳፩ አስተርእዮ ማርያም

ወላዲተ አምላክ ምንም እንኳን የአምላክ እናት ብትሆንም ሞተ ሥጋ ለሁሉም ዕጣ ፈንታ በመሆኑ በስድሳ አራት አመቷ ከሞት ወደ ሕይወት ከመከራ ወደ ደስታ የተሸጋገረችበት ዕለት ነው፡፡ታላቁ የቤተክርስቲያን አባት ቅዱስ ያሬድም “ሞትሰ ለመዋቲ ይደሉ ሞታ ለማርያም የአጽብ ለኩሉ” ትርጉሙ ሞት ለማናኛቸውም ሰው ሁሉ የተገባ ነው የማርያም ሞት ግን ሁሉን ያስደንቃል፡፡ በማለት አደነቀ፡፡ በመሆኑም በዓሉ የወላዲተ አምላክ በዓለ ዕረፍት ከመሆኑ የተነሳ ታላቅ በረከት የሚያስገኝ ስለሆነ በየዓመቱ ይከበራል፡፡

… የእረፍቷስ ነገር እንደምን ነው ቢሉስድሳ አራት ዓመት በዚህ ዓለም ኖራ ጥር ፳፩ እሁድ ቀን ጌታ እልፍ አዕላፋት መላዕክቱን አስከትሎ መጥቶ እናቴ ሆይ ከዚህ ዓለም ድካም ላሳርፍሽ መጣሁ አላት፡፡ ልጄ ሰማይና ምድር የማይወስኑ ዘጠኝ ወር ከአምስት ቀን በማህጸኔ ተሸክሜ በድንግልና ወልጄህ እሞታለሁ አለችው፡፡ በሲዖል የሚሰቃዩ ነፍሳትን አሳይቶ እናቴ ሆይ ሞትሽ ለእነዚህ ቤዛ ይሆንላቸዋል አላት፡፡ እኚህን ከማርክልኝስ ይሁን አለችው፡፡ ቅድስት ሥጋዋን ከቅድስት ነፍሷ ለይቶ በቃለ አቅርንት በዝማሬ መላእክት አሳረጋት፡፡

ደቀመዛሙርቱንም ከያሉበት በደመና ጠቅሶ ካለችበት አድርሶ እመቤታችሁን ቅበሩ አላቸው፡፡ ይዘወት ወደ ጌሰማኒ ሲስደት አይተው ልጇን ተነሳ አረገ እያሉ ሲውኩን ይኖራሉ አሁን ደግሞ እሷን ተነሳች አረገች እያሉ ሊያውኩን አይደለም ብሎ ኑ እናቃጥላት ተባባሉ፡፡ ከመካከላቸው አንዱ ታውፋንያ ዘሎ ያልጋውን ሸንኮር ያዘ፡፡ የታዘዘው መላእክት መጥቶ በሰይፍ ሁለት እጁን ቀጣው፡፡ በድያለሁ ማሪኝ ብሎ ቢማጸናት ድኖለታል፡፡ ከዚህ በሗላ ዮሐንስን ጨምሮ ከመካከላቸው ነጥቆ በእጸ ሕይወት ሥር አኑሯታል፡፡

አንድም በዓሉ-፡ እግዚአብሔር ወልድ በሰውነት ተወልዶና ማንነቱ በይፋ ታውቆ በተገለጠበት በዘመነ አስተርእዮ ውስጥ ስለሚከበር የ“አስተርእዮ ማርያም” ተብሏል፡፡ አስቀድመው አሥራ ሁለቱም ሐዋርያት ለስብከተ ወንጌል ወደ ዓለም ሁሉ ተበትነው ነበርና በመንፈስ ቅዱስ ተነድተው ሁሉም ደመናን ጠቅሰው ወደ ኢየሩሳሌም መጡ፡፡ ነገር ግን መንፈስ ቅዱስ መርቶ አመጣቸው እንጂ ለምን እንደመጡ አያውቁም ነበር፡፡ እመቤታችንም ለምን እንደመጡ ጠየቀቻቸው፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስም፡- “ጸጋን የተመላሽ ቅድስት ሆይ! የመምጣታችን ምሥጢርማ እኛ አንቺን እንጠይቅ እንጂ አንቺም እኛን ትጠይቃለሽን? ሁላችንም ለምን እንደመጣን አናውቅም፡፡ ለምሳሌ እኔ አስቀድሜ በአንጾክያ ነበርኩኝ አሁን ግን እነሆ እዚህ ነኝ፡፡ ለምን እንደመጣሁኝ ግን አላውቅም” አላት፡፡ እርሷም ሁሉም በአጠገቧ በተሰበሰቡ ጊዜ የሚሆነውን ነገር አስቀድማ ከልጇ ከወዳጇ አውቃ ተዘጋጅታ ነበርና ለምን እንደመጡ (ዕረፍተ ሥጋዋን ለማየት እንደሆነ) ነገረቻቸው፡፡ ሌሊቱንም በሙሉ በጸሎትና በማኅሌት ደግሞም በዝማሬ ሲያመሰግኑ አደሩ፡፡ ከዚህ በኋላ የተወደደችው እናት በረከቷን አሳድራባቸው በሰላም አንቀላፋች፡፡ ነፍሷም በዐብይ ዕልልታና በታላቅ ምስጋና በመላእክት እጅ ወደ አምላኳ ሄደች፡፡ ኋላ ሐዋርያቱ ዮሐንስን ሲያገኙት፡- “እመቤታችን እንደምን ሆነች?” አሉት፡፡ እርሱም “በገነት በዕጸ ሕይወት ሥር ዐርፋለች” አላቸው፡፡ የቀሩት ሐዋርያት “ዮሐንስ ያን ድንቅ የእግዚአብሔርን ሥራ አይቶ እኛስ ሳናይ እንዴት እንቀራለን?! አቤቱ ለእኛም ቸርነትህን አድርግልን” ብለው በነሐሴ መባቻ በአንድነት ሆነው ወደ ፈጣሪያቸው የሚቀርብ የአንድ ሳምንት ጾምና ጸሎት ጀመሩ፡፡ በሁለተኛው ሱባዔ ማብቂያ ዕለት ነሐሴ ፲፬ ቀን እሑድ የእመቤታችንን ትኩስ ሥጋ መልአኩ ከገነት አምጥቶ ለሐዋርያቱ ሰጣቸው፡፡ እነርሱም ልመናቸው ስለ ተፈጸመላቸው ፈጣሪያቸውን በጸሎት አመስግነው በዚያችው ዕለተ እሑድ ቅዱስ ሥጋዋን ወስደው ቀብረውታል፡፡ እርሷም በሦስተኛው ቀን ነሐሴ ፲፮ ቀን ማክሰኞ ተነሥታለች፡፡
ትንሣኤዋ “ከመ ትንሣኤ ወልዳ- እንደ ልጇ ትንሣኤ” ያሰኘው ይህ በሦስተኛው ቀን ከሙታን ተለይታ የመነሣቷ እውነታ ነው።

ከበዓሉ ረድኤት በረከት ያሳትፈን!አሜን!

ኅዳር 12 የሊቀ መላእክት ቅዱስ ሚካኤል ታላቅ በዓል የሚከበርበት ምክንያትሚካኤል ማለት በዕብራይስጥ ቋንቋ ሚ-መኑ' ካ-ከመ' ኤል- አምላክ ማለት ሲሆን በአንድነት ሲነበብ መኑ ከመ አምላክ ...
19/11/2021

ኅዳር 12 የሊቀ መላእክት ቅዱስ ሚካኤል ታላቅ በዓል የሚከበርበት ምክንያት

ሚካኤል ማለት በዕብራይስጥ ቋንቋ
ሚ-መኑ' ካ-ከመ'
ኤል- አምላክ ማለት ሲሆን በአንድነት ሲነበብ መኑ ከመ አምላክ (እንደ እግዚአብሔር ያለ ማን ነው) ማለት ነው፡፡ ይህ ታላቅ መልአክ ዮሐንስ ወንጌላዊ በራዕዩ ‹‹በእግዚአብሔር ፊት የሚቆሙትን ሰባቱን መላእክት አየሁ›› ብሎ ከተናገረላቸው መላእክት ውስጥ የሚመደብ ሲሆን የሰባቱም ሊቃነ መላእክት አለቃ እንዲሆን እግዚአብሔር መርጦ ሹሞታል፡፡ ይህ ታላቅ መልአክ ያደረጋቸው የሠራቸው እጅግ ብዙ የሆኑ ተአምራት አሉት፡፡

★★በኅዳር 12 ክቡር ገናና የሆነ ቅዱስ ሚካኤል ካደረጋቸውና ከሠራቸው ብዙ ተአምራት ውስጥ የተወሰኑትን በመልአኩ ተረዳኢነት እንዲህ ብለን እንናገራለን አንጽፋለን፡፡
👉ንግሥት ክሌዎፓትራ ‹‹ሳተርን›› ለሚባለው ጣዖት የሠራችው ቤተ ጣዖት በእስክንድርያ ነበር፡፡ ይህ ቤተ ጣዖት እስከ እስክንድርያው ፓትርያርክ እለ እስክንድሮስ /312 - 326/ ዘመን ድረስ ነበር፡፡ እለ እስክንድሮስ ሊያጠፋው ሲነሣ ሕዝቡ ከልቡ ገና የአምልኮ ጣዖት ስላልጣፋ 18 ፓትርያርኮች ያልነኩትን አንተ ለምን ታፈርስብናለህ ብለው ተቃወሙት፡፡ እለ እስክንድሮስም ሕዝቡን መክሮና አስተምሮ የሳተርን በዓል ይውልበት በነበረው ዕለት የቅዱስ ሚካኤልን በዓል እንዲያከብሩ አውጆ ቤተ ጣዖቱንም በቅዱስ ሚካኤል ስም ሰይሞ ቤተክርስቲያን አደረገው፡፡ ከዚህ በኋላ በቅዱስ ሚካኤልም ስም አብያተ ክርስቲያናት መታነጽ ጀመሩ በዓሉ በዚህ ቀን እንዲከበር ተወስኗል፡፡
👉እንዲህም ሆነ የእግዚአብሔር ወዳጅ የሆነ ስሙ ዱራታዎስ የሚባል አንድ ሰው ነበረ፡፡ የሚስቱም ስም ቴዎብስታ ነው፡፡ እነርሱም ሁልጊዜ ያለ ማቋረጥ የዚህን የከበረ መልአክ የሚካኤልን የበዓሉን መታሰቢያ ያረጉ ነበር፡፡ ከዚህም በኋላ በሀገር ውስጥ ችግር በሆነ ጊዜ ገንዘባቸው አለቀ፡፡ በዚህም የተነሳ ለመላእክት አለቃ ለቅዱስ ሚካኤል ለበዓሉ መታሰቢያ የሚያደርጉትን አጡ፡፡ ዱራታዎስም ሽጦ ለበዓሉ መታሰቢያ ያደርገው ዘንድ የእርሱን ልብስና የሚስቱን ልብስ ይዞ ወጥቶ ሄደ፡፡ የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤል በታላቅ መኮንን አምሳል ለዱራታዎስ ተገለጠለት፤ ቅዱስ ሚካኤልም ዱራታዎስን ወደ በጎች እንዲሔድና በእርሱ ዋስትና በአንድ ዲናር አንድ በግ እንዲወስድ አዘዘው፤ ሁለተኛም ወደ ዓሣ አጥማጅ ሔዶ አንድ ዓሣ እንዲወስድ አዘዘው፡፡ መልአኩም ወደ ቤት ሳይደርስ የዓሣውን ሆድ እንዳይቀድ አስጠነቀቀው፡፡ ወደ ባለ ስንዴም እንዲሔድና የሚሻውን እንዲሁ በእርሱ ዋስትና እንዲወስድ አዘዘው ዱራታዎስም ቅዱስ ሚካኤል እንዳዘዘው አደረገ፡፡
ወደ ቤቱም በተመለሰ ጊዜ በረከትን ሁሉ ቤቱ ተመልቶ አገኘው፤ እጅግም አደነቀ፤ የዚህንም የከበረ መልአክ የበዓሉን መታሰቢያ እንዳስለመደው አደረገ፡፡ የተራቡ ድሆችን ሁሉንም ጠርቶ መገባቸውና ወደ ቤታቸው አሰናበታቸው፡፡
ከዚህም በኋላ ለዱራታዎስና ለሚስቱ ቅዱስ ሚካኤል ለሁለተኛ ጊዜ ተገለጠላቸው ዱራታዎስንም የዓሳውን ሆድ እንዲሰነጥቅ አዘዘው፤ በሰነጠቀውም ጊዜ ሦስት መቶ የወርቅ ዲናር በዓሳው ሆድ ተገኘ፡፡ ቅዱስ ሚካኤልም ዱራታዎስንና ቴዋብስታን እንዲህ አላቸው፡፡ ‹‹ከዚህ ዲናር ወስዳችሁ ለባለ በጉ ለባለ ዓሳውና ለባለ ስንዴው ዕዳችሁን ክፈሉ የቀረውም ለፍላጎታችሁ ይሁናችሁ፤ እግዚአብሔር አስባችኋልና በጎ ሥራችሁን መስዋዕታችሁን ምጽዋዕታችሁን በዚህ ዓለም አሳመረላችሁ፡፡ በኋላኛውም መንግሥት ሰማያትን አዘጋጅቶላችኋል፡፡››

👉በአንድ ዘመን ብዙ ሰዎች ከግብፅ አውራጃ መጥተው ወደ ባሕር ማዶ ሄዱ፡፡ ከባሕሩም በደረሱ ጊዜ በመርከብ ላይ ተሳፍረው ከየብሱ ጥቂት በራቁና ወደ ባሕሩ መካከል በደረሱ ጊዜ ጽኑ ነፋስ ተነሳባቸው ለመስጠም እስኪ ደርሱ ድረስ፡፡
የማዕበሉ ሞገድ እየጨመረ እየጸና ከፍ አለ፡፡ ታላቅም ማዕበል መጥቶ ሊገለብጣቸው ደረሰ፡፡ ፍጹም ጥፋትና ክፉ ሞት እንደ መጣባቸው ባዩ ጊዜ ጽኑ ሐዘን ያዛቸው፡፡ የሚያድናቸው የሚያጽናናቸው አጥተው ተስፋ ቆረጡ፡፡ ያን ጊዜ እንዲህ ብለው ጮኹ፡፡
‹‹የመላእክት አለቃቸው ግሩም ገናና የምትሆን ሚካኤል ሆይ የተአምራትና የይቅርታ መልአክ ነህና፡፡ ልዑል ቸርነቱን የሚገልጥብህ መልአክ ሆይ! እግዚአብሔር ፍቅሩን የሚያስታውቅብህ መልአክ ሆይ ወደኛ ተመልከት እርዳን፡፡ የተጨነቅን እኛን አድነን፡፡ ከመጣብን ሞትና ጥፋት እንድን ዘንድ ስለኛ ወደ ፈጣሪህ ወደ ፈጣሪያችን ወደ እግዚአብሔር ለምንልን፡፡ አሁን የሞት መጋረጃ ዓይናችንን ሸፍኖታልና፡፡ ፍጹም የጥፋት ጥላንም አይተናታልና›› ብለው በፍጹም ልቦናቸው ወደ እግዚአብሔር ጮኹ፡፡ በመርከብ ውስጥ ያሉት ሁሉ ጽኑ ለቅሶ እያለቀሱ መራራ እንባ እያፈሰሱ ጮኹ፡፡
ከባሕር ጽኑ ማዕበል ከሞት ያድናቸው ዘንድ ያን ጊዜ በዚያች ሰዓት እግዚአብሔር የልቦናቸውን ሐዘንና ልመናቸውን ሰማቸው፡፡ ያን ጊዜም ይረዳቸው ዘንድ ቸር መልአኩን ሚካኤልን ላከላቸው የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤልም ከሰማይ ወረደ መርከቡን በእጁ ይዞ ሳበው፡፡ በመርከቡ ውስጥ ያሉትንም ወደ የብስ አወጣቸው፡፡ በደኅናቸው ተሻገሩ፤ ክፉ ነገር ጥቂትስ ስንኳ ፈጽሞ አላገኛቸውም፡፡
ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም ገናና የሆነ የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤል ልመናውና አማላጅነቱ ፈጽሞ ይጠብቀን፡፡ ከጽኑ ጠላት እጅ በክንፎቹ ጋርዶ ይሰውረን፡፡ ለዘለዓለሙ አሜን፡፡

ድርሳነ ሚካኤል ዘኅዳር
ምንጮች መጽሐፈ ስንክሳር ዘኅዳር
የሐመር መጽሔት 1993 ዓም መጋቢት እና ሚያዝያ

[ሐምሌ 19 የሊቀ መላእክት የቅዱስ ገብርኤልና የቅዱስ ቂርቆስ በዓል]❖ሐምሌ 19 ዕለት የመላእክት አለቃ ቅዱስ ገብርኤል አምላካቸው ክርስቶስን አንክድም በማለታቸው የፈላ ጋን ውስጥ የተወረወ...
25/07/2021

[ሐምሌ 19 የሊቀ መላእክት የቅዱስ ገብርኤልና የቅዱስ ቂርቆስ በዓል]

❖ሐምሌ 19 ዕለት የመላእክት አለቃ ቅዱስ ገብርኤል አምላካቸው ክርስቶስን አንክድም በማለታቸው የፈላ ጋን ውስጥ የተወረወሩት ቅዱስ ቂርቆስና እናቱን ቅድስት ኢየሉጣ ተራድቶ ያዳነበት በዓል ነው።

❖ ይኸውም የቅድስት ኢየሉጣን ልጅ ሕፃኑ ቅዱስ ቂርቆስ ከሐዲው መኰንኑ ይዞ “ስምኽ ማነው” ብሎ በጠየቀው ጊዜ “ነቅዕ ዘእምዐዘቅት ንጹሕ ወእማይ ዘኢይማስን ክርስቲያን ስምየ” (ከንጹሕ ዐዘቅትና ከማይለወጥ ከማይጠፋ ውሃ የተገኘ ስሜ ክርስቲያን ነው ሞክሼ ስም ከፈለግኽ ደግሞ እናቴ የሠየመችኝ ቂርቆስ ነው) በማለት ክርስትናው መመኪያው የኾነው ይኽ ቅዱስ ሕፃን መለሰለት፡፡

❖ መኰንኑም ለአማልክት ከሠዋኽ ስታድግ እሾምኻለኊ ክርስቶስን ካድ ቢለው ቅዱስ ቂርቆስ ግን “የሰይጣን መልእክተኛ ለእውነትም ጠላቷ የኾንኽ ከእኔ ራቅ” አለው፡፡ መኰንኑም ይኽነን ሰምቶ በመቈጣት የቅዱስ ቂርቆስ ደሙ እንደ ውሃ እስኪፈስስ ድረስ እንዲጨምቁት እና ጨውና ሰናፍጭ በኹለቱ የአፍንጮቹ ቀዳዳዎች እንዲጨመሩ ቢያደርግበት፤ በመንፈስ ቅዱስ ጸጋ የጠነከረው ሕፃኑ ቅዱስ ቂርቆስ ግን “ትእዛዝኽ ለጒረሮዬ ጣፋጭ ኾነ ከማርና ከሥኳርም ለአፌ ጣመኝ” እያለ አምላኩ ክርስቶስን አመሰገነ፡፡

❖ መኰንኑ በዚኽ ሳያበቃ እናትና ልጇ በክፉ አሟሟት እንዲሞቱ በማሰብ የረዘሙና የተሳሉ በእሳትም እንደ ፍም የጋሉ ዐሥራ አራት የብረት ችንካሮች እንዲመጡ አስደርጎ ሰባቱ በእናቱ አካላት፤ ሰባቱ በሕፃኑ ሰውነት ላይ እንዲሰካ ቢያስደርግም በጌታችን ትእዛዝ ግለቱ ጠፍቶ እንደ በረዶ በመቀዝቀዝ ምንም ምን ጒዳት ሳያደርስባቸው ቀረ፡፡

❖ ከዚያም ወደ ወኅኒ ቤት እንዲገቡና እንዲዘጋባቸው አደረገ፤ ከዚያም ሕፃኑና እናቱ የሚሠቃዩበት ታላቅ መንኰራኲር ለ፵ ቀናት ተሠርቶ ካለቀ በኋላ ኹለቱንም በደራቁ ራሳቸውን ላጭተው የእሳት ፍሕምን በላያቸው ላይ ቢያደርጉም የእግዚአብሔር መልአክ ሥቃዮቹን ኹሉ ከእነርሱ አራቀላቸው፡፡

❖ የሕፃኑ ምላስ እንዲቈረጥ አዝዞ ቢያስቈርጠውም ጌታችን ምላሱን መልሶለታል፡፡ “ወአዘዘ ካዕበ ያፍልሑ ማየ ውስተ ጽሕርት ዐቢይ ወይደይዎሙ ለሕፃን ቂርቆስ ወለእሙ ኢየሉጣ” ይላል በታላቅ ጋን ውሃ አፍልተው ሕፃኑንና እናቱን እንዲጨምሯቸው ሲያዝዝ ከሚፍለቀለቀው ውሃ ድምፅ የተነሣ ለጊዜው እናቱ ፍርሀት ሥጋዊ ቢያገኛትም ልጇም ወደ ጌታችን በጸለየላት ጊዜ ፍርሃቱ ርቆላት ከልጇ ጋር ስትገባ መልአከ ብርሃን ቅዱስ ገብርኤል ወርዶ ውሃውን አቀዝቅዞ ሐምሌ ፲፱ አውጥቷቸዋል፡፡

❖ በመጨረሻም የሰማዕትነትን አክሊል የሚያገኝባት ጊዜ ሲደርስ ጌታችን ተገልጾለት ስሙን ለሚጠራ ኹሉ ቃል ኪዳንን ከሰጠው በኋላ ሥጋኽን በኤልያስ ሠረገላ ላይ አኖርልኻለኊ አለው፤ ይኽነን በሰማ ጊዜ በእጅጉ ተደሰተ፤ ከዚኽም በኋላ ጥር ፲፭ በሌሊቱ እኲሌታ ከእናቱ ጋር አንገቱ ተቈረጠ የሰማዕትነትን ክብር ተቀዳጅተዋል።

❖ ጥር ፲፮ ደግሞ የቅዱስ ቂርቆስ ማኅበር የኾኑ ዐሥራ አንድ ሺሕ አራት በሰማዕትነት ዐልፈዋል፡፡

✔ሊቁ አርከ ሥሉስም የቅዱስ ቂርቆስን ተጋድሎ በማዘከር፡-
“እግዚአብሔር ሤመ ረድኤቶ ለንእስናከ ዐቃቤ
ወስምዖ መጥበቤ
ፍትወ ምግባር ቂርቆስ ወምዑዘ ኂሩት እምከርቤ
ለዘተጽዕረ በምንዳቤ ወለዘቈስለ በጥብጣቤ
ለአባልከ ሰላም እቤ”
(እግዚአብሔር ረድኤቱን ለታናሽነትኽ ጠባቂን አስቀመጠ፤ ብልኅ የሚያደርግ ምስክርነቱንም፤ ምግባርኽ ያማረ በጎነትኽ ከከርቤ ይልቅ የሚሸት ቂርቆስ፤ በመከራ የተቸገረ በግርፊያ የቈሰለ ለኾነ ሰውነትኽ ሰላም እላለኊ) እያለ ሕፃኑን ሰማዕት ያወድሳል፡፡

❖ ሊቁ አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫም በመጽሐፉ፦
“ሰላም ለቂርቆስ ወሬዛ በመንፈስ
በልደት ንዑስ፤
ንጹሕ ከመ ዕጣን
ወፍሡሕ ከመ ወይን”፡፡
(በልደተ ሥጋ ታናሽ በመንፈስ ጐልማሳ፤ እንደ ዕጣን ንጹሕ እንደ ወይንም አስደሳች ለኾነ ለቂርቆስ ሰላምታ ይገባል)

❖“ሰላም ለሰማዕታት እለ ምስሌሁ ፭፼ ወ፬፻፤ ፬፼ ወ፪፻፲ወ፬”፡፡
(ከርሱ ጋር ያሉ ፭፼ ከ፬፻፤ ፬፼ከ፪፻፲፬ ሰማዕታት ሰላምታ ይገባቸዋል) በማለት አመስግኗል፨
[የሊቀ መላእክት የቅዱስ ገብርኤል ተራዳኢነት የቅዱስ ቂርቆስ የእናቱ የኢየሉጣ፤ ስለአምላካቸው ስለ ክርስቶስ ፍቅር አንገታቸው በሰይፍ የተቆረጡት የሰማዕታት በረከት ይደርብን፨
[ከመጋቤ ሐዲስ ሮዳስ ታደሰ]

 ሰኔ ሃያ አንድ በዚች ዕለት የአዳምና የዘሩ ድኅነት የተደረገባት አምላክን የወለደች   የታላቁ በዓል መታሰቢያና በዓለም ሁሉ የቤተ ክርስቲያን መታነፅ መታሰቢያ ነው፣ ከምስር አገር   በሰማ...
28/06/2021



ሰኔ ሃያ አንድ በዚች ዕለት የአዳምና የዘሩ ድኅነት የተደረገባት አምላክን የወለደች የታላቁ በዓል መታሰቢያና በዓለም ሁሉ የቤተ ክርስቲያን መታነፅ መታሰቢያ ነው፣ ከምስር አገር በሰማዕትነት ሞተ፣ የእስክንድርያ ሊቀ ጳጳሳት አረፈ፣ በመሸታ ቤት ባረድዋት በአንዲት ሴት ላይ ላደረገው ተአምር መታሰቢያ ነው፡፡

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

(ህንጸተ ቤተክርስቲያን)

ሰኔ ሃያ አንድ በዚች ዕለት የአዳምና የዘሩ ድኅነት የተደረገባት አምላክን የወለደች የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የታላቁ በዓል መታሰቢያና በዓለም ሁሉ የቤተ ክርስቲያን መታነፅ መታሰቢያ ነው። ከሁሉ አስቀድሞ ያቺ ቤተ ክርስቲያን በሐዋርያት ዘመን ብቻዋን ታነፀች።

ይኸውም ጳውሎስና በርናባስ በአሕዛብ ውስጥ በሰበኩ ጊዜ ክብር ይግባውና በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ አመኑ ከሰዎች ቤቶች በቀር ቅዱስ ቊርባንን የሚቀበሉበት ቤተ ክርስቲያንም አልነበራቸውም ነበር። ስለዚህም ወደ ጴጥሮስና ወደ ሐዋርያት ሁሉ ስለ ቤተ ክርስቲያን መታነፅ ጉዳይ እየለመኑ መልእክትን ላኩ።

ሐዋርያትም እንዲህ ብለው መለሱላቸው ክብር ይግባውና ያለ ጌታችን ፈቃድ እኛ ምንም ምን አንሠራም። ነገር ግን የምንሠራውን እስኪያስረዳን ድረስ ወደ እግዚአብሔር እየጸለዩና እየማለዱ አንድ ሱባኤ ይጾሙ ዘንድ ወደ ሃይማኖት የተመለሱ አሕዛብን እዘዙአቸው እንዲህም አዘዙአቸው።

በሱባዔውም ፍጻሜ ክብር ይግባውና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተገለጸላቸው ሐዋርያትንም ሁሉ ከየአገሮች ሁሉ እስከ ፊልጵስዮስ በደመና ሰበሰባቸው ከእርሳቸውም ጋር ጳውሎስና በርናባስ ነበሩ ጌታችንም ባረካቸው እንዲህም ብሎ ነገራቸው "ይቺ ዕለት በእናቴ በማርያም ስም በአራቱ ማእዘነ ዓለም አብያተ ክርስቲያናት እንድታንፁ የፈቀድኩባት ናት።"

ይህንንም ብሎ ከከተማዋ በስተ ምሥራቅ በኲል አወጣቸው የቤተ ክርስቲያኒቱንም ቦታና መሠረቷን ወሰነላቸው ከእርሳቸውም ጋራ የእግዚአብሔር ኃይል ነበረ የቤተ ክርስቲያኒቱ ሕንፃዋ እስከ ተፈፀመ ድረስ ደንጊያዎች በሐዋርያት እጆች ውስጥ ይለመልሙ ነበረ ጌታችንም ነዋየ ቅድሳቷን አልባሳትዋንና መሠዊያዋን አዘጋጀ።

ከዚህ በኋላ ጌታችን እጁን በጴጥሮስ ራስ ላይ ጭኖ በአራቱ ማእዘነ ዓለም ውስጥ "አርሳይሮስ" ብሎ ሾመው ይህም "ሊቀ ጳጳሳት" ማለት ነው። ለሐዋርያት አለቃ ጴጥሮስ ከጽንፍ እስከ ጽንፍ የጳጳሳት አለቃ ይሆን ዘንድ ይገባዋል ይገባዋል ይገባዋል እያሉ ሰማያውያን መላእክትና ምድራውያን ሰዎች ሦስት ጊዜ አሰምተው ተናገሩ።

ከዚህም በኋላ ጌታችን ሐዋርያትን የቊርባኑን ቅዳሴ ሥርዓት ያከናውኑ ዘንድ ለሕዝቡም ሥጋውን ደሙን ያቀብሏቸው ዘንድ አዘዛቸው እንዲህም የሚል አለ ራሱ መድኃኒታችን ቀድሶ ሥጋውንና ደሙን ለሐዋርያት አቀበላቸው። እንዲህም አላቸው በዚች ቀን የእጃቸውን ሥራ እንዳይሠሩ ሕዝቡን ሁሉ እዘዙአቸው ይኸውም በሰኔ ወር ሃያ አንድ ቀን ነው።

ከዚህም በኋላ መድኃኒታችን ከእርሳቸው ዘንድ በታላቅ ክብር ወደ ሰማያት ዐረገ። ከዚያችም ቀን ጀመሮ አባቶቻችን ሐዋርያት በዓለሙ ሁሉ ውስጥ አምላክን በወለደች በእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ስም ቤተ ክርስቲያን የሚያሳንፁ ሆኑ።

በቂሣርያው ሊቀ ጳጳሳት በባስልዮስ ዘመን እንዲህ ሆነ በእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ስም ቤተ ክርስቲያን በሠራ ጊዜ በውስጡ የእመቤታችን የማርያምን ሥዕል ይሥልበት ዘንድ ሠሌዳ ፈለገ ሰዎችም በአንድ ባለጸጋ ዘንድ ስለ አለ አንድ መልካም ሠሌዳ ነገሩት።

ቅዱስ ባስልዮስም ሠሌዳውን እንዲሰጠው ወደ ባለጸጋው ላከ ባለጸጋውም ይህ ሠሌዳ ለልጆቼ ነው አለ እንጂ ፈቃደኛ አልሆነም። ከዚያም አልፎ በመድፈር በእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ቤተ ክርስቲያን ላይ የስድብ ቃል ተናገረ ወዲያውኑም በድንገት ወድቆ ሞተ ልጆቹም ፈሩ ያንንም ሠሌዳ ከብዙ ወርቅና እንቊ ጋራ ወደ ቅዱስ ባስልዮስ አምጥተው የአባታቸውን በደል ያቃልልለት ዘንድ ለመኑት።

ቅዱስ ባስልዮስም ያንን ሠሌዳ ወስዶ የእመቤታችንን ሥዕል ይሥልበት ዘንድ ለሠዓሊ ሰጠው። እመቤታችንም ቅድስት ድንግል ማርያም በሌሊት ራእይ ለቅዱስ ባስልዮስ ተገለጸችለት ሥዕሏንም በዚያ ሠሌዳ ላይ እንዳይሥል ከለከለችው። ከዐመፀኛ ሰው እጅ ወስዶታልና። እጅግም ያማረ የእመቤታችን ሥዕሏ የተሣለበት የሁለት ደናግልም ሥዕል ያንዲቱ በቀኝ ያንዲቱ በግራ ሆኖ የተሣለበት ቀይ ሠሌዳ ያለበትን ቦታ ነገረችው።

ቅዱስ ባስልዮስም እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ወደ አመለከተችው ወደዚያ ቦታ ሔደ ያንንም ሠሌዳ አገኘው ወደዚያች ቤተ ክርስቲያንም በታላቅ ደስታ አመጣው።

ከዚህም በኋላ ዳግመኛ በአንድ ጣዖት ቤት ሁለት ምሰሶዎች እንዳሉ አስረዳቸው እነርሱንም አምጥቶ በመቅደሱ ፊት ለፊት እንዲአቆማቸው በላያቸውም ሥዕሏን እንዲያኖር አዘዘችው።

ቅዱስ ባስልዮስም እነዚያን ምሰሶዎች ያመጣቸው ዘንድ ሔደ መሠርያኑም ሊከለክሉት ፈለጉ ጌታችንም ኃይላቸውን ደመሰሰ እነዚያንም ምሰሶዎች አምጥቶ በቤተ መቅደሱ ፊት ለፊት አቆማቸው በላያቸውም የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ሥዕሏን አስቀመጠ እግዚአብሔርም ከእነዚያ ምሰሶዎች በታች የውኃ ምንጭ አፈለቀ በውስጥዋም የሚታጠብ ሁሉ ከአለበት ደዌ ሁሉ የሚድን ሆነ።

እንዲሁም ከእመቤታችን ማርያም ሥዕል በሽተኞችን ሁሉ የሚፈውስ የዘይት ቅባት ፈሰሰ ይህ ሁሉ የሆነ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ቤተ ክርስቲያን በከበረችበት በሰኔ ወር በሃያ አንድ ቀን ነው።

በዚያችም ቀን እንዲህ ሆነ አንዲት ሴት መጥታ ታጠበች ወዲያውኑም ሁለመናዋ በለምጽ ተሸፈነ ቅዱስ ባስልዮስም ወደርሱ አስቀርቦ በእርሷ ላይ የሆነውን ጠየቃት እርሷም የእኅቷን ባል እንደወደደችና እኅቷን በመርዝ ገድላ እንዳገባችው ነገረችው። ቅዱስ ባስልዮስም ታላላቅ ሦስት ኃጢአቶችን ሠራሽ ግን ወደ እግዚአብሔር ንስሐ ግቢ ምንአልባት በደልሽን ይቅር ይልሽ እንደ ሆነ አላት በዚያን ጊዜም ምድር ተሠንጥቃ እንደ ዳታን ዋጠቻት እርሷ የረከሰች ስትሆን ወደ ቤተ ክርስቲያን መግባትን ደፍራለችና።

እኛ ሁላችን የክርስቲያን ወገኖች አምላክን ለወለደች ለእመቤታችን ለከበረች ድንግል ማርያም ለመታሰቢያዋ መንፈሳዊ በዓልን ልናደርግ ይገባናል ሰለ እርሷ ለአዳምና ለሁላችን ለልጆቹ ድኅነት ሆኖአልና ይህንንም በዓል ለማድረግ የሚተጋ የተመሰገነ ነው።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞



ዳግመኛም በዚህች ቀን ከምስር አገር ቅዱስ ጢሞቴዎስ በሰማዕትነት ሞተ። ይህም ቅዱስ አስቀድሞ ከእንዴናው ገዥ ከአርያኖስ ጭፍራዎች ውስጥ ነበር ሰው ሁሉ ጣዖታትን እንዲያመልክ የሚያዝ የዲዮቅልጥያኖስ የመልእክት ደብዳቤ በተነበበ ጊዜ ይህ ቅዱስ ከሕዝቡ መካከል ተነሥቶ የንጉሡን ደብዳቤ ወስዶ ከሕያው እግዚአብሔር ልጅ ከኢየሱስ ክርስቶስ በቀር ሌላ አምላክ የለም ብሎ የከሀዲውን ንጉሥ የመልእክት ደብዳቤ ቀደደ።

መኰንኑም ድፍረቱን አይቶ ወደርሱ ገሥግሦ ሔደና የራሱን ጠጉር ይዞ አንሥቶ በምድር ላይ ጣለው ታላቅ ድብደባም እንዲደበድቡት አዘዘ ሁለተኛም ሁለመናው እስቲደቅ እንዲደቁሱት አዘዘ እርሱም የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ ርዳኝ እያለ ይጮኽ ነበር።

ጌታችንም ትዕግሥቱን አይቶ መልአኩን ልኮ ከሥቃዩ አድኖ ጤነኛ አደረገው ወደ መኰንኑም ቀርቦ ከሕያው እግዚአብሔር ልጅ ከአንዱ ከኢየሱስ ክርስቶስ በቀር ሌላ አምላክ የለምና አንተ ከሀዲ እፈር አለው።

ያን ጊዜም ይዞ ጽኑ ሥቃይን አሠቃየው በመጋዝም መግዞ ሰቀለው ከዚያም በኋላ ሥጋው እንደ ሰም ቀልጦ እንደ ውኃ እስቲፈስ በብረት ምጣድ ውስጥ አበሰለው ከከተማ ውጪም ጣሉት።

ክብር ይግባውና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ያለምንም ጉዳት አንሥቶ ጤነኛ አደረገው። ወደ መኰንኑም ተመልሶ ከሕያው እግዚአብሔር ልጅ ከጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ በቀር ሌላ አምላክ የለምና አንተ ከሀዲ እፈር ብሎ ጮኸ። ይህንንም ድንቅ ተአምር አይተው ቁጥር የሌላቸው ብዙ አሕዛብ ክብር ይግባውና በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ አምነው በሰማዕትነት ሞቱ።

መኰንኑም ማሠቃየቱ በሰለቸው ጊዜ ራሱን በሰይፍ እንዲቆርጡ አዘዘ። የድል አድራጊነት አክሊልንም በመንግሥተ ሰማያት ተቀበለ።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞



በዚህችም ቀን ለአባቶች ሊቃነ ጳጳሳት አራተኛ የሆነው የእስክንድርያ ሊቀ ጳጳሳት አባ ከላድያኖስ አረፈ። ይህም ቅዱስ በወንጌላዊው ማርቆስ እጅ የክርስትና ጥምቀትን ተጠመቀ እርሱም ዲቁናን ሾመው ደግሞም ቅስናን ሾመው የቤተ ክርስቲያንንም ትምህርትና ሕግ ጠንቅቆ ተማረ።

አባ ሜልዮስም በአረፈ ጊዜ ይህን አባት መርጠው በእስክንድርያ ከተማ ሊቀ ጵጵስና ሾሙት ዐሥራ አንድ ዓመት ያህል በቀናች ሃይማኖት እያጸናቸው በትምህርትና በምክር ሁሉ እንደሚገባ የክርስቶስን መንጋዎች ጠበቀ። ልዑል እግዚአብሔርንም አገልገሎ በሰላም አረፈ።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞



በዚችም ቀን ሐዋርያው ቶማስ በመሸታ ቤት ባረድዋት በአንዲት ሴት ላይ ላደረገው ተአምር መታሰቢያ ነው።

አንድ ጎልማሳ በሐዋርያው ቅዱስ ቶማስ እጅ የተባረከ እንጀራን ከሕዝቡ ጋር ተቀብሎ ሊበላ ሲል እጆቹ ፈጽመው ደረቁ፡፡ እርሱንም ያዩት ሰዎች በዚህ ጎልማሳ ላይ የሆነውን ነገር ለሐዋርያው ነገሩት፡፡ ቅዱስ ቶማስም ልጁን ጠራውና ‹‹ልጄ ሆይ! የእግዚአብሔር ቸርነት በግልጽ ዘልፎሃልና ያደረከውን ነገር ንገረኝ?›› አለው፡፡ ጎልማሳውም ከሐዋርያው እግር ሥር ወድቆ ሰገደና ‹‹መልካም ሥራ የሠራሁ መስሎኝ ክፉ ሥራን ሠርቻለሁ፡፡ ይኸውም አስቀድሜ ወደ አንዲት የጠጅ አበዛ ሴት ልጅ እገባ ነበር፡፡ አንተም በንጽሕና እንድንኖር አስተማርኸን፤ ያችም ሴት አብሬያት እተኛ ዘንድ ነዘነዘችኝ፡፡ ስለዚህም ሰይፍ አንሥቼ አረድኳት›› አለው፡፡ ሐዋርያውም ‹‹እንዴት እንዲህ ያለ ቁጣና የአውሬ ሥራን ትሠራለህ?›› ብሎ ከገሠጸው በኋላ ውኃ አስቀርቦ በላዩ ጸለየበትና ጎልማሳውን ‹‹በዚህ ታጠብ ትድናለህ›› አለው፡፡ ጎልማሳውም በውኃው በታጠበ ጊዜ የደረቁ እጆቹ ዳኑ፡፡ ከዚህም በኋላ ቅዱስ ቶማስ ‹‹የዚያቸ ሴት በድን ወዳለበት ቦታ ምራኝ›› አለው፡፡ ጎልማሳውም መርቶ ከቦታው አደረሰው፡፡ ሐዋርያውም በድኗን ባየ ጊዜ እጅግ አዘነ፡፡ ወደ ውጭ አውጥተው በአልጋ ላይ እንዲያኖሯት ካዘዘ በኋላ እጁን በላይዋ ጭኖ ጸለየ፡፡ ጸሎቱንም በፈጸመ ጊዜ ጎልማሳውን ‹‹ሂድ እጇን ይዘህ ‹እኔ ቀድሞ በእጄ ገደልኩሽ፣ አሁን ግን በሃይማኖት በእኔ እጅ ክርስቶስ ያስነሣሽ› በላት›› አለው፡፡ ጎልማሳውም ቅዱስ ቶማስ እንዳዘዘው ባደረገ ጊዜ ፈጥና ከሞት ተነሣች፡፡ ከአልጋዋም ፈጥና ወርዳ ከቅዱስ ቶማስ እግር ሥር ወድቃ ሰገደችለት፡፡

ቅዱስ ቶማስም ለሞተች በኋላ የት እንደነበረች ያችን በሕዝቡ ሁሉ ፊት ጠየቃት፡፡ እርሷም በሲኦል እንደነበረችና በዚያም ያሉትን ልዩ ልዩ የሆኑ እጅግ ጽኑ ሥቃዮችን ሁሉ በዝርዝር ለሕዝቡ አስረዳች፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ቶማስም ከዚያ የነበሩትን ‹‹ይህች ሴት ሞታ እንደነበር አይታችኋል፣ አሁንም አይታ የምትመሰክረውን ሰማችሁን? በሲኦል ያለው ሥቃይ ብቻ አይደለም ነገር ግን ከዚህ የሚከፋ አለ፡፡ እናንተም የኃጢአትን ሥራና ክፉ ሀሳብን ትታችሁ ወደ እግዚአብሔር ተመለሱ፡፡ ትሕትናን፣ የዋህነትን፣ ፍቅርንና ንጽሕናን ጠብቁ ከእግዚአብሔር ዘንድ ጸጋን ትቀበላላችሁ›› አላቸው፡፡ ሕዝቡም ሁሉ በክብር ባለቤት በጌታችን አመኑ፡፡ ለድኆቸም ምጽዋትን ሊሰጡ ብዙ ገንዘብ ሰብስበው አመጡ፡፡ ለድኆች ምጽዋት መስጠት ለሐዋርያው ልማዱ ነበርና፡፡ ወሬውም በሀገሩ ሁሉ ተሰማና ሕመምተኞችን ሁሉ ሰብስበው አምጥተው በፊቱ ጣሏቸው፡፡ ቅዱስ ቶማስም ሁሉንም ፈወሳቸው፡፡

ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን፤ ልመናዋ በረከቷም ወንዶችና ሴቶች ባሮቿ ከሆን ከሁላችን የክርስቲያን ወገኖች ጋራ ይኑር፣ በቅዱሰኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

( እና )

 ሰኔ ሃያ በዚች ቀን በኬልቄዶን አውራጃ በቂሣርያ አገር   ቤተ ክርስቲያን በተወደደ ልጅዋ እጅ የታነፀችበት ነው፣ ከገልገላ አውራጃ አለሙት ከምትባል ቦታ የሆነው የሳፋጥ ልጅ   አረፈ።✞✞✞...
27/06/2021



ሰኔ ሃያ በዚች ቀን በኬልቄዶን አውራጃ በቂሣርያ አገር ቤተ ክርስቲያን በተወደደ ልጅዋ እጅ የታነፀችበት ነው፣ ከገልገላ አውራጃ አለሙት ከምትባል ቦታ የሆነው የሳፋጥ ልጅ አረፈ።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

(ህንጸተ ቤተክርስቲያን)

ሰኔ ሃያ በዚች ቀን በኬልቄዶን አውራጃ በቂሣርያ አገር የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ቤተ ክርስቲያን ያለ ዕንጨት ያለ ጭቃና ውኃ በሦስት ደንጊያዎች በተወደደ ልጅዋ እጅ የታነፀችበት ነው።

ይኽም በዓል ከእመቤታችን 33ቱ በዓላት አንዱ ነው። ‹‹ህንጸተ ቤተ ክርስቲያን›› ይባላል። የመጀመሪያዋ ቤተ ክርስቲያን የታነጸችው በሰኔ 20 ቀን ነው። አናጺውም እራሱ ባለቤቱ መድኃኔዓለም ክርስቶስ ነው፤ ቦታው ፊልጰስዩስ ነው፤ ቤተክርስቲያኗ የተሰየመችው ደግሞ በእመቤታችን ስም ነው። እመቤታችን ካረገች በ4ኛ ዓመት ጳውሎስና ባርናባስ በፊሊጲስዮስ ገብተው አስተምረው ሕዝቡን አሳምነው ካጠመቁ በኋላ ‹‹እንግዲህ ወደ ቤተ ጣዖት አትሂዱ›› አሏቸው። አሕዛብ የነበሩትና አምነው የተጠመቁትም ‹‹የለመድነውን ከከለከላችሁን መካነ ጸሎት ስጡን›› አሏቸው። የከበሩ ሐዋርያትም ወደ ጴጥሮስና ዮሐንስም መልእክት ላኩባቸው። ጴጥሮስና ዮሐንስም ‹‹ያለ ጌታችን ፈቃድ አንዳች ልታደርጉ አይገባምና ጸልዩ እኛም እንጸልያለን›› ብለው መለሱላቸው። ሁሉም ሱባኤ ይዘው በጸሎት ተጉ። ጸሎትና ሱባኤያቸውን ከጨረሱ በኋላ ጌታችን በሞት ያረፉትን አስነሥቶ በሕይወት ያሉትንም ደቀመዛሙርቱን በደመና ጠቅሶ ፊልጵስዩስ ሰበሰባቸው። ጌታችን በኪሩቤል ጀርባ ላይ ሆኖ እልፍ አእላፍ መልአክትን አስከትሎ ይወርዳል እመቤታችን በቀኙ ነበረች። ቅዱስ ዮሐንስም ‹‹ጌታዬ ለምን ሰበሰብከን?›› ብሎ ጠየቀ። ጌታችንም ‹‹በእናቴ ስም ከጽንፍ እስከ ጽንፍ አብያተ ክርስቲያናት እንዲታነጹ ፈቃዴ ነውና ሕንጻ ቤተ ክርስቲያን ላሳያችሁ ሥርዓት ላስተምራችሁ ነው›› አለው። ይህንን ብሎ ወደ ምሥራቅ ወሰዳቸው። በዚያም ተራርቀው የነበሩ 3 ደንጊያዎች ነበሩ። ጌታችንም ሦስቱን ድንጋዮችን በተአምራት አቀራርቦ አንሥቶ ጎተታቸው። ድንጋዮቹም እንደ ሰም ተለጠጡ፣ እንደ ግድግዳም ሆኑ። ቁመቱን ወርዱን መጥኖ ለሐዋርያቱ ሠጣቸው። እነርሱም እሳት እንዳየው ሰም ከእጃቸው እየለመለሙ (እየተሳቡ) ቁመቱን 24 ወርዱን 12 ክንድ አድርገው ሠርተውታል።

ዳግመኛም የብርሃን ምሰሶ ወረደ በሰማያዊቷ ኢየሩሳሌም አምሳያ አድርጎ አነጻት ሁለንተናዋም ተጠናቀቀ። ከዚህም በኋላ ጌታችን ለሐዋርያቱ ‹‹እንግዲህ እናንተም እንዲህ አድርጋችሁ ሥሩ›› ብሏቸው ዐረገ። ሦስቱ ድንጋዮች የሥላሴን ሦስትነት ወደ አንድ ሆነው አንድ ሕንፃ መታጹ የሥላሴን አንድነት ያስረዳል። በአጠቃላይ የቤተ ክርስቲያን መታነጽ ለኛ ለክርስቲያኖች እጅግ ታላቅ በዓልና ደስታ ነው። ስለዚች ቤተ ክርስቲያን አባቶች ደማቸውን አፍሰውላታል፣ አንገታቸውን ለሰይፍ ሰጥተውላታል፣ አጥንታቸውን ከስክሰውላታል፣ ቆዳቸው ተገፏል፣ በድንጋይ ተወግረዋል፣ በእሳት ተቃጥለዋል፣ በአውሬ ተበልተዋል። ቤተ ክርስቲያን ግድግዳዋ ውኃ መሠረቷ ደም ነው። የማትታደስ ነገር ግን ከኃጢአት ከበደል የሚታደሱባት ርትዕት ናት። ይህች ቤተ ክርስቲያን ‹‹የክርስቶስ አካሉና ሙላቱ ናት።›› ኤፌ 1፡13፣ ቆላይ 1፡18፣14። እናም የዚህችን ቤተ ክርስቲያን ሥርዓት መጣስና ትምህርቷን መቆነጻጸል የክርስቶስን አካል ማድማት ነው።

ዳግመኛም በማግሥቱ ሰኔ 21 ቀን ጌታችን ድንግል እናቱን እመቤታችንንና ቅዱሳን መልአክትን አስከትሎ ወረደ። እመቤታችንን መንበር፣ ጴጥሮስን ተራዳኢ ካህን፣ እስጢፋኖስን ሠራዒ ዲያቆን አድርጎ ቀድሶ ለሐዋርያቱ አቁርቧቸዋልና ፍጹም ደስታም ሆነ።

ዳግመኛም ጴጥሮስን እጁን ጭኖ ፓትርያርክ አድርጎ ሾሞታል። በዚህም ጊዜ ሰማያውያን መላእክት ምድራውያን ሐዋርያት አንድ ሆነው አመስግነዋል። ከዚህ በኋላ ሐዋርያት ከጌታችን እንዳዩት በዓለም ዞረው ቤተ ክርስቲያን አንጸዋል። ከዚያ በፊት የነበረው የእነ ሰሎሞን ቤተ መቅደስ፣ የአይሁድ ምኩራብ፣ የአይሁድ ሥርዓተ አምልኮ መፈጸሚያ እንጂ የአዲስ ኪዳን የቁርባንም ሆነ የጥምቀት ሥርዓት መፈጸሚያ አልነበረም። እንኪያስ ‹‹ሐዋርያት የት ነበር ሕዝቡን የሚያጠምቁትና የሚያቆርቡት?›› ከተባለ እንደ ማርቆስ እናት ቤታቸውን ለሐዋርያት በሰጡ ‹‹በየአማኞቹ ቤት›› ይከናወን ነበር።

ሰኔ 20 ቀን ህንጸተ ቤተክርስቲያን (የቤተ ክርስቲያን መታነጽ) ታላቅ በዓል ነው። ቤተ ክርስቲያን እንደ እንግዳ ደራሽ እንደ ውኃ ፈሻሽ የመጣችና ሩቅ ብእሲ የመሠረታት ሳትሆን እራሱ ጌታችን አምላካችን በገዛ ደሙ የመሠረታት ናት። ሐዋ 20፡28። በዕለተ ዐርብ በዕፀ መስቀል ላይ ከጌታችን የፈሰሰው ቅዱስ ደም ቅዱሳን መላእክት በብርሃን ፅዋ ቀድተው በዓለም ሁሉ ረጭተውታል። ስለሆነም የጌታችን ወርቀ ደም በነጠበባቸው ቦታዎች ሁሉ ላይ ዛሬም ድረስ ቤተ ክርስቲያን ይሠራባቸዋል።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞



በዚህችም ዕለት ከገልገላ አውራጃ አለሙት ከምትባል ቦታ የሆነው የሳፋጥ ልጅ ታላቁ ነቢይ ኤልሳዕ አረፈ። የዚህም ነቢይ መጠራቱ እንዲህ ኾነ ኤልያስ አልፎ ሲሔድ የሳፋጥ ልጅ ኤልሳዕን በፊቱ ዐሥራ ሁለት ጥምድ አስጠምዶ ሲያሳርስ አገኘው እርሱም በነዚያ የተሾመ ነበር ኤልያስም ሔዶ መጐናጸፊያውን በላዩ ጣለበት።

ኤልሳዕም ጥማዱን ትቶ ኤልያስን ተከተለው ኤልሳዕም አባቴ እወድሃለሁ አንተንም እከተላሉሁ አለው ኤልያስም ብላቴናዬ አድርጌሃለሁና ተመለስ አለው። እርሱም ኤልያስን ከመከተል ተመለሰ ዐሥራ ሁለቱንም ጥምድ በሬዎች ወስዶ አረደ በላመ ፈጅ ጋኖችም ቀቅሎ ለሕዝቡ አቀረበላቸው እነርሱም በሉ ኤልያስንም ተከትሎት ሔደ ብላቴናውም ሆነ።

ብዙ ዘመናትም ሲያገለግለው ኖረ። ኤልያስም በሚያርግበት ጊዜ ኤልሳዕን ከአንተ ተለይቼ ወደ ሰማይ ሳልወጣ አደርግልህ ዘንድ የምትሻውን ለምነኝ አለው ኤልሳዕም በአንተ ያደረ ሀብተ መንፈስ ቅዱስ እጥፍ ሆኖ ይደርብኝ አለው።

ኤልያስም ኤልሳዕን ድንቅ ነገርን ለመንከኝ ነገር ግን ከአንተ ተለይቼ ወደ ሰማይ ስወጣ ብታየኝ ይደርብህ ከአንተ ተለይቼ ወደ ሰማይ ስወጣ ባታየኝ ግን አይሆንልህም አለው።

ሁለቱም እየተነጋገሩ ሲሔዱ የእሳት ፈረስና የእሳት ሠረገላ መጣ ወደ መካከላቸውም ገብቶ አራራቃቸው ኤልያስም በመነዋወጥና በጥቅል ነፋስ እንደዚህ ወደ ሰማይ ዐረገ። ኤልሳዕም አይቶ የእስራኤል ኃይላቸውና ጽንዓታቸው አባ አባ ብሎ ጮኸ። ከዚህ በኋላም ዳግመኛ አላየውም ልብሶቹንም ከሁለት አድርጎ ከፈላቸው። ኤልያስም ለኤልሳዕ መጠምጠሚያውን ጣለለት በኤልሳዕ ራስ ላይም ወረደ ኤልሳዕም ተመልሶ በዮርዳኖስ ባሕር ዳር ቆመ። በራሱ ላይ የወረደች የኤልያስንም መጠምጠሚያ ይዞ ውኃውን መታባት ውኃውም አልተከፈለም የኤልያስ ፈጣሪ ወዴት ነው ይህስ እንዴት ነው አለ ከዚህ በኋላም ውኃውን መታው ውኃውም ተከፍሎ ወዲያና ወዲህ ቆመ ኤልሳዕም ተሻገረ።

በዚህም ኤልሳዕ የመንፈስ ቅዱስን ሀብት በዕጥፍ እንደተቀበለ ታወቀ። ኤልያስ የወንዙን ውኃ እንድ ጊዜ ከፈለ። ኤልሳዕ ግን ሁለት ጊዜ ከፈለ ኤልያስ አንድ ምውት አስነሣ ኤልሳዕ ግን ሁለት ምውት አስነሣ።

ከዚህም በኋላ ሒዶ ወደ ኢያሪኮ ገባ የዚያች አገር ሰዎችም ጌታችን እነሆ እንደምታያት የዚች አገር ኑሮዋ ያማረ ነው የአገሩ ውኃ ግን ክፉ ነው ሴቶች ሲጠጡት ይመክናሉ አሉት ኤልሳዕም ጨው ጨምራችሁ አዲስ ሸክላ አምጡልኝ አላቸው እነርሱም አመጡለት። ኤልሳዕም ወደ ውኃው ምንጭ ሒዶ ያንን ጨው በውኃው ምንጭ ጨመረው እንዲህም አላቸው እግዚአብሔር እንዲህ ይላል እርሱን ከመጠጣት የተነሣ የሚሞት እንዳይኖር የሚመክንም እንዳይኖር ይህን ውኃ አጣፈጥሁት። ከዚያች ቀን ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ኤልሳዕ እንደተናገረ ያ ውኃ ጣፋጭ ሆነ።

ከዚያም አገር ወደ ቤተል ወጣ ሲወጣም ከከተማው ሲወጡ ታናናሽ ልጆችን በጎዳና አገኘ እነርሱም አንተ ራሰ በራ ውጣ ውጣ እያሉ ይዘባበቱበት ጀመር። ወደ ኋላው ተመልሶ በአያቸውም ጊዜ የእግዚአብሔርን ስም ጠርቶ ረገማቸው የዚያን ጊዜ ሁለት ድቦች ከዱር ወጥተው ከእነርሱ አርባ ሁለት ልጆችን ገደሉ።

ከነቢያት ልጆች አንዲት ሴት ነበረች ወደ ኤልሳዕም ጮኸች ባሪያህ ባሌ ሞተ ባሌ እግዚአብሔርን የሚፈራ ሰው እንደ ነበረ አንተ ታውቃለህ ባለዕዳ ሁለቱን ልጆቼን ወስዶ ይገዛቸው ዘንድ መጣ አለችው። ኤልሳዕም አደርግልሽ ዘንድ ምን ትሻለሽ በቤትሽስ ምን አለሽ አላት ዘይት ካለበት ማሰሮ በቀር ለእኔ ለባሪያህ ምንም የለኝም አለችው።

ሔደሽ ከጎረቤትሽ ሁሉ የሸክላ ዕቃና ባዶ ዕቃዎችን ተዋሺ አታሳንሺ። ወደ ቤትሽም ገብተሽ በአንቺና በልጆችሽ ላይ ደጁን ዝጊ በዚያ በሸክላ ዕቃም ዘይቱን ገልብጪው የመላውንም አንሥተሽ አኑሪው አላት። እርሷም ወደ ቤቷ ገብታ በልጆቿና በእሷ ደጃፏን ዘጋች እነርሱ ያቀርቡላት ነበር እርሷም እየቀዳች ትገለብጥ ነበር። ከዚህ በኋላ ልጆቿን ዳግመኛ የሸክላ ዕቃ አቅርቡልኝ አለቻቸው የሸክላ ዕቃ ሁሉ አለቀ የለም አሏት ከዚህ በኋላ ያም ዘይት ተገታ።

እርሷም ሒዳ ለእግዚአብሔር ነቢይ ነገረችው አልሳዕም ሒጂ ይህን ዘይት ሸጠሽ ዕዳሽን ክፈዪ የቀረውን ዘይት ግን የልጆችሽን ሰውነትና ያንቺን ሰውነት አድኚበት አላት።

ከዚህም በኋላ ኤልሳዕ በአንዲቱ ቀን ወደ ሱማን ሔደ በዚያም አገር አንዲት ታላቅ ሴት ነበረች ወደዚያ ከመሔድ ውሎ አድሮ ነበርና እህል ይበላ ዘንድ አቆመችው። ያቺም ሴት ባሏን እነሆ ይህ የእግዚአብሔር ነቢይ ቅዱስ ነው ዘወትር በእኛ ዘንድ እያለፈ ይሔዳል። ትንሽ እልፍኝ እንሥራለት አልጋም እንዘርጋለት መብራት የሚበራበት መቅረዝንና ወንበርን ጠረጴዛንም እናዘጋጅለት ወደ እኛም በመጣ ጊዜ በዚያ ይደር አለችው።

ከዚህም በኋላ በአንዲቱ ቀን ወደዚያ ገብቶ በእልፍኙ አደረ። ደቀ መዝሙሩ ግያዝንም ያቺን የሱማን ሴት ጥራት አለውና ጠራት እርሷም መጥታ በኤልሳዕ ፊት ቆመች። እነሆ ይህን ሁሉ ክብር አከበርሽኝ ምን ላድርግልሽ ከንጉሥ ዘንድ ከአለቃም ዘንድ ቢሆን ጉዳይ እንዳለሽ ንገሪኝ በላት አለው እርሷም እኔስ በወገኖቼ መካከል እኖራለሁ አለችው። ምን ላድርግላት አለ ደቀ መዝሙሩ ግያዝም ልጅ የላትም ባሏም ሽማግሌ ነውና የሚታዘንላት ሴት ናት አለው። ደግሞ ጥራት አለው በጠራትም ጊዜ መጥታ በደጃፍ ቆመች። ኤልሳዕም የዛሬ ዓመት እንደዛሬ ልጅ ትወልጃለሽ አላት እኔን አገልጋይህን ጌታዬ አታሰቅቀኝ አለችው።

ከዚህም በኋላ ያቺ ሴት ፀንሳ ኤልሳዕ በነገራት ቀን በዓመቱ ወንድ ልጅን ወለደች። ያም ልጅ አድጎ ከአባቱ ጋራ ወደ አዝመራው መጣ። አባቱን ራሴን ራሴን አለው የሕፃኑም አባት ብላቴናውን ወደ እናቱ አስገባው አለው። ብላቴናውም ያንን ልጅ ወደ እናቱ አስገባው እናቱም እስከ ቀትር በጉልበቷ ላይ አስተኛችው።

ከዚህም በኋላ በሞተ ጊዜ አውጥታ በእግዚአብሔር ነቢይ ዐልጋ ላይ አስተኛችው ዘግታበትም ወጣች። ባሏንም ጠርታ ወደ እግዚአብሔር ነቢይ እሔዳለሁና አንድ አህያና ከብላቴኖች አንድ ብላቴና ስደድልኝ አለችው። ባሏም መባቻ ያይደለ ቅዳሜ ያይደለ ዛሬ ለምን ትሔጃለሽ አላት እጅ እነሣው ዘንድ እሔዳለሁ አለችው። አህያውንም ጫኑላት አገልጋይዋንም ተነሥ እንሒድ ባልኩህ ጊዜ መሔድን አትከልክለኝ ና ተከተለኝና ወደ እግዚአብሔር ነቢይ ወደ ቀርሜሎስ እንሒድ አለችውና ሔደች።

ኤልሳዕም ያቺን ሴት ስትመጣ በአያት ጊዜ ብላቴናው ግያዝን ያቺ ሴት ሱማናዊቷ ሴት ናት። አሁንም ሩጠህ ሒደህ ተቀበላት ደኅና ነሽን ባልሽስ ደኅና ነውን ልጅሽስ ደኅና ነውን በላት አለው እርሷም ደኅና አለችው። ወደ ኤልሳዕም ዘንድ ወደ ተራራው ደርሳ እግሩን ያዘችው ግያዝም ሊከለክላት መጣ ኤልሳዕም ሰውነቷ አዝናለችና ተዋት እግዚአብሔር ግን ነገሩን ሠውሮኛልና አልነገረኝም አለው። አታሰቅቀኝ ያልኩህ አይደለምን በውኑ እኔ ከአንተ ከጌታዬ ልጅን የለመንኩት መለመን አለን አለችው።

አልሳዕም ግያዝን ወገብህን ታጠቅ በትሬንም በእጅህ ይዘህ ሒድ ሰውም ብታገኝ እንዴትነህ አትበለው እንዴት ነህ ቢልህም አትመልስለት በትሬንም በሕፃኑ ግንባር ላይ አስቀምጣት አለው። የዚያም ሕፃን እናት እንዳልተውህ ሕያው እግዚአብሔርን በረከትህን አለችው ኤልሳዕም ተነሥቶ አብሮአት ሔደ። ግያዝም በፊታቸው ይሔድ ነበር ሩጦም ቀደማቸው በትሩንም በዚያ ልጅ ግንባር ላይ ጣላት ነገር ግን አልሰማውም አልተናገረውም ግያዝም ተመልሶ ኤልሳዕን ተቀብሎ ያ ልጅ አልተነሣም አለው።

ኤልሳዕም ወደ ቤት ገብቶ ሕፃኑን ሙቶ በዐልጋ ላይ ተኝቶ አገኘው በሁለታቸውም ላይ ደጃፉን ዘግቶ ወደ እግዚአብሔር ጸለየ። ወደ ዐልጋውም ላይ ወጥቶ በዚያ ሕፃን ላይ ተኛ አፉን በአፉ ላይ ዐይኖቹን በዐይኖቹ ላይ እጆቹንም በእጆቹ ላይ አድርጎ በላዩ ላይ ተኛ የዚያም ልጅ ሰውነት ሞቀ።

ከዚህ በኋላ ተነሥቶ በቤቱ ውስጥ ወዲያና ወዲህ ተመላለሰ ዳግመኛም ወጥቶ በዚያ ልጅ ላይ ተኛ እስከ ሰባት ጊዜ እንዲህ አደረገ ከዚያም በኋላ ያ ልጅ ዐይኑን ገለጠ ኤልሳዕም ግያዝን ጠርቶ ያቺን ሱማናዊት ሴት ጥራት አለው።

ጠርቷትም ወደርሱ ገባች ኤልሳዕም እነሆ ልጅሽን ውሰጂ አላት እርሷም ከእግሩ ላይ ወድቃ ሰገደችለት ልጅዋንም ይዛ ወጣች። የሶርያ ሰው ንእማንም ወደርሱ በመጣ ጊዜ በዮርዳኖስ ውኃ ከለምጹ አዳነው ንእማንም ብዙ እጅ መንሻ ወርቅና ብር ልብሶችንም አመጣለት ከእርሱም ምንም ምን አልወሰደም።

ደቀ መዝሙሩ ግያዝም ተደፋፍሮ ንእማንን ተከተለው ምክንያትም ፈጥሮ ንእማንን እንዲህ አለው ከኤፍሬም አገር ከነቢያት ልጆች ሁለት ሰዎች መጥተውብኛልና አንድ መክሊት ብርና ሁለት ልብሶች ስጣቸው ብሎሃል አለው ንእማንም ሁለት መክሊቶችንና ሁለት ልብሶችን ሰጠው።

ኤልሳዕም ግያዝ ያደረገውን አውቆ ረገመው የንእማንም ለምጽ ገንዘብ ወዳጅ በሆነው በግያዝ ላይ ተመለሰ። በሰማርያም ረኃብ ጸና ከሶርያ ሰዎች የተነሳ የአህያ መንጋጋ በአምሳ ወቄት ብር እስቲለወጥ ድረስ ኵስሐ ርግብም የድርጎ አራተኛ በአምስት ብር እስቲሸመት ድረስ በሀገራቸው የሶርያ ሰዎች ሰፍረው ተቀመጡ። በዚህ ነቢይ ጸሎትም በአንዲት ቀን ረኃቡ ተለወጠ ጥጋብም ሆነ። በዘመኑም ብዙ ድንቆችና ተአምራቶችን አደረገ በሞተም ጊዜ በመቃብር ውስጥ አኖሩት በዚያም ወራት የሞአብ ሰዎች አገራቸውን ከበቡ። ይቀብሩም ዘንድ ሌላ ሰውን አመጡ አደጋ ጣዮችንም በአዩ ጊዜ የዚያን ሰው ሬሳ በኤልሳዕ መቃብር ላይ ጣሉት የዚያም ሰው ሬሳ በኤልሳዕ ዐፅም ላይ ወረደ የኤልሳዕንም ዐፅም በነካው ጊዜ ያ በድን ድኖ በእግሮቹ ቆመ።

ይህም ነቢይ በአራት ነገሥታት ዘመን ትንቢት ተናገረ እሊህም ኢዮራም፣ አካዝያስ፣ ኢዩና፣ ዮአስ ናቸው የትንቢቱም ዘመን ከሀምሳ ዓመት በላይ ነው። ክብር ይግባውና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ዓለም ከመምጣቱ አስቀድሞ ትንቢት ተናገረ ከዚህ በኋላም በሰለም አረፈ።

ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን፤ ልመናዋ በረከቷም ወንዶችና ሴቶች ባሮቿ ከሆን ከሁላችን የክርስቲያን ወገኖች ጋራ ይኑር፣ በቅዱሰኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

( እና )

ሰኔ 17ጌታም ለአቡነ ገሪማ የሞት ጥላ እንደማያገኝህ ታላቅ የምሥራች እነግርሃለው ።ይህንንም ተናግሮ ሰላምታም ሰጥቶት በታላቅ ክብር ወደ ሰማይ አረገ።ቅዱስ አባ ገሪማም በልቡ ደስ ተሰኘ ወዲ...
25/06/2021

ሰኔ 17

ጌታም ለአቡነ ገሪማ የሞት ጥላ እንደማያገኝህ ታላቅ የምሥራች እነግርሃለው ።ይህንንም ተናግሮ ሰላምታም ሰጥቶት በታላቅ ክብር ወደ ሰማይ አረገ።ቅዱስ አባ ገሪማም በልቡ ደስ ተሰኘ ወዲያውኑም በብርሃን ሠረገላ ተነጥቆ ብሔረ ሕያዋን ገባ ።

ስንክሳር ዘ ወርሃ ሰኔ 17

ቅዱስ ሥዕሉ በሠዓሊ ዘሪሁን ገ ወልድ ተሣለ

ይህን ገፅ ጠቃሚ ነው ብለው ካመኑ ለወዳጅ ዘመድዎ ያጋሩ ላይክ ያድርጉ ሃሳብዎትን ይጻፉ

ጾም ሙሽሪትን ትመስላለች፤ ሙሽሪትን በሠርግ አዳራሽ ኾነው የሚቀበሏት ሰዎች ቤቱን ያስጌጡታል፤ ይሸልሙታል፡፡ ወደ ሠርጉ አዳራሽ የሚገባውን ሰው የሠርግ ልብስ ለብሶ እንደኾነ፣ የቆሸሸ እንዳል...
21/06/2021

ጾም ሙሽሪትን ትመስላለች፤ ሙሽሪትን በሠርግ አዳራሽ ኾነው የሚቀበሏት ሰዎች ቤቱን ያስጌጡታል፤ ይሸልሙታል፡፡ ወደ ሠርጉ አዳራሽ የሚገባውን ሰው የሠርግ ልብስ ለብሶ እንደኾነ፣ የቆሸሸ እንዳልኾነ አይተው ያስገቡታል፡፡ እኛም እንዲኽ ልንኾን ይገባናል ብዬ እነግራችኋለኹ፡፡ ልቡናችንን በማንጻት፣ ልል ዘሊል ከመኾን በመራቅ፣ የክፋት እርሾን በማስወገድ፣ ከጾም ጋር አብረው የሚመጡትን የሚያጅቧትን መልካም ምግባራትንም ለመቀበል የልቡናችንን ውሳጤ በመክፈት የምግባር እናት፣ የማስተዋል እንዲኹሉም ለሌሎች ምግባራት ኹሉ ንግሥት የምትኾን ጾምን ልንቀበላት ይገባናል ብዬ እነግራችኋለኹ፡፡ ይኽን ያደረግን እንደኾነ ታላቅ ሐሴት እናደርጋለን፤ ርሷም ቁስለ ነፍሳችንን ትፈውስልናለች፡፡ በሌላ አገላለጽ ብነግራችኁ ሐኪሞች በአንድ ታማሚ ሰውነት ውስጥ ያለውን ቆሻሻ፣ መርዘኛ ፈሳሽን ማስገድ ሲፈልጉ መጀመሪያ የሚያደርጉት ነገር ቢኖር ታማሚው ምግብ ከመውሰድ እንዲቈጠብ ነው፡፡ ታማሚው ለጊዜው ምግብን ከመብላት ካልተከለከለ ሓኪሞቹ የሚሰጡት መድኃኒት እንደተፈለገው ውጤት አይሰጥም፡፡ እኛም ቁስለ ነፍስ ቁስለ ሥጋ የምትፈውሰውን ጾም ስንቀበላት ከዚኽ በላይ ልንኾን ይገባናል ብዬ እነግራችኋለኹ፡፡ ድኅነተ ሥጋ ድኅነተ ነፍስን የምንሻ ከኾነ ልቡናችንን ንጹሕና ንቁ በማድረግ ልንወስዳት ይገባናል፡፡ እንዲኽ ካልኾነ ግን ከጥቅሟ ይልቅ ጉዳቷ ያመዝናል፡፡



 !ማርያምን ያህል እናት ሰቶን ጸጋ የመላባት የማይደክሙ ጠባቂዎችን መላእክትን ሰቶን ከምግብ መርጦ ስጋውን ሰቶን ከመጠጥ መርጦ ደሙን ሰቶን፤ ትልቁን ሰላም ሰቶን ጥቂት ሰላም ፍለጋ ሁላችሁም...
04/06/2021

!

ማርያምን ያህል እናት ሰቶን ጸጋ የመላባት የማይደክሙ ጠባቂዎችን መላእክትን ሰቶን ከምግብ መርጦ ስጋውን ሰቶን ከመጠጥ መርጦ ደሙን ሰቶን፤ ትልቁን ሰላም ሰቶን ጥቂት ሰላም ፍለጋ ሁላችሁም መዝሙር ያልሰጣችሁን ሰላም ዘፈን ሊሰጣችሁ በየኢንተርኔቱ ስትርመሰመሱ የምትውሉ ትኖራላቹ እንኖራለን።

ከድራማ የራሳችሁ ህይወት ድራማ ሁኖ ድራማ ሌላ ድራማ ስታሻትቱ ትውላላችሁ። በእግዚአብሔር ቤት ያላገኘነውን ሰላም የትም አናገኘውም። ርካሽ ነገር ፍለጋ ህሊና ሰማያዊ አጣን ማስተዋሉን ይስጠን።

እንኳን አደረሳችሁ ዳግማይ ትንሳኤዳግማይ ትንሣኤ (ሁለተኛው ትንሳኤ) ማለት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶ ከሙታን ተለይቶ በተነሳ በስምንተኛው ቀን በዕለተ እሑድ ደቀመዛሙርቱ በአንድነት ተሰብስበው ...
09/05/2021

እንኳን አደረሳችሁ

ዳግማይ ትንሳኤ
ዳግማይ ትንሣኤ (ሁለተኛው ትንሳኤ) ማለት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶ ከሙታን ተለይቶ በተነሳ በስምንተኛው ቀን በዕለተ እሑድ ደቀመዛሙርቱ በአንድነት ተሰብስበው ሳሉ ለሁለተኛ ጊዜ ተገልጦ ትንሳኤው ምትሐት ያይደለ ፍጹም አማናዊ እንደሆነና እንደ ቶማስ የተጠራጠረውን ና ንካኝ በማለት ያሳመነበት ዕለት ነው፡፡ዳግማይ (ሁለተኛ) ያሰኘው መገለጡን ይዞ ነው፡፡ቅድስት ቤተ ክርስቲያንም ትንሳኤ ባለፈ የሚመጣውን እሑድ ሰይማ ታከብረዋለች፡፡ /ዮሐ20፤24-30/
ጌታችን ስለምን ዳግመኛ ተገለጠ?
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለሐዋርያቱ ቀድሞ በተዘጋ ግንብ ገብቶ ሰላም ለእናንተ ይሁን ብሎ ተገልጦላቸው ነበር ዳግመኛም ሐዋርያው ቶማስ ባለበት ተገለጠላቸው ምክንያቱም ደግሞ
1ኛ.ካልዳሰስኩ አላምንም ያለ ሐዋርያው ቶማስን ሊያሳምነው ፡- ቶማስን ደቀመዛሙርቱ መጥተው ጌታችንን በመካከላችን ተገልጦ አየነው ብለው ሲነግሩት ‹‹የችንካሩን ምልክት በእጄ ካላየሁ ጣቱንም ወደ ተቸነከረበት ካልጨመርሁ እጄንም ወደ ጎኑ ካላገባሁ አላምንም ›› ብሎ ነበርና ና ንካኝ ብሎ አሳምኖታል፡፡ቶማስ ለምን ተጠራጠረ ብንል ፈሪሳዊ ስለነበረ ነው፡፡ፈሪሳውያን ትንሳኤ ሙታን የለም ብለው ያምናሉ /በማቴ.ወ22፤23-33/ ሃይ.አበው 48፤8-13 ገጽ255/ እርሱም ከሞት በኋላ ሕይወት አለ ብሎ አያስብም ነበር፡፡የጌታችንን ጎን የነካች የቶማስ እጅ በኋላ ላይ ሳትበሰብስ በሕያውነት ለብዙ ዘመናት ኖራለች፡፡ሀገረ ስብከቱና ሰማዕትነት በተቀበለባት በሕንድ ሀገር ከታቦት ጋር ከመንበሩ ላይ ያኖሯት ነበር፡፡በዓመት በዓመት በእመቤታችን በዓል በአስተርዕ ሊያጥኑ ሲገቡ የሚሾመውን ወጥታ ቀኝ እጁን ትይዘዋለች ዓመት አገልግሎ ያርፋል በዓመቱ ሊያጥን ሲገባ ትይዘዋለች እንዲህ እያለች ትኖራለች፡፡
ሌላው ቶማስን ‹‹ ና ጎኔን ንካ›› ሲለው በኋላ በዓለም ዞሮ ወንጌልን የሚሰብክ ነውና ሐዋርያ ከሆነ ዘንድ ደግሞ ‹‹ሐዋርያት እንዳሉት ጌታችን ተነስቷል›› ብሎ ያስተምር ዘንድ አይገባውም ይልቁንም እንደ ወንጌላዊው ዮሐንስ ‹‹በጆሮአችን የሰማነውን በዓይኖቻችንም ያየነውንን የተመለከትነውን እጆቻችን የዳሰሱትን እንነግራችኋለን ሕይወት ለእኛ ተገልጻለችና አየናት›› 1ኛዮሐ1፤1-2 እንዳለው ቶማስን ና ንካኝ ብሎታል፡፡በእርግጥ ‹‹ሐዋርያት እንዲህ አለ›› ብሎ ማስተማር ስህተት ሆኖ አይደለም ምክንያቱም እነ ጳውሎስ ጌታችን ሲነሳ አላዩም ግን እንደ ሐዋርያት በዓለም ወንጌልን አዳርሷል ፡፡ነገር ግን ቶማስ ከ12ቱ ሐዋርያት አንዱ ስለሆነ ግድ ሆኖበታል፡፡

2ኛ.ሰንበትን ሲያጸናልን ፡- የክርስቲያኖች ሰንበት የምንላት ዕለተ እሑድ ጌታችን ሞትን ድል አድርጎ የተነሳባት በመሆኗ የእረፍት የመንግስተ ሰማይ አምሳል ብለን እናከብራታለን፡፡ የዕለቲቱንም ክብርትነት እንድናስብና ዕለተ እሑድ በመጣች ቁጥር ጌታችን የተነሳባትና ለሐዋርያቱ ትንሳኤውን ደግሞ የገለጠባት እንደሆነ እንድናስብ ለአክብሮተ ሰንበት ደግሞ ተገለጠላቸው፡፡አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ ‹‹የእሑድ ቀን የክርስቶስ ቀን ናት እሑድ ሰንበትም ተባለች›› መጽ.ምስ ገጽ296

3ኛ.ትንሳኤው ምትሐት እንዳልሆነ ለማስረዳት፡-ጌታችን ራሱ የተገለጠበትን ዓላማ ሲነግራቸው ‹‹እጄን እግሬን እዩ ዳስሱኝም እኔ እንደሆንኩ ዕወቁ በእኔ እንደምታዩት ለምትሐት አጥንትና ሥጋ የለውምና›› ሉቃ24፤39 እንዳላቸው የጌታችን ትንሳኤ ምትሐት ያይደለ አማናዊ በቀደመው ተዋሕዶ ባለመለወጥ እንደተነሳ ለማጠየቅ ተገለጠላቸው፡፡ሲገለጥም በተዘጋ ግንብ መግባቱ መለኮት አለመለየቱንና ወደ ሥጋ መለወጥ እንዳላገኘው ያስረዳል፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

Address

Addis Ababa
1000

Alerts

Be the first to know and let us send you an email when አኮቴት Akotet posts news and promotions. Your email address will not be used for any other purpose, and you can unsubscribe at any time.

Share