03/06/2026
“የማይንቀሳቀስ ንብረት (ቤትና መሬት) ሲገዙ ማረጋገጥ ያለብዎት 5 ወሳኝ ነገሮች” ፦ የሕይወት ዘመን ጥሪትዎ በአጭበርባሪዎች እንዳይበላ!
የዓመታት ልፋትና ጥሪትዎን አውጥተው የመሬት ወይም የቤት ግዢ ከመፈጸምዎ በፊት “የባለቤትነት ማረጋገጫ ደብተር (ካርታ)” ማየትዎ ብቻ በቂ ይመስልዎታል? በፍጹም አይደለም! ይህንን ስህተት ከሰሩ ገንዘብዎንም መሬቱንም ሊያጡ ይችላሉ።
በአገራችን የመሬትና የቤት ሽያጭ ከፍተኛ የገንዘብ ዝውውር የሚደረግበት ቢሆንም፣ በዚያው ልክ በርካታ ዜጎች የሚታለሉበትና የሕይወት ዘመን ቁጥባቸውን የሚያጡበት ዋነኛ መስክ ሆኗል። ብዙ ጊዜ ገዢዎች በደላላ ግፊት ወይም “ካርታ አለው” በሚል መተማመን ብቻ ውል ውስጥ ይገባሉ። ነገር ግን መሬት በኢትዮጵያ ሕገ-መንግሥት አንቀጽ 40(3) መሠረት የሕዝብና የመንግሥት ንብረት በመሆኑ፣ እኛ የምንገዛውና የምንሸጠው “የመጠቀም መብትን” (Leasehold/Possession) ብቻ ነው።
ስለሆነም ግዢ ከመፈጸምዎ በፊት የሚከተሉትን 5 ነጥቦች በሕግ ፊት ማረጋገጥ አለብዎት፦
1) የካርታው ትክክለኛነት (Search)፦ ካርታው በእጅዎ ቢኖርም፣ በክፍለ ከተማ ወይም በወረዳ የመሬት ማኔጅመንት ቢሮ በአካል ቀርበው መሬቱ ዕገዳ (Injunction) ያለበት መሆን አለመሆኑን እና ካርታው በሲስተም ውስጥ መኖሩን ማረጋገጥ አለብዎት።
2) የጋራ ንብረትነት (የባልና ሚስት)፦ መሬቱ በባል ወይም በሚስት ስም ብቻ የተመዘገበ ቢሆንም፣ በጋብቻ ጊዜ የተፈራ ከሆነ የሁለቱም የጋራ ንብረት ነው። የትዳር አጋር ሳይስማማና ሳይፈርም የሚደረግ ሽያጭ በሕግ ፊት ፈራሽ (Void) ይሆናል።
3) ክስ ወይም የፍርድ ቤት ዕገዳ፦ መሬቱ ወይም ቤቱ በፍርድ ቤት ክስ ሂደት ላይ ያለ ወይም በዕዳ ምክንያት በባንክ የተያዘ (Mortgage) መሆን አለመሆኑን ማረጋገጥ።
4) የመንግሥት ልማት (የማስተር ፕላን) ስጋት፦ ቦታው ወደፊት ለመንገድ ማስፋፊያ፣ ለፓርክ ወይም ለሌላ የመንግሥት ልማት የተያዘ (አረንጓዴ ቦታ) መሆን አለመሆኑን ከወረዳው ማስተር ፕላን ማረጋገጥ።
5) ሕጋዊ ውል ማረጋገጫ፦ በኢትዮጵያ የፍትሐ ብሔር ሕግ ቁጥር 1723 እና 2877 ላይ በግልጽ እንደተደነገገው፣ ከማይንቀሳቀስ ንብረት (ከቤትና መሬት) ጋር የተያያዙ ማናቸውም ውሎች በሕግ ፊት የጸኑ እንዲሆኑ በግድ በጽሑፍ መደረግና በሕግ ሥልጣን በተሰጠው አካል (በሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ ኤጀንሲ/ውልና ማስረጃ) ፊት ቀርበው መመዝገብ አለባቸው። የመንደር ውል ወይም በደላላ ፊት የሚደረግ ውል በሕግ ፊት ዋጋ የለውም።ይህንን የሕግ ድንጋጌ ይበልጥ ያጠናከረውና በመላው አገሪቱ ባሉ ፍርድ ቤቶች ላይ አስገዳጅ ሕጋዊ ትርጉም የሰጠው የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት (በመዝገብ ቁጥር 21448 እና መሰል መዛግብት) ላይ የሰጠው ውሳኔ ነው። የሰበር ችሎት ውሳኔው እንደሚያስረዳው፦
“በማይንቀሳቀስ ንብረት ላይ የሚደረግ የሽያጭ ውል በሕግ ሥልጣን በተሰጠው የመንግሥት አካል ፊት ቀርቦ ካልተመዘገበ፣ ውሉ እንደ አልተደረገ (Void) ይቆጠራል። ውሉ ሕጋዊ ውጤት ስለማይኖረውም ገዢው የባለቤትነት መብት እንዲተላለፍለት የመጠየቅ መብት የለውም።
ሰዎች በተደጋጋሚ የሚሰሩት ስህተት፦ "ሰነዱ ዋናው ነው" በሚል በመተማመን ብቻ፣ የመሬት አስተዳደር ቢሮ ሄዶ ሳይንቀሳቀስና ሳይመረምር ሙሉ ገንዘብ መክፈል። አጭበርባሪዎች ከአንድ በላይ "የመጠባበቂያ" ወይም የሐሰት ካርታ አዘጋጅተው በአንድ ጊዜ ለ3 እና 4 ሰው ሊሸጡ እንደሚችሉ አይዘንጉ። በተጨማሪመ “ሻጩ የዋህ ሰው ነው፣ ምስክሮችም አሉን፣ ደረሰኝም ተጻጽፈናል” በሚል መተማመን የውልና ማስረጃ ምዝገባን ማዘግየት ወይም መተው። ሻጩ ከዓመታት በኋላ ዋጋ ሲጨምር ሃሳቡን ቀይሮ “ውሉ በሕግ ፊት አይጸናም፣ መሬቴን/ቤቴን መልሱልኝ” ብሎ ፍርድ ቤት ቢከስዎት፣ ቤቱ ላይ መብት እና ጥቅም አለኝ የሚል 3ኛ ወገን ተከራካሪ ቢከስ ሰበር ችሎት በሰጠው አስገዳጅ ትርጉም መሠረት ንብረቱን ለሻጩ እንዲመልሱ ይገደዳሉ። እርስዎ የሚመለስልዎት የከፈሉት ዋና ገንዘብ ብቻ ሊሆን ይችላል፤ ይህም በዋጋ ንረት ምክንያት የዛሬውን ዋጋ አይተካም።
ተግባራዊ የሕግ ምክር፦ ማንኛውንም የቅድመ-ክፍያ (Advance/Advance Payment) ከመክፈልዎ በፊት ከሻጩ ጋር በመሆን ወደ መሬት አስተዳደር ቢሮ በመሄድ የንብረቱን የነፃነት ማረጋገጫ (Clearance) በጽሑፍ ይጠይቁ። ውል ከመፈጸምዎ በፊት የሕግ ባለሙያ ወይም ጠበቃ ማማከር የሚጠይቀውን አነስተኛ ክፍያ በመፍራት፣ የነገውን ትልቅ ኪሳራ አይጋብዙ።
ይህ መረጃ ዛሬውኑ ለአንድ ቤት ወይም መሬት ለመግዛት ለሚያስብ ወዳጅዎ ሊደርስ ይገባል፤ Share በማድረግ ከትልቅ አደጋ ይታደጓቸው። መሬት ሲገዙ ያጋጠማችሁ ፈታኝ ነገር ካለ በኮሜንት ያካፍሉን።